«የትግራይ ህዝብ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቹን ተጠቅሞ ጽንፈኛው ህወሓት ላይ ጫና ማሳደር ይገባዋል» ፡- ዶክተር ኃይሉ አርዓያ

«የትግራይ ህዝብ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቹን ተጠቅሞ ጽንፈኛው ህወሓት ላይ ጫና ማሳደር ይገባዋል» ፡- ዶክተር ኃይሉ አርዓያ

መላው የትግራይ ህዝብ ነባር ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም አገር በማተራመስ ላይ ያለውን ፅንፈኛውን የህወሓት ቡድን በሰላም እጁን እንዲሰጥ ጫና ማሳደር እንደሚገባው የቀድሞው የቅንጅት አመራርና ፖለቲከኛ ዶክተር ኃይሉ አርዓያ አስታወቁ።

ዶክተር ኃይሉ አርዓያ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ላለፉት 27 ዓመታት ህዝብ ሲበድልና ሲያንገላታ መቆየቱ አልበቃ ብሎ ከሰሞኑ ደግሞ ሀገርን በመጠበቅ ላይ ባለ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙ የቡድኑን ከሃዲነት የሚያሳይ ነው።

ጥቃቱ የትግራይ ህዝብ ከኖረበት መልካም እሴት አኳያም ተፃራሪ የሆነ እኩይ ተግባር በመሆኑ ይህንን ኃይል በገሃድ ወጥቶ ሊያወግዘው ይገባል።ህወሓት አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ ተቻችሎ የኖረውን ህዝብ በብሔር በመከፈፋል እርስበርስ እንዲባላና እንዲገዳደል በማድረግ ከፍተኛ ወንጀል ሲፈጽም መቆየቱን አመልክተው፣ ይህ ጽንፈኛ ሃይል ባለፉት 27 ዓመታት አሰፈንኩ ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ከወረቀት ያልዘለለ፤ በተጨባጭ ህዝቡን ተጠቃሚ ያላደረገና አገሪቱን ወደ ለየለት አዘቅት ውስጥ የጨመረ መሆኑን አመልክተዋል።

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለእሱና እሱን ለሚከተሉ ብቻ ተለክቶ የተሰፋ እንጂ ህዝቡ የዚህ ዴሞክራሲያዊ መብት ተጠቃሚ እንዳልነበር የጠቆሙት ዶክተር ኃይሉ ፣ ለአብነትም የራያና አካባቢው ህዝብ ያለውዴታው በእነሱ ጨቋኝ አገዛዝ ውስጥ እንዲወድቅ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ይህ ህዝብ ይተዳደር የነበረው ከአድዋ በመጡ እንደራሴዎች ብቻ እንዲሆን መደረጉ በአገሩ ባይተዋር ሆኖ እንዲኖር ያደረጉት መሆኑን ገልጸዋል።

ጥቂት የማይባለው የአካባቢው ተወላጅ ጭቆናውን በመሸሽ ከአገር የተሰደደበት ሁኔታ መኖሩን አስታውሰው፤ ሥርዓቱን የተቃወሙ ወጣቶች ለእስራትና ለእንግልት ሲዳረጉ መኖራቸውን አመልክተዋል።

«የመከላከያ ሰራዊታችንም ሆነ መንግሥታችን በዚህ ኃይል ላይ እየወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ የምደግፈውና መቀጠል ያለበት ነው» ያሉት ዶክተር ኃይሉ፤ እርምጃው የአገርን ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ያለመ በመሆኑ ፅንፈኛው አካል እጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ መላው ህዝብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።በተለይም የትግራይ ክልል ህዝብ የዚህ ኃይል የጭቆና ቀንበር በዋነኝነት ያረፈበት እንደመሆኑ ከባህሉ ከወጉ ውጭ በመሆን ህዝብ ለማስጨረስ የወጣውን ኃይል በገሃድ መቃወምና ለህግ ራሱን አሳልፎ እንዲሰጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።«እውነተኛ ጀግና በሃቅ የሚያምን፤ ለሃቅ የሚሞት፤ ሲሳሳትም ስህተቱን አምኖ ከስህተቱ የሚመለስ ነው» ያሉት ዶክተር ኃይሉ፤ አገር በማተራመስ ላይ ያሉት እነዚህ የህወሓት አባላት ጀግና የህዝብ ልጅ ነን ብለው የሚያምኑ ከሆኑ ጊዜው ሳይረፍድባቸውና ብዙ ህዝብ ከማስጨረሳቸው በፊት ራሳቸውን ለህግ አሳልፈው ሊሰጡ እንደሚገባም መክረዋል።

የእስካሁኑ ግትርነታቸው በተለይም የትግራይን ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ ከመሆኑም ባሻገር የአገርንም ህልውና አደጋ ውስጥ የሚጥል በመሆኑ በአፋጣኝ ማሳሪያቸውን መጣል እንደሚጠበቅባቸውም አስታውቀዋል።

Share this post