በሰላምታ ገደልኳት

በሰላምታ ገደልኳት

ከቤት ስወጣ እንደ ወትሮ እግሬን አፍታትቼ እመለሳለሁ ነበር እንጂ ይህንን ጒድ ጨርሶ አልጠበቅሁም።
ከወዲያ ማዶ ጐረበቴ ቢስኪሌት ስትጋልብ አይቻት በሩቊ በአገሬ ወግ ሰላም አልኳት። አፃፋ እመልሳለሁ ብላ አንድ እጇን ለሰላምታ ስታነሳ የቢስኪሌቱ መሪ ወለም ብሎባት ይመስለኛል ፍንግል አለች። “እኔን! እኔን!” ለማለት ርቀቱ አላመቸም፤ እያየኋት ምን ላርግላት? መንገዴን ቀጠልሁ…

ቆይቼ ስመለስ፣ አስፋልቱ ላይ ጒድ ተነጥፏል። አንቡላንስ በያዙኝ ልቀቊኝ ጩኸት ቀይ መብራት እያራገበ ሠፈሩን ደም በደም ለቅልቆታል። ማን ይሆን ደግሞ? ስል፣ ያቺው ጐረበቴ ሆና ተገኘች። በወሳንሳ አንከብክበው ይዘዋት ሄዱ። “ሰላም ስላልኳት፣ ሰላም ልትለኝ ቀኝ እጇን ስታነሳ በመሪ ወለምታ ወደቀች” ብል፣ ደግሞ ነገር ይጎትትብኛል ብዬ ሠግቼ። በሆዴ እንደ ያዝኩ እቤቴ ገባሁ።

በሳምንቱ እንዲሁ ሳገድም ባለቤቷን ከሽንት ቤት ሲወጣ አገኘሁት። “እንዴት ነህ ጃል? ሥራስ? ያቺን ቮልስ መኪናህን አሠራሃት ወይስ በልዋጭ ሸጥኻት?” ብዬ ዳር ዳር ካልኩ በኋላ፣ “ልጆች እንዴት ናቸው? ሚስትህ ደህና ነች ሰሞኑን አላየኋትም” አልኩት። የሰላምታዬን አኳኋን ለምዶ፣ “ደህና፣ ደህና፣ አመሰግናለሁ ስለ ጠየቅኸኝ። አዎን፣ ደህና ናቸው፣ አመሰግናለሁ ስለ ጠየቅኸኝ … (ትንሽ ተከዝ አለና) ሚስቴ ሆስፒታል ገባች እኮ! ከገባች ሳምንት ሆናት” አለኝ። “ቀኝ እጇን ለሰላምታ ስታነሳ የቢስኪሌቱ መሪ ወለም ብሎ እኰ ነው” ልል፤ እንደ መጣሁበት ጒዳይ በርትቼ ያዝ አረግሁት።

ሰው ለራሱ ባዳ ነው። በወሳንሳ የገባች፣ በወሳንሳ ወጣች። ልሸኛት ብል፣ ሽኝት ለቤተሰብ ብቻ ነው ተባለ። እኔም ቤተሰብ ነኝ እኮ ብዬ አልከራከር፤ የዐይኔን ዕርጥባን አይቀበሉ ሆነ ነገር። በዚያች መንገድ ባለፍኩ ቊጥር ቢስኪሌት የተፈናጠጠች ሴት ባይ ማማተር ሥራዬ ሆነ። ያቻትና! ቀኝ እጇን ለሰላምታ … ያቻት! ፍንግል ብላ … ሰላም ባላልኳት ምን ነበር? ሰላምታ ብነሳት ለልጆቿና ለባሏ ትተርፍ ነበር ይሆን?

© March 2006/2021 by Mitiku Adisu. All Rights Reserved.

Share this post