ኮሮና ቫይረስ ና የስኳር በሽታ

ኮሮና ቫይረስ ና የስኳር በሽታ

ከተለያዩ  ሀገራት  የሚወጡ መረጃዎች እና ሰንጠረዦች እንደሚያሳዮት ከሆነ፤ በስኳር በሽታና በተያያዥ ህመም የተጠቃ ሰው በኮሮና ቫይረስ ከተያዘ ፡ ለበሺታ ከመጋለጥ ባሻጋር የመሞት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው። የወደፊቱ የአለማችን ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በምንመገበው ምግብ እና የኑሮ ዘይቤአችን መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።በጥንቃቄ እና እየመረጡ መመገብ ህይወትን ያተርፋል።በመሰረቱ ይህንን ግልፅ እውነታ ለመረዳት፤ አደገኛ የሆኑ ተላላፊ  በሽታዎች እስኪመጡ ድረስ  መጠበቅ የለብንም።ምክንያቱም ለሰውነታችን አስፈላጊ ያልሆኑ ምግቦች (junk food) ለበሽታ ተጋላጭ ከማድረጋቸውም ባሻገር ለሞት እንደሚያበቃ ሳይንስ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው። የህክምና እና የአመጋገብ ስርአት ባለሙያዎች ይህንን ጉዳይ አስመልክተው የተለያዩ ዘመቻዎችን ሲያደርጉ እና ምክሮችን ሲሰነዝሩ ኖረዋል።

እንደ ሀገራችን ባሉ ታዳጊ ሀገራት ባለፉት ጥቂት አሠርት ዓመታት የታየው የኢኮኖሚ ለውጥ በርካታ በረከቶችን ያመጣ ቢሆንም በዚያው ልክ ለተለያዩ ጉዳቶች መከሰት ምክንያት ሆኗል።  የመሠረተ ልማት አውታሮች በሰፊው መዘርጋት፣ ፈጣን የከተማ ልማት እና የሰዎች አማካይ የዕድሜ ጣሪያ መሻሻል የመሳሰሉት ሰፊ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች አስከትሎአል። ዛሬ ዛሬ በጣም በርካታ ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ፥ በእግር ከመራመድ ይልቅ፥ የተለያዮ የመጒዋጉዋዣ መንገዶችን ይመርጣሉ። ከመጠን በላይ የሰውነት ውፍረት እየጨመረ ነው። ዝቅተኛ የነጥረምግብ ይዘት ያላቸው ምግቦች (low-nutrition fast food ) እና አለቅጥ ስኳር የበዛባቸው ምግቦች መበርከት በህብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ እየደቀነ ነው። ይህም በምላሹ  በሀገሪቱ  የስኳር በሽታ መጠን እንዲጨምር አድርጓል። የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ቁጥር ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ከፍተኛው መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ከዚህ ቀደም ገልጽዋል፡፡ ማህበሩ የስኳር ህሙማን ቁጥር በፍጥነት እያደገ መምጣቱን  እና ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን አብራርቷል። በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 36 ዓመታት የአዋቂዎች ከመጠን በላይ ውፍረት (በተለምዶ ቦርጭ የምንለው) መጠኑ ወደ 500 ከመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ለሰውነታችን አስፈላጊ ያልሆኑ ምግቦችን እየተመገቡ ነው፡፡በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴም አያደርጉም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን በኮሮናቫይረስ ከሞቱት መካከል ምን ያህሎቹ ተያያዥ በሺታዎች እንደነበረባቸው አልተገለፀም። በአሜሪካን ሀገር 70 ከመቶ በላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው ናቸው።በፈረንሳይ ና በእንግሊዝ ሀዞች እንደሚያሳዩት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው በቫይረሱ የመሞት እድላቸው በእጥፍ ከፍ ያለ ነው። በሌላ አባባል ሰዎች መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ካርቦሃድሬት በመውሰድ ለበሺታ እየተጋለጡ ነው።ለዚህም በዋናነት ተጠያቂ የሆኑት ስኳር የበዛባቸው ምግቦች ሲሆኑ በርካታ ሰዎች ከሚጠጧቸው የለስላሳ መጠጦች እና ከሚመገቧቸው ዝቅተኛ የነጥረምግብ ይዘት ያላቸው (fast-food) ምግቦች ጋር ይያዛል። ስለዚህ አመጋገባቸን እና በአጠቃላይ እንቅስቃሴአቸን እናስተካክል።

Share this post