ኒውዮርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙስሊም ከንቲባ መረጠች

ኒውዮርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙስሊም ከንቲባ መረጠች
  • በትራምፕ ዘመን በተደረገ የመጀመሪያ ምርጫ ዴሞክራቶች ድልን ተጐናፀፋ 

ኒውዮርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙስሊም ከንቲባ መረጠች።የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል የሆነውና እንደ በርኒ ሳንደርስ ተራማጅ የማህበራዊ ፍትህን የሚራምደው፥ ዞህራን ማምዳኒ፥ የአሜሪካዋ ትልቋ ከተማ ከንቲባ ሆኖ ተመርጧል።ታሪካዊ ነው በተባለለት በዚህ ምርጫ ከቱጃሮች ድጋፍ የተቸራቸውና የኒውዮርክ ግዛት አገረ ገዢ የነበሩት አንድሪው ኩሞን በግላቸው ሲሳተፉ የ71 ዓመቱ ዕጩ ከርቲስ ሰሊዋ፤ ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ተወዳድረዋል።ማምዳኒ በኒውዮርክ የከንቲባ ታሪክ በእድሜ ትንሹ ተመራጭ በመሆንም ታሪክ ሠርቷል።የዲሞክራቲክ ፓርቲና የአሜሪካ ፖለቲካ አዲስ ፊት ማሳያ ሆኖ እየቀረበ ነው።

አባትና እናቱ የሕንድ ዝርያ ያላቸው ማምዳኒ የተወለደው በካምፓላ፣ ኡጋንዳ ሲሆን በሰባት ዓመቱ ወደ ኒው ዮርክ በመምጣት እዚያው እንዳደገ የህይወት ታሪኩ ይገልፃል።ቦውድዮን በተባለው የግል ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና እና ኢኮኖሚክስ ሙያ ተምሯል። 

ኩዊንስ (Queens)ን በመወከል የተወዳደረው ማምዳኒ በ2016 የበርኒ ሳንደርስ የምረጡኝ ዘመቻ ላይ በማስተባበር ተሳትፏል።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለዘብ ያለ አቋም ካላቸው( centrist) ከሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች መራራቅ ጀመረ።የታችኛውን መደብ ያማከለ ሃብት ክፍፍል፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ማስፋፋትና ድሀ እና ተጋላጭ ዜጎችን መደገፍ የሚሉ ተራማጅ ፖሊሲዎችን ማራመድ ጀመረ። ሁሉም  የአውቶቡስ አገልግሎት ነጻ እንዲሆን፣አከራዮች የቤት ኪራይ እንዳይጨምሩ ገደብ ማስቀመጥ፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ቤቶችን መገንባት፣ ከተማዋ የምትቆጣጠራቸው የገበያ መደብሮችን ማስፋፋት፣ የሸቀጥ ፍጆታዎችን አነስ ባሉ ዋጋ ማቅረብ፣ ነጻ የልጆች እንክብካቤን ማስፋፋት ለመፈፀም ቃል የገባቸው አጀንዳዎቹ ናቸው። እነዚህን ሁሉ ተግባራት ለመፈፀም የሚያስፈልጉ ወጭዋች፤ በሀብታምች ላይ ግብርን በመጨመር መሠብሠብ አለበት ብሎ ያምናል።ይህ ሃሳብ በነጋዴዎችና በቢዝነስ ሰዎች ዘንድ አልተወደደም።በንግዱ ዓለም ላይ የሚያተኩረውና ከፍተኛ ተነባቢነት ያለው ዋል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ በተደጋጋሚ ይተቸው ነበር።

ዞህራን ማምዳኒ፥ በፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሰውን ግፍ በይፋ ይተቻል። እስራኤል ጋዛ ላይ “የዘር ማጥፋት ወንጀል” እንደፈጸመች ቀድመው ከተናገሩት አንዱ ነበር። ይህ አቋም ፥ በጣም ከፍተኛ የጂዊሽ (Jewish) ማህበረሰብ በሚገኝባት ኒውዮርክ በጥሩ አይታይም።ግን ተራማጅ ከሆኑ የግራ ዘመም ጂዊሽ ወጣቶች፣ ቡድኖች፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች- እንደ Jewish Voice for Peace፣ ድጋፍ አግኝቷል።

ሁለቴ በኒውዮርክ ግዛት ጉባኤ ላይ ተመርጦ አገልግሏል።እንደ በርኒ ሳነደርስ ሁሉ፥ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች የታችኛውን መደብ ችላ በማለታቸው ነው ባለፈው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ  የተሸነፉት ብሎ ያምናል።

የካፒታሊዝም ሥርዐት ቤተመቅደስ ተደርጋ በምትወሰደውና 8 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት ከተማ ፥ ሙስሊምና የስደተኛ ልጅ በከንቲባነት ከተማውን እንዲያስተዳድር መመረጡ ልዩ አንደምታ አለው።ይህን ድል ድርብ የሚያደርገው በርካታ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች ሳይደግፉት የተገኘ መሆኑ ነው።የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ፣ የቬርሞንት ሴናተር በርኒ ሳንደርስ፣ የኒውዮርክ 14ኛ ኮንግረስ ዲስትሪክት ተወካይ አሌክሳንድሪያ ኦካሲዮ ኮርትዝ ቢደግፋትም፥ ሌሎች ዲሞክራቶች ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም።የኒዋርክ ግዛትን በመወከል ሴኔት ላይ የሚገኙት ሿክ ሹመር በጭራሽ ማምዳኒን አልደግፋም ካሉት አንዱ ናቸው።እነዚህ አመራሮች ማምዳኒንን መደገፍ ያልፈለጒበት ምክንያት የሚራምዳቸው አቋምቹ ከተወሰነው ደጋፊችን ጋር ያጣላናል በሚል ነው። በተለይ የነፃ ገበያ አቀንቃኝ ከሆኑትና የዴሞክራቲክ ፓርቲን በገንዘብ ከሚደግፋ አካላት። ማምዳኒ አሜሪካን ሀገር ባለ መወለዱ ለፕሬዝድነት ምርጫ መቅረብ አይችልም። በዴሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ይችላል። እንደ ኒውዩርክ በኑሮ ውድነት በሚታመሡ ሌሎች ከተሞች፥ ማምዳኒ ያቀረባቸው መፍትሔዎች፣ እኛም ጋር መተግበር አለባቸው በሚል፥ መራጮች የዲሞክራቲክ ፓርቲን አቅጣጫ ሊያስቀይሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለ።

በኩዊንስ ተወልደው ያደጕት ዶናልድ ትራምፕ ለማምዳኒ ያላቸውን ጥላቻ መግለፅ ከጀመሩ ከራርመዋል።የነጮችን የበላይነት በሚያቀነቅኑ አካላት የሚደገፋት ትራምፕ ስደተኛና ሙስሊም ፓለቲከኛን የጥቃት ኢላማ ማድረጋቸው የሚጠበቅ ነው።”ኮሚኒስት” በማለት የፈረጁት ሲሆን ለኒውዮርክ የሚላከውን የፌደራል መንግስት በጀት እንደሚይስቆሙት ገልፀዋል። ከማምዳኒ የተሻለ ነው በሚል ለአንድሪው ኩሞ ያላቸውን ድጋፋ ገልፀዋል። አንድሪው ኩሞ በበርካታ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እና ትንኮሳ በመፈፀም ተከሰው ነበር፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ በሌሎች ቦታዎች በተከናወኑ ምርጫዎች ዴሞክራቶች ማሸነፋቸው ተገልጧል ።በቨርጂኒያ ለመጀመርያ ጊዜ ሴት ሀገረገዢ ተመርጣለች። አቢጌል ስፓንበርገር።የፓርቲው ለዘብተኛ ክንፍ አቋምን በማንፀባረቅ የተወዳደረችው አቢጌል በግዛቱ ስለተንሰራፋው የኑሮ ውድነትና በትራምፕ አስተዳደር ከሥራ ስለተባረሩት የፌደራል መንግስት ሠራተኞች በማውሳት ነው የብዙ መራጮችን ድጋፍ ያገኘችው። ሚኪ ሼርየል የኒውጀርሲ ሁለተኛ ሴት ሀገረገዢ ሆናለች። ሚኪ ሼርየልም ለኑሮ ውድነት መፍትሄ ለመሻት ቃል በመግባት የተሰካ የምረጡኝ ዘመቻ አደረገች።

የዚህ ሳምንት ውጤት አጉልቶ ያሳየው ነገር በዲምክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የቆየው ልዩነትና አለመግባባት አለመፈታቱን ነው።ፓርቲው የበለጠ ወደ ግራ ያዘመመ ተራማጅ አጀንዳ ወይስ የገበያውን ዓለም የማያስከፋ መካከለኛ መንገድ መከተል አለበት የሚለው አስተሳሰብ አባላቶቹን እያጨቃጨቃቸው ነው። የትኛው ወገን እያየለ የፓለቲካ መድረኩን ይቆጣጠረዋል የሚለው በጊዜ የሚታይ ይሆናል።

Share this post

3 thoughts on “ኒውዮርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙስሊም ከንቲባ መረጠች

  1. Kedir Hussen Mohammed · Edit

    ኒውዮርክ የመጀመሪያውን የሙስሊም ከንቲባ አገኘች እያሉ ድቤ የሚደልቁ ምእመናን እያስተዋልን ነው:: ይህ እኮ ሙስሊሞች ምን ያህል አቅመ ቢስ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው:: እንደ ሙስሊም ሙስሊምን የሚያሳድድ አለ እንዴ? እዚሁ ኢትዮጵያ መሥሪያ ቤት ውስጥ ሙስሊም ሆነህ ባለጉዳይ ሆነህ ጉዳይህ ሙስሊም ከያዘው you’re done. ኢንፊሪየሪቲ ጫና የተጠናወተው ሰው ባይሾም ይሻላል:: ኦባማ ሲመረጥ በአያቱ ሙስሊም ነው, በአክስቱ, በአባቱ ተባለ:: እንደ ኦባማ ዘመን ሙስሊሞች የተጨፈ^ጨፉበት የለም:: እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠሚው አባቱ ሙስሊም ናቸው, ውስጡ ሙስሊም ነው ተብሎ ከታላላቅ ነቢያት በላይ ነው ሁላ ያለ ረዳት ፕሮፌሰርም አለ:: ሙስሊሞች በተለይም ሙፍቲዮችና ኢማሞች እንደዚህ ዘመን የተረገጡበት አለ እንዴ?
    ወንድሜ ሰው ሁን:: ሰውነት ከሁሉ ይቀድማል:: ስምህ ሳይሆን ሥራህ ይመስክር:: ኃይማኖትና ብሔር ስትሸነፍ የምትሸሸግበት ቀሚስ መሆን የለበትም:: የዘመኑ ሙስሊሞች ፍትሓዊ ቢሆኑ ኖሮ ዐለሙን ሁሉ ኒውዮርክ ያደርጉት ነበር:: የተትረፈረፈ ሀብታቸው የዱ^ርዬ መጫወቻ አይሆንም ነበር:: በእስልምና አሪፍ እንደሆነ የሚሰክስ ሰው ቅዱስ ተግባሩ ንጹሓንን ማ^ረድ, ሕንጻ ማፈን^ዳት, መስጂድ ውስጥ ቦ^ምብ መቅበር, ሸይኾችና ሙፍቲዎችን ማዋረድ ከሆነ ውሎ አድሯል:: አውሬ እንኳ የሚጠየፈን ደረጃ ደርሰናል:: ትልቅ ሰው ሲሞት የማያዝን ባልጩት የሆነ ደናቁርት ስለሹመት ያወራል:: ግዴለህም ሰው ሁን:: ሰው ስትሆን ለውሻ ታዝናለህ:: ውኃ ታጠጣለህ:: ውሻ ሳይቀር ተከትሎህ ዋሻ ይገባል:: ነጃሳ የምትለው ውሻ ከዋሻም አልፎ ንጹሑ ጀነት ይገባል:: የቁርኣን ሱረቱል ካህፍን አንብብ::

    1. ከድር፣
      ተቻኲለህ ሁለት የማይመሳሰሉ እውነታዎችን ደባለቅካቸው። ማምዳኒ “የመጀመሪያው ሙስሊም” መባሉ፦ 1/ በአሜሪካ አይቻሉም የተባሉ ነገሮች እንደሚቻሉ ለመግለጽ ነው 2/ በትረምፕ ዘመን በእስልምና (በአፍሪካውያን በጥቊሮች) ላይ ትልቅ የጥላቻ ዘመቻ እየተካሄደ ስለ ሆነ፣ ሕዝብ ቢተባበር እንዲህ የነጭ ክርስቲያን የበላይነትን ቅስም መሰበር ይቻላል ነው 3/ ማምዳኒ በእምነቱ በዝርያው በችሎታው የማያፍር የማያሳፍር መሆኑ ነው ጉዳዩ 4/ እነ ትረምፕ፣ አገሩ የኛ ነው፤ ሌሎቻችሁ ልትገዙልን ይገባል፤ ከእንግዲህ እንደ እናንተ ዓይነቱን አገር ውስጥ አናስገባም፤ የማምዳኒን አስተዳደር የፌዴራል በጀት በመከልከል (አይችልም) ስም በማጥፋት በማዋከብ አዳክመዋለሁ፣ እንዳይሳካለት አደርጋለሁ ብሎ ዝቷል። የማምዳኒን እስላም መሆን ያገነኑት ትረምፕ እና ዲቃላዎቹ እንጂ ሙስሊሞች አይደሉም። ጣልያኑ፣ ሞርመኑ፣ ካቶሊኩ (ኬኔዲም ባይደንም ወዘተ ሲመረጡ ይኸው ውረፋ ተደምጧል)፤ አዲስ አይደለም።

  2. የተወዳደረው በሙስሊምነቱ አይደለም አልያም ውክልናው ለሙስሊሙ አይደለም። በሙስሊምነቶ ሳይሆን የኒዎ ሊበራል አስተሳሰብን ድባቅ በመምታቱ ነው።

Comments are closed.