የጠቅላይ ሚኒስትሩን የዛሬ የፓርላማ ንግግርን ጊዜ ወስጄ፣ አንዳንዱንም እርግጠኛ ለመሆን ደግሜ ሰማሁት፡፡ ጠቅለል ሲደረግ ‘የለየልኝ አምባገነን መሆኔን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ጎረቤት አገሮችና የቀረው አለም ይወቅልኝ’ የሚል እንድምታ ያለው የጸብ እወጃ የጀመረ ንግግር ነው፡፡ ጠቅላዩ ሦስቱንም የአንባገነን ሥርአቶች ባህሪያት፤ (benevolent, military and elective dictatorship) ብልጽግና ተኮር፣ ወታደራዊ ኃይልን እና ምርጫን ያማከለ አንባገነን መሆናቸውን በይፋ ሊያውጁ የወጡበት መድረክ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
በዝርዝር ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ደግሞ፤ ተሽመድምዶ አደጋ ላይ የወደቀውን አገሪቱን ኢኮኖሚ እና አንገቷ ድረስ በእዳ የተዋጠችውን አገር እሳቸው ተአምራዊ የኢኮኖሚ ግስጋሴ ላይ እንዳለች ለማስመሰልና እሱንም ካላመናችሁኝ የሚል እንድምታ ያለው በተሳሳቱ መረጃዎችና አሃዞች የታጨቀና ከተጨባጩ እውነታ የሚርቁ የስኬት ማሳያዎች፣ ማስከበር የተሳናቸውን የሕግ የበላይነትና የአገሪቱን ሰላም ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል የሄዱበት መንገድ፣ ነገሮች ከቁጥጥራቸው ውጪ እንዳልወጡና የአገሪቱን ሁለት ትልልቅ ክልሎች በስፋት የመንቀሳቀሻ ሜዳቸው ያደረጉትን ተፋላሚዎቻቸውንም አኮስሰው የመንደር ሽፍቶች ለማስመሰል የሄዱበት እርቀት፣ ከአሰብ ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲገባቸው ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን ለማሸማቀቅና ስለ ሰላም በማውራታቸው ብቻ የኤርትራ መልዕክተኛ እንደሆኑ አድርገው መግለጻቸው እና የወደብ ጥያቄንም በተመለከተ የሰጡት ፍጽም ግልብ፣ ጸብ አጫሪ የሆነ የጦርነት ጥሪ ወይም እወጃ የሚመስል ንግግራቸው፣ አለምና መላው አፍርካ ያደነቀውን ልማት የኢትዮጵያ ሕዝብ አልታይ ብሎታል በሚል ሕዝብን የመረዳት አቅም የሌለው በማስመሰል የዘለፉበት መንገድ፣ መጪውን ምርጫ አስመልክቶም የሰነዘሩዋቸው ሃሳቦችና ተቃዋሚዎችን ለማዋረድ የሰነዘሯቸው ቃላቶች፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ተልዕኮም በማስመልከት የሰጡት የተምታታ አስተያየት፤ በአጠቃላይ የጠቅላዩ ድንፋታ፣ ስድብ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ አዘል ንግግራቸው በአንድ በኩል ጥልቅ ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን እና በሌላ በኩል ደግሞ ከፍርሃት የመነጨ የፈሪ ብትራቸውን በማንም ላይ ለመጠቀም በቋፍ መሆናቸውን እንድታዘብ አድርጎኛል፡፡
የሆነው ሆኖ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎችን ከኤርትራ ጋር በማበር የባንዳነት ተግባር ፈጽመዋል የሚለው የጠቅላዩ ክስ የሌባ አይነደረቅ አይነት አይሆንም ወይ? ማነው ከኢሳያስ ጋር አብሮ፣ የሻቢያን ጦር ጋብዞ ትግራይን ያስወረረ? ማነው የራሱን አገር ትግራይን አይኑ እያየ በሻቩታ ያዘረፈ? ማን ነው የትግራይ ሴቶችንና ሕጻናት ሳይቀሩ በጥላቻና በበቀል በተሞላ የኤርትራ ወታደሮች ዘኛኝ በሆነ መንገድ ያስደፈረ? ማን ነው የዛሬ ሦስት አመት የትግራይ ሴቶች በሻቢያ ወታደር መደፈራቸውን አስመልክቶ ሲጠየቅ በፓርላማ ውስጥ የማይገባ ንጽጽር አቅርቦ ያላገጠ? ማን ነው ኢሳያስን ጋብዞ ድንበር አቋርጦ ከነሰራዊቱ አገር እንዲወርና ያሻውን እንዲያደርግ የፈቀደለት? ማነው ውሉ በማይታወቅ ግንኙነት የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት በሻቢያ እንዲደፈር ያደረገ? ሌሎቹ ተቃዋሚዎች ከኤርትራ ጋር ወግናችኋል ተብለው የባንዳነት ማዕረግ ከተሰጣቸው ቀለበታቸውን አውልቀው ለኢሳያስ ያጠለቁት፣ ጃኖ ያለበሱት እሳቸው ምን ሊባሉ ይሆን? በኢትዮጵያ የ40 እና 50 አመት ታሪክ ውስጥ ከሻቢያ ጋር በማበር ኢትዮጵያ ላይ እጅግ አስከፊ ወንጀል የፈጸሙት አንዱ ሟቹ ተቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲሆኑ ቀጣዩ ተሰላፊ ደግሞ የዛሬው ጠቅላይ ናቸው፡፡ መለስ ሆን ብለው አገሪቱ ወደብ አልባ በማድረግ ለመከራ የዳረጓት ሲሆን አብይ ደግሞ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ወንጀሎች ከሻቢያ ጋር ተባብረው ፈጽመዋል፡፡
ለማንኛውም የፓርላማው ውሎ ባጭሩ የአገሪቱ ፈላጭ ቆራጭ፣ ከሕገ መንግስት በላይ እና በ130 ሚሊዮን ሕዝብ እጣ ፈንታ ላይ ያሻውን የሚወስነው አንድ ሰው፤ እሱም አብይ አህመድ መሆኑን ማሳያ ሆኖ አልቋል፡፡