በዛሬ ሳምንቱ የመልዕክተ ቅዳሜ ዳሰሳ የአብላጫውን ቁጥር ስለያዘውና ዝምታን ብቸኛና የተሻለ ምርጫው አድርጎ በገዛ አገሩ የዜግነትና የሰውነት ክብር ተነፍጎት የራሱን እና የልጆቹን እጣፈንታ ለጥቂት ደፋርና ውል አልቦ ልሂቃን እርግፍ አድርጎ ትቶ የታዛቢነትን፣ የተመልካችነትን፣ የተጉረምራሚና መስሎ አዳሪነትን መገለጫ ስላደረገው የአገራችን ሰፊ ሊሂቃን ነበር የጻፍኩት፡፡ በዛሬው መልዕክተ ቅዳሜ ደግሞ የትኩረት ነጥቤ በሌላኛው ጫፍ ስለቆመውና እጅግ ድምጹ የጎላው፣ በአገሩ ጉዳይ፣ በሃይማኖቱ፣ በባህሉ፣ በሌሎችም የማህበረሰብ መስተጋብሮች፣ በሚያውቀውም ሆነ በማያውቀውና በማያገባው ጉዳይ ሁሉ ሁሌም ከፊት የሚገኘው፣ ሰማይ እስኪሰነጠቅ የሚጮኽው፣ ለቅሶውም ሆነ ሳቁ በአደባባይ ስለሆነው፣ እውቀቱን፣ ልምዱን፣ ድንቁርናውን፣ ክሽፈቱን፣ ጥላቻውን፣ ፍቅሩን፣ ጥበቱን፣ ስፋቱን፣ አቃፊነቱን፣ አግላይነቱን፣ መሰሪነቱን፣ ቅንነቱን፣ ነውረኝነቱን፣ ጨዋነቱን ምንም አይነት ጾታ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ የኑሮ ደረጃም ሆነ ሌሎች የማንነት መገለጫዎች ሳይገድቡት እና ሳይሰስት ባገኘው መድረክ ሁሉ ዝርግፍ አድርጎ አውጥቶ አደባባይ ስለሚያሰጣው፣ ያሰበውን ሁሉ ሳይተነፍስ ስለማያድረው፣ በሚስጢር የዶለተውን ሳይቀር የአደባባይ ወሬ የሚያደርገው፣ እራሱን የአዋቂነት ቁንጮ አድርጎ የሚቆጥረውን ወይም ጥራዝ ነጠቅነቱን መቆጣጠር ስለሚሳነው፣ በዛው ልክ በጨዋነትም ማህበረሰቡን የማስተማር፣ መረጃ የማካፈል፣ የማንቃት እና የመምራት ግዴታ አለብኝ ብሎ ከልቡ በማመን የአደባባይ ምሁር ስለሆነው ህዳጣን ልሂቃ ያለኝን ግንዛቤ እና ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦችን የማካፍልበት ነው፡፡
በመጀመሪያ ይህ እጅግ አናሳ ቁጥር ያለው ነገር ግን በዝምታ ውስጥ የተዋጠውን የአብላጫውን ልሂቅ ውክልና በራሱ ሥልጣን የወሰደ ወይም እራሱን የሾመ (self-appointed) እና በዛው ልክ የጨፍላቂነት (tyrant) ባህሪ የተላበሰ የአገራችን ልሂቅ ማውራትም ሆነ ሃሳብኑን ለውይይት ማቅረብ አደባባይ የወጡ ብዙ ልሂቃንን ሊያስቀይምና ሊያስቆጣ እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በእዚህ ስብስብ ውስጥ እራሴንም ጨምሬ ሰለማይና ትችቶችን የማቀርበው አንባቢዎች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ እራሳችሁን ብታገኙት ነገሩን በጥሞና አስባችሁበት በማናቸውም መድረክ በሃሳብ ብትሞግቱኝ ምላሽ ለመስጠት፣ ለመከራከር እና ሃሳብ ለመለዋወጥ ዝግጁ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በጥቂት ድምጻቸው እጅግ የጎላ፣ ደፋርና የአደባባይ ልሂቃን ምርኮ ሥር መውደቁ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ከ95 በመቶ በላይ በዝምታ ውስጥ ተውጦ የትዕይንቶቹ ተመልካችና ታዛቢ የሆነው silent majority በዝምታው ያደመቃቸው፣ በዝምታው የሾማቻው፣ በዝምታው ያጠገባቸው፣ በዝምታው ያባለጋቸው፣ በዝምታው የስህተትና የክህደት ቁልቁለቱን እንዲንደረደሩ ፈቶ የለቀቃቸው፣ በዝምታው ዝናን ያፈራላቸው፣ በዝምታው ያሞሰናቸው፣ በዝምታው ነውራቸውን፣ ወንጀላቸውን፣ ድንቁርናቸውን፣ ውሸታቸውን፣ ጥላቻቸውን በአደባባይ እንዲያቀረሹ የፈቀደላቸው ጥቂት ልሂቃን ዛሬ ላይ ጥሩ ፈላጭ ቆራጭ ወይም Tyranny vocal minority ሆነውበታል፡፡
እነዚህ ድምጻቸው ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የሚሰማ ጥቂት ልሂቃን ገሚሶቹ በስልጣን ላይ ተፈናጠው፣ ገሚሱ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ተከልሎ፣ ገሚሱ በምሁራን ዘርፍ ተሰልፎ፣ ገሚሱ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚል የቁልምጫ ስም ተሰጥቶት፣ ገሚሱ ሰባኪ፣ አስተማሪ፣ ፈዋሽ፣ አነቃቂ እየተባለ በሁሉም የእውቀት፣ የሙያና ሌሎች ዘርፎች ተሰማርቶ በብዙ መልኩ በሚያደርጓቸውም ሆነ በአደባባይ በሚናገሯቸው ነገሮች የአብላጫውን ሕዝብ ህይወት በአንድ ወይም በሌላ መልክ የሚጠቅም ወይም የሚጎዳ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል አቅም የፈጠሩ ግለሰቦችና ስብስቦች ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ ይህ የጥቂት ተጽዕኖ ፈጣሪ የአደባባይ ልሂቃን በብዝሃ ዝምተኛው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና የመፍጠርና አብላጫውን ሕዝብ ወደ ፈለጉት አቅጣጫ የመምራትና የማሾር ሂደት ዲሞክራሲ በሰፈነባቸውና የዳበረ የፖለቲካ ባህልም ባላቸው አገሮች ጎልቶ የሚታይ ክስተት ነው፡፡ ልዩነቱ በእነዚህ አገራት vocal minority የሚባለው የማህበረሰብ ክፍል እጅግ የተማረ፣ በሳይንሳዊ አስተሳሰብ፣ በጥናትና ምርምር በተገኙ እውቀቶች አብላጫውን ሕዝብ ማሳመን የሚችል ወይም በአንድ የተለየ ተሰጥኦው ቅቡልነት ያገኘ ወይም በኢኮኖሚም የጠነከረ ልሂቅ ስለሆነ ስልታዊ በሆኑ ተጽዕኖዎች ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቀባይነት ያላቸውን ፖሊሲዎች ጭምር በራሱ መንገድ የመገደብ፣ የመቀየርና ወደ ፈለገው አቅጣጫ የመውሰድ ብቃት አለው፡፡ ይህል ልሂቅ የTyranny of the vocal minority ውስጥ የሚፈረጅ ቢሆንም እኛ ዘንድ ካለው ጨፍላቂ ልሂቅ የተለየ ነው፡፡
በብዙ አፍሪካ አገሮች፤ በተለይም በአገራችን በኢትዮጵያ ያለው ይህ Tyranny of the vocal minority ውስጥ ያለው ልሂቅ የተለዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ በዚህ ስብስብ ውስጥ ልሂቅ የሚለው ከአንድ የዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር እስከ ገና በጊዜ ትምህርቱን መንገድ ላይ ገትሮ በአቋራጭ የአደባባይ ልሂቅ የሆነውን፣ ከሃይማኖት መሪ እስከ የአደባባይ የእምነት አቀንቃኝ፣ ከአገር መሪ እስከ ቀበሌ ካድሬ፣ በሙያ ጋዜጠኛ ከሆነው አንስቶ እግረ መንገዱን የተቀላቀለው፣ ከመብት ተሟጋች እስከ ብሄረተኝነት አቀንቃኝ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አደባባይ ላይ ራሳቸውን አውጥተው በማናቸውም ግዳይ ሃሳባቸውን ለሕዝብ የሚያጋሩና ተጽዕኖ ለመፍጠር ወይም ቅቡልነት ለማግኘት የሚደክሙ ሰዎችን ሁሉ ያቅፋል፡፡ ይህ ስብስብ በኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ግዳዮቻችን ላይ ያለው የተጽዕኖ ፈጣሪነት ልክ እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ ከፋፍለን ብናየው ለመረዳት ይቀለናል፡፡
ይህ የልሂቃን ጎራ የጋራ መገልጫዎች ባህሪያት ያሉትን ያህል እጅግ የተሰባጠረም ነው፡፡ በመጀመሪያ የወል መገለጫ ባህሪዎቹን በአጭሩ እንመልከት፡፡
1ኛ/ ተጽዕኖ ፈጣሪነትን (Influence) ማዕከል ያደረገ ልሂቅ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኛው ልሂቅ ተናጋሪ ወይም ሃሳብ አቅራቢ እንጂ አድማጭ አይደለም ወይም የመሆን ፍላጎት የለውም፡፡ በዚህም የተነሳ በሁሉም የሃሳብ መስጫ መድረኮች አሸንፎና ተቀባይነትን አግኝቶ መመለስን አስልቶ ስለሆነ ወደ አደባባይ የሚወጣው አዳዲስ ሃሳቦችን ከሌሎች የመቀበል ዝንባሌ የለውም፡፡ የራሱን ሃሳብ በሌሎች ላይ ለመጫን ከመዋሸት አንስቶ የማይቧጥጠው ተራራ አይኖርም፡፡
2ኛ/ እጅግ ቁጡና ተናዳፊ (Aggressive) ባህሪ የተላበሰ ነው፡፡ ሃሳቡን የማይቀበሉት ወይም ጠንከር ባሉ መከራከሪያዎች ውድቅ የሚያደርጉበትን ሰዎች ቁጡ በሆነ የውይይት ስልት (aggressive approach) በመጠቀም ያልተመጣጠነ ተጽዕኖ የመፍጠርና ከምክያታዊነት ይልቅ በጩኸትና በቁጣ ተጽዕኖ መፍጠር እና የመደመጥ አቅሙን ከፍ ማድረግ የሚችል ነው፡፡ ይህ ባህሪው ማንንም በአደባባይ ከማዋረድ፣ ከማንኳሰስ እና ከመፈረጅ አይመልሰውም፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው እንኳን የሃሳብ ተቀናቃኙን ይቅርና ፈጣሪውንም አጥረግርጎ ከመሳደብ አይመለስም፡፡
3ኛ/ (Contrast with silent majority) የጠቅላይነት ባህሪ የተላበሰ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ በዝምታ ውስጥ ያለውን የ”silent majority” በጥቅል ፍረጃ ውስጥ በማስገባት “ሕዝቡ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው” የሚሉ ሀረጎችን በመጠቀም በራሱ ዝምታ እና በፍርሃት ተለጉሞ የተቀመጠውን ሕዝብ የሃሳቡ ማዳበሪያ የማድረግ ዝንባሌ አለው፡፡ silent majority ወክሎ አደባባይ በመውጣት የሚሞግተው አካል ስለማይኖር ሁሌም ሕዝብን ያስፈራራል፣ ያወግዛል፣ ብዙዎችን ያዋርዳል፣ ያብጠለጥላል፣ አንዳንዴም በሕግ በሚያስጠይቅ ደረጃ በአንድ ማህበረሰብ ላይ ጥላቻና ስድብን ያዘንባል፡፡
4ኛ/ (Character assassination and defamation) ሙግትና የሃሳብ ፍጭት ያለባቸውን መድረኮች ይሸሻል ወይም መገኘት የግድ ከሆነበትም ውይይቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስድብ ልውውጥ፣ ሌሎችን ወደ ማጥቂያ መድረክነት ወይም ሌሎች ሃሳብ አፍላቂዎችን ከሃሳባቸው ይልቅ በሰዎቹ ማንነት ላይ ያተኮሩ ሃሳቦችን በመሰንዘር ውይይቶችን ያደፈርሳል፡፡
ከላይ ያሉትን የአደባባይ ልሂቅ ባህሪያት በመጠኑ ከገለጽኩ የአገራችን የአደባባይ ልሂቃንን በፈርጅ በፈርጁ ለማየት ከዚህ የሚከተሉትን ስብጥሮች ማየት ጥሩ ነው፡፡
1ኛ/ በትምህርት እውቀታቸውም ሆነ በህይወት ልምድ ያገኙትን ሰፊ እውቀት እና ብልሐት ለሕዝብ ለማቅረብ እና በአገራቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር በፍጹም ቅን እሳቤ ተነስተው ከዝምታ ይልቅ የአደባባይ ልሂቅነትን የመረጡ ሰዎች የመጀመሪያው ስብስብ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ዋነኛ ግባቸው ማህበረሰቡን ወደ ቀና አስተሳሰብ የመምራትና የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው የማድረግ ምሁራዊ ወይም ልሂቃዊ ግዴታ አለብኝ በለው የሚያስቡና እንቅልፍ አጥተው የሚተጉ ሰውች ናቸው፡፡ ቁጥራቸው ብዙም ባይሆን በኢትዮጵያ አናሳ ግን ድምጻቸው የሚሰማ ልሂቃን መካከል በስምና በሁሉም ሙያ ዘርፍ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰዎች አሉ፤ ነበሩም፡፡
2ኛ/ ቁንጽል እውቀትና ቁንጽል መረጃ ይዘው ግን ደግሞ እጅግ ድፍረት በተሞላው መልኩ በሁሉም ጉዳይ ላይ ሰፊና አታካች የሆነ የልሂቅ ትንታኔ ሲሰጡ የሚውሉ፣ ለንባብም ሆነ ለተሻለ ትምህርት ጊዜ የሌላቸው፣ ሁሌም ለመደመጥ፣ ለመታየት፣ ተጽዕኖ ለመፍጠር፣ ብዙዎችን ለማስደመም በጥድፊያ ላይ ያሉ ነገር ግን በሚናገሩት፣ በሚጽፉት እና አደባባይ በሚወጡበት ጉዳይ ላይ ጥልቅና የተሟላ መረጃና እውቀት ለመሰብሰብ ጊዜ የሌላቸው ልሂቃን የተሰባሰቡበት ማዕቀፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የአደባባይ ልሂቃን መንደር ትልቁን ቁጥር የሚይዙት በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉት ሰዎች ሲሆኑ አብዛኛውን የአደባባይ መድረኮች ማለትም የመገናኛ ብዙሃን የሆኑ ሚዲያዎችን፣ ዩቲዩቦችን፣ የድህረ መረብ ማህበራዊ ገጾችን በተሳትፎም ይሁን በባለቤትነት የተቆጣጠሩና ከፍተኛ አድማጭና ተከታይ ያላቸው ናቸው፡፡ እነኚህ ልሂቃን በተለይም ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ በሆኑ መድረኮች ላይ ጎልተው ይታያሉ፡፡
3ኛ/ መረን የለቀቀው የልሂቃን ስብስብ የሚገኝበት ጎራ ነው፡፡ ይህ ስብስብ በተለይም ቲክቶክ፣ ዩቲዩብና ፌስቡክን የተቆጣጠረ፣ የወጣቱን ማህበረሰብ ክፍል አትኩሮት የሳበ፣ ሚሊዮኖችን አድማጭ ማድረግ የቻላ እጅግ የተሰባጠረ ስብስብ ሲሆን ተሳዳቢዎች፣ አክራሪ ብሄረተኞች፣ ጽንፈኛና አክራሪ ሃይማኖተኞች፣ ጠርዝ የረገጡ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ቧልተኞች እና አላፊ አግዳሚውን በማዋረድና በማቃለል የሚሳለቁና በዚህም ገንዘብ የሚሰሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት ክፍል ነው፡፡ ይህ ስብብስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ የፖለቲካ ቁርሾዎችን፣ ሃይማኖት ተኮር ግጭቶችና የማህበረሰብ መናቆሮች ትልቅ የትኩረቱ ማዕከል ያደረገና ብሽሽቅና መዘላለፍን ዋነኛ የመግባቢያ ቋንቋው ያደረገ ልሂቅ የሚገኝበት ነው፡፡ በዚህ ስብስብ ውስጥ ያሉት ልሂቃን ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በተከታይና በአድማጭ ብዛት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙ ሲሆኑ እጅግ የሚገርመው ደሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን silent majority ትኩረት ያገኙ ናቸው፡፡
4ኛ/ የነጋዴ ባህሪ የሚታይበት እና አብዛኛውን ትኩረቱን መዝናኛዎችና ለገበያ የሚውሉ ቁሳቁሶች ላይ ያተኮረ፤ በአደባባይ ፖለቲካ ወይም የአገር ጉዳይ አያገባኝም የሚል፣ ቧልት ላይ ያተኮረ እና አልፎ አልፎም ሰብአዊ እርዳታዎችን ማዕከል ያደረገ የልግስና ሥራዎች ላይ ያተኮረ ልሂቅ እና በግለሰብ ኑሮዎች ላይ ብቻ ያተኮሩ ይዘት ያላቸውን ሃሳቦች ይዞ አደባባይ የወጣ ነው፡፡ ይህም ስብስብ የsilent majority ትኩረት የተቸረው ነው፡፡
ጽሁፌን ለማጠናቀቅ የኢትዮጵያ Gene Z ከወዴት አሉ? በሚል የጻፍኩትን ከዚህ በፊት ያነበባቸው ሰዎች በቀላሉ ይህን ጽሁፍ አብራችሁ ልታዩት ትችላላችሁ፡፡ እንደ እኔ ምዘና ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የድህረ መረብ ትውልድ በ3ኛውና በ4ኛው የአደባባይ ልሂቅ ጎራ ውስጥ የሚገኝ ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ ከኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮና ማዳጋስካር ከመጡ Gene Zዎች ጋር በአካል የመገናኘት እና ቁጭ ብሎ የማውራት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ በእነዚህ አገራት ያሉ ወጣቶች ስለአገራቸው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያላቸው ጥልቅ እውቀት፣ ያየሁባቸው በራስ የመተማመን ስሜት፣ እውቀታቸውንና ሃሳባቸውን በድፍረት ለመናገር ያላቸው ብቃትና ጥንካሬ፣ በማህበረ ድህረ ገጾች ላይ ስለሚለዋወጡዋቸው ሃሳቦች፣ መንግስታቶቻቸውን ተጠያቂ ለማድረግ የሚሄዱበት እርቀትና መብታቸውን ለማስከበር እያካሄዱት ስላለው ንቅናቄ ያካፈሉኝን ሃሳቦች ይዤና ታዝቤ የኢትዮጵያ Gene Zዎች እራሳቸውን የደበቁበትን የአደባባይ ጥጋጥግ ስመለከት ብዙ ሃሳቦችን አጭሮብኛል፡፡ እሱን ወደፊት አካፍላችኋለው፡፡
ይህ አደባባዩን የተቆጣተረ፣ በገዢና ተገዢ፣ በአጥፊና ጠፊ፣ በበዳይና ተቆርቋሪ ተፈራርጆ የምታየው ኢትዮጵያዊው ድምጹ እንደ ብራቅ የጎላ ግን እጅግ የተከፋፈለና የተቧደነ፣ የተበታተነና አቅም አልቦ የሚመስል ተጽዕኖ ፈጣሪ ልሂቅ ኢትዮጵያን ይታደጋታል ወይስ ከ silent majority ዝምታ ጋር ተዳምሮ በጩኸት ያፈርሳታል?
መልካም ሰንበት!