ለኦቦ ቦጎሳ ቀኖ + ለአዴ ሶሬቲ መታሰቢያ ይሁን +
ወንዙን ተሻግሮ ጉብታው ላይ ባለ ሣር ክዳን ቤት፤ ከአጠገቡ የተራበ ሕጻን ሆድ የምታክል ያጋደለች የእህል ጎተራ፤ ፈንጠር ብሎ ማማ፣ ማማው ላይ ከወጣህ የበቆሎ ማሣ ከዳር ዳር እንደ እጅህ መዳፍ ወለል ብሎ ይታይሃል፤
በቆሎ አዘርዝሯል፣ ዱባ በሆዱ ተስቦ ተሳስቦ ጡት እንደ ተጋተ እምቦሳ መሬቱን ነክሶታል፤ ጎመን ከእንቅልፍ ባንኖ እንደ ተነሳ ጎልማሳ ተንጠራርቶ ቆሟል፤
ምነው እግዚአብሔር ዝናቡን አንዴ በለቀቀው፣ ከተቋረጠ ወር አለፈ…
ጋዲስ ከጧት ጀምሮ ሰማይ ሰማዩን ሲያይ፣ የደመናውን አኳኋን ሲያጠና ማማው ላይ ዋለ፤ … በስተ ሰሜን ምሥራቅ አጨልሞ ያየሩ ሽታ ለውጧል…
ጋዲስ ማማው ላይ እንደ ቆመ ዝግ ባለ ድምጽ “እናንተ ስጡን አስገቡ፣ እንስራ ደቅኑ” አለ በእርግጠኛነት፤
“እርሱ ይርዳና” አለች፣ ሴትዮ …
እቤት ገብቶ ያቀረበችለትን በልቶ ሳይጨርስ ሰማዩ ፈነዳ፤ … ለዛሬ ያ መከረኛ ሆድ ሞልቷል፤ ለነገ ተስፋ ከደጅ ያንኳኳል፤
ያላመጠውን ሳይውጥ ነፋስ ቀላቀለ፤ … የሰማዩን ጉሮሮ አንቆ ዝናቡን አቀጠነው፣ ቀስፎ ይዞት እልም አለ፤ ጋዲስ ጆሮውን ማመን ቢያቅተው ሮጦ ደጅ ወጣ፤ የውሃ ሽታና ነፋስ ብቻ ቀርቷል፤ ለእርድ እንደ ተቃረበ ወይፈን፣ በረጅሙ አቃሰተ፣ “ምነው እንዲህ አረግኸኝ፣ ምነው ምን በደልኩህ? ሰጥተህስ እንዴት ትነሳለህ?” አለ፤
“ተው፣ ተው አታማርር፣ ሌላ ነገር እንዳታመጣ” አለች፣ ሴትዮ፤ የራሷን ጭንቀት በሆዷ ቋጥራ፤ “በረሃብ ማለቃችን ነው እኮ” አለ … ቆይቶ፣
“እርሱ ያውቃል፣”
“እውነትሽን ነው፣ እርሱ ያውቃል፣” ለራሱ እንደሚያወራ፣ ደንግጦ ከቆመበት ሳይነቃነቅ፣ ጋዲስ ያን ሌሊት ሥጋትና ፍርሓት ተጋግዘው ተስፋውን ሲገዘግዙት አደረ፤ ፈጣሪ ያመጣውን ለማን አቤት ይባላል? … በአሳብ ብዛት ንጋት መልሶ አሸለበው፤
አንድ ሕልም አየ… ከባድ እንቅልፍ ወስዶት ይመስለዋል፣ በስመ አብ የሚያሰኝ ዶፍ፣ ከቤቱ በታች ያለው ወንዝ ሞልቶ ማሣውን ሲያጥለቀልቅ፣ ጎርፎ ቤትና ጎተራውን ሲያፈራርስ ባንኖ ነቃ፤ አኳኋኑ አስደንግጧት፣ “ምነው ምነው ምን ሆንክ?” አለች ከጎኑ፣
እያዛጋ፣ እየተንጠራራ፣ ዐይኑን እያሻሸ ሕልሙን ይነግራት ጀመር፤
“እንዳፈቀደ ያርገን” አለች እየደጋገመች…
ጋዲስ ሰላሣ ዓመት ሮበዩ ሲኖር እግዚአብሔር አንዴም አስቀይሞት አያውቅም፤ ይህንኑ ማሰብ ጀመረ፣ … እስካሁን ያኖረኝ እርሱ አይደለ? ይህን ያህል ዘመን ከእጁ መልካምን ተቀብዬ የለ?
… እንዲህ የሚመስል ብዙ ብዙ አውጥቶ አወረደ፤
ለምን ደብዳቤ አልጽፍም? አለ …
ይቅርታ ቅድም ሳልነግርህ ረስቼ፣ ጋዲስ ገበሬም ቢሆን በመሠረተ ትምህርት ሁለት ዙር ዘመቻ ማንበብና መፃፍ ተምሯል፤ ሆኖም ቀለም ሲበዛ ሥራ ፈት ያደርጋል ብሎ ሌላውን ዙር አልተማረም… የሚቀጥለው ቀን እሑድ ነበረ፤ ቁጭ ብሎ በቆሎ በሚያካክሉ ፊደሎች ደብዳቤ መፃፍ ጀመረ፤

ወረቀቱን አጣጥፎ በፖስታ ካደረገ በኋላ እኪሱ ከትቶ ወደ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን አመራ፤ ፀሐፊዋ ለምሳ ስትወጣ ከደጅ የታሸገ ፖስታ ታገኝና አንስታ ለመጋቢው፣ መጋቢ የጸሎት ጥያቄ መስሎት እንደ ታሸገ ለጸሎት ጓድ መሪ፣ የጸሎት ጓድ መሪ የገንዘብ እርዳታ ጥያቄ መሆኑን ሲያውቅ መልሶ ለመጋቢው፤ መጋቢ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ይዞ ቀረበ፤ ደብዳቤው፣ ያልተለመደ ስለሆነ ለመሣቅም ለመተውም ቸገረ፤ ቤተ ክርስቲያን ችግረኞቿ ብዙ ናቸው፤ ለስንቱ ይህን ማድረግ ይቻልና ነው? ተባባሉ፤ የደብዳቤው አፃፃፍ ቀጥተኛነትና የፀሐፊው እምነት በቀላሉ የሚታለፍ አልሆነም፤ ለማንኛውም ሁለት ሰዎች ጉዳዩን አጥንተው እንዲያቀርቡ ተወሰነ፤ ብቻ ምን ቸገረህ፣ ወዲያ ወዲህ ሲባል ሣምንታት አለፉ፤ ጋዲስ ሰልችቶ ተስፋ አለመቁረጡ! ይኸውላችሁ፣ ገበሬ መሆን ለዚህ ለዚህ ጊዜ ይጠቅማል፤ ሌላ ቀን ተመልሶ ሲመጣ አትክልተኛው ከወዲያ ይጣራል፣
“ጋዲስ አንተ ነህ? …
“አዎ!”
“ፖስታ አለህ!”
ፖስታውን ተቀብሎ ትንሽ ራቅ ካለ በኋላ ሲከፍተው፣ “ከግዛቤር” የምትል ወረቀትና ብር ያገኛል፤ብሩን ቆጠረ፤ … ደግሞ ቆጠረ… ገልመጥ ብሎ ሰው አለመኖሩን አይቶ እንደ ገና ቆጠረ፤ ጥግ ቁጭ ብሎ ደብዳቤ መፃፍ ጀመረ…

አሁን የሚያስፈልገው © ምትኩ አዲሱ (የመጀመሪያ እትም 2008 ዓም፤ 2ኛ እትም 2011 ዓም)፣ ገጽ 63-67