በርካታ አባላት የነበሩበትና ብዙ ዝግጀት የተደረገበት የኤትኖግራፊ ጉዞ ነበር። እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ዓ.ም. ከ1931 እስከ 1933 የተደረገው የዳካር ጂቡቲ የተልዕኮ ቡድን (Mission Dakar-Djibouti)።
የአፍሪካ አህጉርን እሴቶች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ የዕደ-ጥበብ ስራዎች፣ እንስሳት ፣ እጽዋት እንዳይጠፉ ለመታደግ መወሰድ ያለበት እርምጃ ነው በሚል ቅርሳ ቅርሶችን ሰብስቦ ወደ አውሮፓ በመላክ ሙዚየም ውስጥ ሰብስቦ ማስቀመጥን የሚያካትት ነው።ሌሎች ታዳጊ አገሮችን የማዳን ሃላፊነት አለብን በሚል ዕሳቤ ላይ የተመረኮዘ የምዕራቡ ዓለም አመለካከት። የተደረገው ነገር ግን የእነዚህን የአፍሪካ ሀገራት ውድ ቅርሶችን በመውሰድ፤ የአውሮፓን ሙዜሞችን የማበልፀግ ሥራ ነበር።
በኤትኖሎጂስቱ ፈረንሳዊው ማርሴል ግሪዩል (1898-1956) የተመራው ይህ የልዑካን ቡድን ከሰሃራ በታች ያሉትን የአፍሪካ ሀገራትን ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ በማቆቋራረጥ፣ ከአትላንቲክ ወደ ቀይ ባሕር በመሻገር በአስራ አራት አገራት በሚገኙ ወደ ሦስት መቶ አርባ የሚጠጉ መንደሮችና ሥፍራዎች ያዳረሰ ነበር። አገራቱ ከኢትዮጵያ በስተቀር የፈረንሳይ ቀኝ ግዛት የነበሩ ናቸው።ሦስት ሺህ አምስት መቶ ዕቃዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ማስታወሻዎች፣ ማውጫዎች፣ መጻሕፍት፣ ፎቶዎች፣ ደርቀው የታሸጉ እንስሳትና ቅጠላ ቅጠሎች በተለያየ ጊዚያት በጀልባ ወደ ፈረንሳይ እንዲላኩ ይደረግ ነበር።ከቡድኑ አባላት መካከል ኤትኖሎጂስቶች፣ ፎቶ ግራፍ አንሽዎች፣ የፊልም ቀራጮች፣ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች፣ የቋንቋ ምሁራን፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ሰዓሊያን ይገኙበታል። የልዑካን ቡድኑንየዕለት ተዕሎት ውሎ መዝግቦ የማቆየት ኃላፊነት የተሠጠው ጸሐፊው ሚሼል ሌሪስ (1901-1990) ነበር።በ1934 ያሳተመው L’Afrique fantôme የተባለው መጽሐፉ በወቅቱ የተፈፀመውን አጠያያቂ የሆነውን ድርጊት በመፀፀት ስሜት የገለፀበት ሥራ ነበር። ይህ መጽሐፍ፤ ቡድኑ እዚህ ግባ የማይባል፣ አነስተኛ ክፍያ በመክፈል፣ አንዳንዴም በግዳጅ አሊያም በማስፈራራት ንብረቶቹ እንዴት እንደወሰደ፤ እንደ ማስረጃ ማጣቀሻ ሆኖ ያገለግላል። ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ ጽሑፎቹን፣ መዛግብቱን፣ ፎቶዎቹንና የዕደ-ጥበብ ስራዎቹን በመመርመር የተሰወረውን እውነታ መግለጥ የተደረገ ሙከራ ብዙም አልነበረም።
ለዚህ ሁኔታ መፍትሄ ለማግኘት ፓሪስ የሚገኘው ኬ ብሮንለይ ሙዚየም (Musée du quai Branly ) እነዚህ ቅርሶች እንዴት እንደተሰበሰቡ ማጥናት የጀመረው በ2021 ነው።ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮ በዘመነ ቅኝ ግዛት ከቤኒን የተዘረፉ የዕደ-ጥበብ ስራዎችን ፈረንሳይ ትመልሳለች ሲሉ ከገለፁበት ጊዜ ጀምሮ ነው።ከኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ሴኔጋልና ጅቡቲ የተውጣጡ ምሁራንና ባለሙያዎች ከሙዚየሙ ሃላፊዎች ጋር በመሆን መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይ፣ ከዚያም በኋላ ወደ አገራቸው በመመለስ የተወሰኑ ዕቃዎች እንዴት እንደወጡ ጥርት ያለ መረጃ ለማግኘት ተሳትፈዋል።ከኢትዮጵያ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር፣ ሲሳይ ሳህሌ በየነ በፕሮጀክቱ ከተሳተፉት መካከል አንዱ ናቸው።
የዳካር ጂቡቲ የተልዕኮ ቡድን ሀሳብ ጠንሳሽ ማርሴል ግሪዩል ከ1928 እስከ 1929 ባሉት ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት 16 በግእዝ የተጻፉ ጥንታውያን የብራና መዛግብት ይዞ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችን የሚያካልል ተመሳሳይ ጉዞ እንዲደረግ በፓሪስ ለሚገኘው ትሮካዴሮ ሙዚየም ሐሳብ ያቀረበው ከዚህ በኋላ ነበር ።
ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ፤ አገሪቷ በቀዳማዊ ሀይለሥላሴ የቀድሞ ስማቸው ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን ትተዳደር ነበር።ንጉሠ ነገሥት ተብለው ዘውድ ከጫኑበት ከሁለት ዓመት በኋላ።ከዳግማዊ ምኒልክ ሞት በኋላ በደጃዝማች ተፈሪን እና የአጤ ምኒልክ አልጋ ወራሽ በነበሩት በልጅ እያሱ መሀል ሃይለኛ የስልጣን ትግል ይካሄድ ነበር ። የዳካር ጂቡቲ የተልዕኮ ቡድን በልጅ እያሱ ድጋፍ በሚተዳደር አካባቢ ለመንቀሳቀስ አቅዶ የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር ለአንድ ወር ለመቆየት ተገዷል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ ቡድኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥሞት ነበር።
ቡድኑን ለማገዝ በአፄ ሀይለሥላሴ የተመደቡትና ቡድንን በትርጉም ሥራ እጅጉን ያገዙት ሰው አባ ጄሮም ገብረ ሙሴ ይባላሉ። የተለያዩ ፎቶዎቻቸውና የሕይወት ታሪካቸው በኤግዚቢሽኑ ውስጥ ይታያል። በአጭር የተጻፈው ታሪካቸው እንደሚያሳየው ፤ የተወለዱት በኤርትራ ነው። ከካቶሊክ ቤተሰብ የተወለዱት አባ ጄሮም በፈረንሳይ ላዛሪስት ትምህርት ቤትና ጣልያን ካፑሲን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።በ1918 ዓ.ም እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለዘውዳዊው መንግሥት መስራት ጀመሩ። ለሚሼል ሌሪስ ቃለ ምልልሶችን ፣ መዝሙሮችንና ግጥሞችን በመተርጎም ከፍተኛ እርዳታ አበረክተውለታል።

አባ ጄሮም ገብረ ሙሴ ጥቁር ካፖርት ለብሰው ይታያሉ