ምክርና ጥቆማ ለፌደራል ፖሊስ፤ የጅምላ ፍተሻ ሕዝብን ማሸበር ነው፤

ምክርና ጥቆማ ለፌደራል ፖሊስ፤ የጅምላ ፍተሻ ሕዝብን ማሸበር ነው፤

በትላንትናው የመንግስት ዜና እወጃ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ማህበራዊ ድህረ-ገጾችን በመጠቀም ለአመጽ ቅስቀሳ የሚያደርኩ አካላትን አድኖ ለመያዝ የተጠናከረ የጅምላ ፍተሻና የእጅ ስልክ ብርበራ እንደሚያደርግ ዛቻና ማስፈራሪያዎች የተቀላቀለበት መግለጫ ሰጥቷል።

በመጀመሪያ ይህ ዜጎችን በየመንገዱ ድንገት አስገድዶ በማቆም ስልካቸውንም ሆነ እራሳቸውን የመበርበር እርምጃ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች የሚጥስና ሽብርን የሚነዛ ሕገ ወጥ እርምጃ ነው። የከፋ ችግር ሲኖርና ለአጭር ጊዜ ብቻ ተመጣጣኝ የሆነ ብርበራ ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ ሊካሄድ ይችላል። ነገር ግን ፖሊስ በአዋጅ ከነገ ጀምሮ የሁሉንም ሰው ስልክ በየመንገዱ እበረብራለሁ ብሎ እንዲያውጅና በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች እንዲጥስ የሚፈቅድ አሠራር ግን በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም። መንግስት አመጽ ለመቀስቀስ አስበዋል ብሎ የጠረጠራቸው አካላት ወይም ግለሰቦች እንኳ ካሉ የመበርበሪያ የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥቶ ሥራውን በጥንቃቄ ይሰራል እንጂ በጅምላ የዜጎችን ነጻነት በዚህ መልክ በማጥበብና በመግፈፍ ሕገ መንግስታዊ ጥሰት ሊፈጽም አይገባም።

ነገርየው ከመንግስታዊ ፍርሃት የመነጨ ሕዝብን የማሸበሪያና የማስጨነቂያ፤ እንዲሁም በህብረተሰቡ ውስጥ ፍርሃትን የማስረጽ ስልት እንደሆነ ማሳያው ከአገር ውጪ ሆነው መረጃ የሚያሰራጩትንም አንምርም የምትለው ሐረግ ነች።

ለማንኛውም የኔ ምክር ፌደራል ፖሊስ የዜጎችን መረጃ የመለዋወጥ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና ያለ በቂ ምክንያት ያለመጠርጠርና ያለመፈተሽ መብትን በመጣስ ሊፈጽም ያሰበውን ሕገ ወጥ ተግባር ከወዲሁ እንዲገታና በእርግጥም አመጽ ለመቀስቀስ የተዘጋጁ አካላት መኖራቸውን የደረሰባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ካሉ ሕጋዊ ሥርአትን በተከተለ መልኩ እና በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ በተጠረጠሩት ላይ ብቻ በማተኮር አደጋውን እንዲከላከል ነው። ለዛ ደግሞ የፖሊስ የዕለት ተዕለት ሥራ ስለሆነ እወጃ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ አያስፈልገውም።

ይልቅስ ለፖሊስ የምሰጠው ጥቆማ ደግሞ አዎ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አመጽ እና ከፍ ያለ ሕዝባዊ ቁጣ ሊቀሰቀስ የሚችልበት ሰፊ እድል አለ። ይህ እንዲሆን የሚከተሉትን ሕዝብን ለአመጽና ለቁጣ የሚቀሰቅሱ ተከታታይ እርምጃዎችን የታቀደ በሚመስል መልኩ በየቀኑ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ፤ ምንም እንኳ ሕዝቡ አልሰማና አላምጽ ቢለውም፤ አመጽ እንዲጠነሰስ፣ አመጽ እንዲቀሰቀስና አገሪቱ ወደለየለት ቀውስና ብጥብጥ እንድታመራ ሌት ተቀን በጀትና የሰው ሃይል መድቦ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እየሰራ ያለ አካል አለ። እሱም ያው አገሪቱን የሚያስተዳድረው ራሱ የብልጽግና መንግስት ነው። ለጥቆማ ያህል፤

– መቶ ሺዎችን በከተማ ግንባታና በኮሪዶር ልማት ስም ቤታቸውን አፍርሶ፣ ንብረታቸውን ሜዳ ላይ በትኖ፣ ከቀያቸውም አፈናቅሎ መንደራቸውን ለከበርቴና ለውጪ ዜጎች በመቸብቸብ ሕዝብን ለአመጽ የቀሰቀሰ፣

– በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ካሉ ታጣቂዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ገብቶ ሚሊዬኖች እንዲፈናቀሉ፣ በመቶ ሺዎች እንዲሞቱ፣ በአስር ሺ የሚቆጠሩ ሴቶችና ሕጻናት እንዲደፈሩ፣ የሕዝብና የአገር ሀብት እንዲወድም ዋነኛ ምክንያት በመሆን ሰላም ፈላጊውን ሕዝብ ለአመጽ የቀሰቀሰ፣

– ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳይመለሱ በማድረግና በተበላሸ የትምርት ሥርዓት ሚሊዮን ወጣቶች ሥራ አጥ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የሥራ ዋስትና በማሳጣት ወጣቱን ለአመጽ የገፋፋና ያነሳሳ፣

– በየቀኑ በሚንረው የኑሮ ውድነት ሳቢያ ልጆቹን በቀን አንዴ ማብላት የተሳነው የመንግስት ሰራተኛ እርሃቡን ለማስታገስና ቤተሰቡን ለመቀለብ ፌስታል ይዞ በየሆቴሉ ትርፍራፊ እንዲለምን በማድረግ፤ ያም አልበቃ ብሎት ተመጣጣኝ ያልሆነ የገቢ ግብር ከሠራተኛው ደሞዝ ላይ እንዲጎመድ የሚያደርግ አዋጅ ያጸደቀና በፖርላማ ጭምር ቢለመን አሻፈረኝ በማለት ሠራተኛውን ለአመጽና ለአድማ የገፋፋና ያነሳሳ፣

– ወጣቱን በየምክንያቱ በጅምላ እያፈሰ በየማጎሪያ ውስጥ ያለምንም የፍትህ ሂደት አሥሮ በማሰቃየት በአገሩ ላይ እንዲያቄም፣ አገሩን እንዲጠላ፣ ጫካ ገብቶ ነፍጥ እንዲይዝና ገሚሱም በባህርም እንዲሰደድም ምክንያተት በመሆን መጣቱን ለወንጀልና ለአመጽ የገፋፋና ያበረታታ፣

– ነጋዴውን በየምክንያቱ ለመንግስት ድግስና የልማት ማስኬጃ ገንዘብ አምጣ እያለ ከማማረር አልፎ ተመጣጣኝ ያልሆኑና አንዳንዴም ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው የግብር አይነቶችን በመጫን ያማረረና ብዙዎች የንግድ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ጭምር ምክንያት በመሆን ነጋዴውን ለአመጽና ለአድማ ያነሳሳና የገፋፋ፣

– የፖለቲካ ፖርቲዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የመብት አቀንቃኞችን እያዋከበ፣ እያሰረ፣ እያሳደደ፣ ከአገር እንዲሸሹ እየያደረገና ሲከፋም እንደ አቶ በቴ በጥይት ደብድቦ እየደፋ ለአመጽ እንዲነሳሱ፣ ከሰላማዊ ትግል ይልቅ ነፍጥን እንዲመርጡ ያላሰለሰ ጥረትና እርምጃ እየወሰደ ያለ፣

– ዜጎች በነጻነት ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱና በሰላም ወጥቶ መግባት ከባድ እስኪሆን ድረስ የደህንነት ስጋት እንዲገጥማቸውና የሕግ የበላይነትን የማስፈን ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አቅቶት በአገሪቱ የደቦ ፍርድና ጭካኔ የተሞላው የግፍ እርምጃ እንዲስፋፋ በማድረግ ሕዝብ የመንግስት ያለህ ብለሰ እንዲያምጽና አደባባይ ወጥቶ ፍትህ እንዲጠይቅ ተግቶ እያነሳሳ ያለ፣

ሌሎችም ሕዝብን ለአመጽ የሚዳርጉ እጅግ በርካታ የግፍና ሕገ ወጥ እርምጃዎችን በተከታታይ እየወሰደ አገሪቱ ምድራዊ ሲኦል እንድትመስልና ወደ ከፋ ግጭትና ነውጥ እንድትገባ ያደረገው የብልጽግና አስተዳደር ሆኖ ሳለ የፌደራል ፖሊስ ይሄ ሁሉ ውርጅብኝ ለአመታት ሲወርድበት በዝምታ እያስተናገደ አላምጽም፣ አላድምም፣ ደግ ቀን እስኪመጣ እጸልያለሁ እያለ ወደፈጣሪው የሚያለቅስን ሕዝብ በአመጽ በመጠርጠር የእጅ ስልክህ ውስጥ የተደበቁ አመጽ ቀስቃሾችን ለመፈለግ ብርበራ አደርጋለሁ የሚል የማስፈራሪያ ዜና እወጃ ይዞ አደባባይ ብቅ ማለቱ ምነዋ? ይህ የፖሊስ ዛቻና ሽብር መንግስት አሁንም አገሪቱ ከገባችበት አደገኛ ሁኔታ እና አዘቅት ለመታደግ ዝግጁ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን ብቃቱም እንደሌለው፣ ብልሃቱም እንደጠፋው ማሳያ ይመስለኛል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አመጸኛ ቢሆን ኖሮ ብልጽግና ታሪክ ሆኖ የሚያልፍበት ዘመን ቢያንስ ወደኋላ በሦስትና አራት አመት ይመለስ ነበር።

‘ሕዝብ እና እምቢተኝነት’ በሚለው ቀጣይ ጽሁፌ ‘ሕዝባዊ እምቢተኝነት’ ወይም civil disobedience ከሰብአዊ መብቶች አንዱ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ምን መልክ እንዳለው በሰፊው እመለስበታለሁ።

እስከዛው ፌደራል ፖሊስ ሕዝብን ለቀቅ አድርጎ አለቆቹን ጠበቅ እንዲያደርግ እመክራለሁ።

ቸር እንሰንብተት

Share this post

One thought on “ምክርና ጥቆማ ለፌደራል ፖሊስ፤ የጅምላ ፍተሻ ሕዝብን ማሸበር ነው፤

  1. አይ ያሬዶ፣
    ውጭ አገር መኖርህ ብዙ ነገር አስረስቶሃል ማለት ነው። ዐቢይ ቢያስር፣ ተኩሶ ቢገድል፣ ዜጋ በቁሙ ሞቷል ትንፍሽ አይልም። ዜጋ የቸገረው ውሃ እህል መብራት ህክምና ነው። ዜጋ ተረስቷል፤ ፖሊስ አስቁሞ ቢፈትሸው፣ እግዜር ሲያድለኝ አስታዋሽ አገኘሁ እንዲል ተደርጓል። የሰላማዊ ሠልፉን ነገር ተወው፤ አለህበት አገር ብታደርገው ይሻልሃል።

Comments are closed.