እንደምን ከርማችኋል የመልዕክተ ቅዳሜ ታዳሚዎች? ላለፉት ሁለት ሳምንታት ስብሰከሰክበት በቆየሁት ርዕስ ላይ ለማተኮር ወደድኩ፡፡ ለምን ጭካኔያችን በዚህ ልክ በረታ? ለምን እርስ በርስ መጠፋፋትን መረጥን? ለምን በበደሎቻችን ክብደት መለካካትን መረጥን? ለምን የአንዳችን ስቃይ የሌላችን የፖለቲካ ግብ ማቀንቀኛና ማሳለጫ ሆነ? ለምን እንዲህ የሰውን አዕምሮ ሰቅፎ የሚይዝ፣ ለማየት እና ለመስማት የሚሰቀጥጡ የጭካኔ እርምጃዎች በራሳችን ወገን ላይ ለመፈጸም ተገደድን? የሚሉት ጥያቄዎች ለረዥም ጊዜ አዕምሮ ውስጥ ቢመላለስም ባሳለፍናቸው ተከታታይ ሳምንታት ደግሞ እንቅልፍ በሚነሳ ደረጃ እየደጋገመ ያቃጭልብኝ ጀመር፡፡
በአርሲ ውስጥ በኦሮቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ በተከታታይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያዎች፣ አስቀጥሎም በቤኒሻንጉል ጉምዝ በአንድ ለሊት በጭካኔ የተፈጁትን በአሥሮች የሚቆጠሩ ንጹሐፍን ዜጎች፣ ከዛም ቢቢሲ ያወጣውን ከ2600 በላይ የአማራ ክልል ሴቶች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አባላት መደፈር፣ ከዛም በአማራ ክልል አንድ ወጠጤ ጎረምሳ እራሱን የፋኖ ታጣቂ ነኝ እያለ የሰው እጅ እንደ ማገዶ እንጨት በመጥረቢያ ሲፈልጥ የሚያሳይ ቪዲዮ በገዢው ፓርቲ ሰዎች ለሕዝብ እንዲደርስ መሰራጨቱ፣ ተያይዘውም የቆዩና አዳዲስ የጭካኔዎቻችንን ለከት ማጣት እና ማህበረሰባችን ውስጥ እራሳቸውን ከአውሬም ያከፉ ሰዎች የሚፈጽሟቸው አሰቃቂ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችና የፎቶግራፍ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨታቸውን ተከትሎ በመንግስት ሹማምንትና ደጋፊዎች የሚሰነዘሩትን አስተያየቶች፣ የመንግስት ተቃዋሚ በሆኑ ሃይሎች የሚሰጡትን ግብረ ምላሾች፣ እርስ በርሳችንም በእነዚህ የጭካኔ ድርጊቶች ዙሪያ የምንወራወራቸው ቃላቶች፣ መወራረፎችና እሰጣገባዎችን ስመለከት እንደ አገር እና እንደ ማህበረሰብ የገጠመን እጅግ ግዙፍ ችግር ክፉኛ ያሳስበኝ ጀመር፡፡
ጭካኔን ያማከለ ፖለቲካ ወይም ስለ political cruelty ከዚህ በፊት በስፋት የጻፍኩበት ቢሆንም ለማስታወስ ያህል ትንሽ ስለትርጉሙ አጭር ነገር ልበል፡፡ Political cruelty ወይም ጭካኔን ያማከለ ፖለቲካ ማለት በአጭሩ ሆን ተብሎና ታስቦበት በሰዎች ላይ እጅግ ዘግናኝ የሆነና ከፍተኛ ጉዳትን ሊያደርስ የሚችል አድራጎት በመፈጸም ሰዎችን ለአካላዊ ወይም ለስነልቦናዊ ጥቃትና ጉዳት በማጋለጥ ከሰውነት ተራ ወጥተው እንዲጎዱ፣ እንዲዋረዱ እና ጥልቅ ፍርሃት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ አላማውም ፖለቲካዊ ግብ ያለው እና በተለይም የሥልጣን የበላይነትን ለመቀዳጀት በማሰብ በተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ዘለቄታዊ ጠባሳን የሚተው ስቃይ መፈጸምና ሰዎችን ወይም ኢላማ የተደረገውን የማህበረሰብ ክፍል ከሰውነት ተራ እንዲወጣና እንዲዋረድ የማድረግ degrading እና dehumanization ትልም ያለው ነው፡፡ መገለጫውም ፍርሃትን የማስረጽ ስልት (weaponizing fear)፣ የተጋነነና የተሳሳተ መረጃን ለማስተላለፍ ትርክቶችን ለመፍጠር (spreading misinformation) እና በጨካኝነት አድራጎት የሚገኝ የመፈራት ጸጋን ለመላበስ ተብሎ የሚፈጸም አድራጎት ነው፡፡ ይህን ድርጊት አንባገነናዊ መንግስታት እና ትወራራሽ ባህሪ የተላበሱ ታጣቂ ቡድኖች ወይም የተደራጁ ሃይሎች የሚፈጽሙት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጭካኔን እና አረመኔያዊ ባህሪን ከተላበሰ ብዙ አሥርት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ችግሩ ዕለት ተዕለት እየተባባሰባ የጭካኔያችንም ደረጃ በዛው ልክ እየጠነከረ ለመምጣቱ ግን ከብልጽግ መንግስት ጋር ያሳለፍናቸው ጥቂት አመታት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ዋናው ጥያቄ ምን ሆነን ነው እዚህ አይነት በጭካኔና መገለጫ ባጣ የበቀለኝነት ስሜት ውስጥ ተውጠን የአንዳችን ስቃይ የሌላችን የፖለቲካ መቆመሪያና መሳለቂያ እስከመሆን የደረስነው? የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይረብሸኝ ጀመር፡፡ ብዙውን ጊዜ አምባገነናዊ የሆኑ የአገዛዝ ሥርአቶች ሕዝብን አሸማቆና በፍርሃት ቆፈን ጠርንፎ ለመግዛት የሚመርጡት መንገድ የጭካኔ እርምጃዎችን በሕዝብ ላይ በጅምላና በተናጠል በመውሰድ ማህበረሰብን ሽብር ውስጥ መክተት ነው፡፡ አሁን ግን መረዳት የቻልኩት ለካ ጭካኔና አረመኔያዊ አስተሳሰብ እያደር ከጨካኝ አገዛዞች ወደ ሕዝብ እንደ ወረርሺኝ በሽታ ይጋባል፡፡ አዎ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ ጨካኝ እና ክፉ ሊባሉ የሚችሉ የአገዛዝ ሥርአቶች ተፈራርቀውበታል፡፡ በእኔ እድሜ እንኳ ጨካኝ የሚባለውን የ17 አመት ወታደራዊ የደርግ አገዛዝ፣ ከጫካ ስነ ልቦና ሳይላቀቅ 27 አመት ግፍን የሥልጣኑ ማጽኛ ያደረገውን የወያኔን አገዛዝ እና አሁን ደግሞ ወደር የሌለው የአውሬነት፣ የጨካኝነት፣ የዘረኝነት ጥግን ያየንበት የብልጽግናን ሥርአት አልቦ ዘመን ብንቃኝ ደረጃቸው ይለያይ እንጂ ሁሉም በጭካኔ፣ በሽብር፣ በሰቆቃ፣ በእልቂት የተሞሉ ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየናቸው ያሉ የጭካኔ አይነቶች ግን በግብር ድርጊቱን ከፈጸሙት ግለሰቦችና ቡድኖች ባለፈ የእያንዳንዳችንን ስብዕና እየተፈታተኑ ያሉ፣ እንደ ማህበረሰብም የገባንበትን እጅግ አስፈሪና አደገኛ ሁኔታ የሚያሳዩ እና ነገንም እንድንፈራ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
+ እንዴት ነው አንድ አገርን የሚመራ አካል በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን፤ በተለይም አለም በሚከታተለው እንደ ቢቢሲ ባለ የዜና ጣቢያ በአማራ ክልል ያሰማራሃቸው ወታደሮች ከ2600 በላይ ሴቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ ደፍረዋል ሲባል ምንም እንዳልሰማ ዝም የሚለው?
+ እንዴት ነው አንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ነኝ የሚል ሰው ከቤተመንግስቱ ቅጭ ብሎ የአንድ ወጣት እጅ በመጥረቢያ ሲጨፈጨፍ የሚያሳይን ቪዲዮ ልክ ሌላውን ወገን ያዋረደ መስሎት ‘ከማረክናቸው ታጣቂዎች ስልክ ያገኘነው መረጃ ነው፣ ገና ምን አይታችሁ ሌላም እንለቃለን’ የሚል መረን የለቀቀ የ political cruelty እንደ ስልት መወሰዱን የሚገልጽ መልዕክት ለሕዝብ የሚያሰራጨው?
+ እንዴት ነው አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ወታደሮችህ በጦርነት ወቅት ሴቶች ደፍረዋል ሲባል “የእኔ ሴት ወታደሮች በእንጨትና በብረት ነው የተደፈሩት፣ የእናንተ ሴቶች ግን በሰው ነው” ብሎ ጭካኔን እና በደልን በዚህ ደረጃ ለማወራረድ ሲሞክር የምናየው?
+ እንዴት ነው አንድ ጨካኝ እና አዕምሮው ወደ አውሬነት የተቀየረ ሰው ወይም በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉ የተሰባሰቡ ታጣቂዎች እራሳቸውን በቪዲዮ እየቀረጹ እጅግ ሰቅጣች የሚባል አድራጎትን በሌሎች ሰዎች ላይ ሲፈጽሙ ማየት የተለመደ የሆነው፣
+ እንዴት ነው የአንድ አገር የመከላከያ ሰራዊት የማረካቸውን ሴቶች ጡት እየቆረጠ፣ ወንዶቹን ብልታቸውን እየቆረጠ፣ አንዳንዶቹንም መሬት ላይ አጋድሞ በጥይት እና በድንጋይ ናዳ ጨፍጭፎና አንዳንዶቹንም ከነነፍሳቸው አቃጥሎ ቪዲዮ ለሕዝብ የሚለቅበት አገር ባለቤት የሆነው?
+ እንዴት ነው የእኛ ያልናቸው ታጣቂ ሃይሎች ሰቅጣጭ ወንጀሎችን፣ ጭካኔዎችን በሕዝብ ላይ፣ በወገን ላይ፣ በሌላው የሰው ልጅ ላይ ሲፈጽሙ ድርጊቱን በጋራ ሆኖ ከማውገዝ ይልቅ አጥፊዎቹን ለከከላከል፣ የወል ገበናዎቻችንን ለመሸፋፈን፣ የአንዱን ሰጣንነት ለማጉላት፣ የራስን ገበና ለመሸፈን የምንጋጋጠው?
እነዚህን ጥያቄዎች እንዳነሳ ያደረገኝ እያንዳንዱን የግፍ ተግባር ለማውገዝ የምለጥፋቸውን መልዕክቶችና ጥሪዎች ተከትሎ ያስተናገድኳቸው የሕዝብ አስተያየቶችና የተላኩልኝ መልዕክቶች የጭካኔ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ (political cruelty) ምን ያህል በማህበረሰባችን እሳቤ ውስጥ ስር እንደሰደደ እንድታዘብ ስላደረገኝ ነው፡፡ እስኪ አንዳንድ የቅርብ ምሳሌዎችን ልግለጽ፤
1ኛ/ የብልጽግና መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ደፈረ ሲባል ድርጊቱን ከማውገዝ ወይም አልተፈጸመም ውሸት ነው ብሎ በማስረጃ ከመሞገት ይልቅ የመከላከያ ሰራዊታችንን ስም ለማጥፋት ነው የሚል እጅግ ከሞራል ልዕልና የወረደ፣ ከሰውነትም ተራ የራቀ፣ ጭካኔ የተሞላው ሙግት ይዘው አደባባይ የወጡ የአገዛዙ ካድሬዎችና አድናቂዎችን ልብ በሉ፤
2ኛ/ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአርሲ ዞን በተከታታይ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ፣ እንዲሁም በቅርቡ የሽኔ ታጣቂዎች ናቸው የተባሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከ40 በላይ ሰዎችን በመግደልና ብዙዎችን በማቁሰል የተፈጸመውን ጭፍጨፋ የሚገልጹ ዜናዎችና ውግዘቶችን ተከትሎ ይህን የጭካኔ እርምጃ የፈይሰሙትን የክልሉን ታጣቂዎች ለመከላከል በይፋ በአደባባይ ወጥተው የሚሟገቱ የኦሮሞ ልሂቃንን እና አንዳንድ ነውርና ጭካኔ ጌጣቸው የሆኑ ሰዎችን ስድብና የጥላቻ ንግግር አስተናግደናል፡፡ እንዴት ኦሮሚያ ውስጥ የሚፈጸምን ግፍ ታጋልጣላችሁ ብለው ለስድብ አደባባይ ከሚወጡት ሰዎች ባልተናነሰ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉ የኦሮሞ ተወላጆች ጭምር ዝምታን መምረጣቸው ሌላው አስፈሪ የማህበረሰባችን ገጽታ ነው፡፡
3ኛ/ በአማራ ክልል አንድ የፋኖ ታጣቂ የነበረ ጎረምሳ የሰው እጅ በመጥረቢያ እየጨፈጨቸ የሚያሳይ እጅግ ሰቅጣጭ የቪዲዮ ምስል መሰራጨቱን ተከትሎ ድርጊቱን የሚያወግዝ መግለጫ ሲወጣ አድራጎቱን ከማውገዝ በፊት ስለማስረጃው ምንጭ እና ማን እንዲፈጸም እንዳደረገ እራስን መከላከል በሚመስል አኳኋን ከፋኖ ደጋጊዎች እና ከአማራ ልሂቃን ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶች እንዲሁ በራሳቸው እጅግ የሚሰቀጥጡ ነበራ፡፡ ኦነግ ሽኔ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰዎችን በእምነታቸውና በብሄር ማንነታቸው ለይቶ የጭካኔ እርምጃ ወሰደ ሲባል ድርጊቱን በቀጥታ ምንም አይነት የማስረጃ ማጣሪያ ሳይጠይቁ በነቂስ ወጥተው የሚያወግዙ እና የሚያነውሩ ሰዎች ልክ አንድ የፋኖ አባል ነኝ ያለ ሰው የጭካኔ እርምጃ ወሰደ ሲባል በተረጋጋ መንፈስ መጀመሪያ ድርጊቱን አውግዞ ከዛም በመረጃው ትክክለኝነት ላይ ጥያቄ ማንሳት ሲገባ ልክ የአማራ ተወላጅ የሆነ ሰው የነውርና የጭካኔ እርምጃ በሌሎች ካልተገደደ ወይም ካልተገዛ በቀር ፍጹም እንደማይፈጽም አድርጎ ለመከራከር የተሄደበት እርቀት እንዲሁ የገባንበትን የጭካኔ ፖለቲካ ጥግ ማሳያ ነው፡፡
ነውሮቻችንን፣ የጭካኔ እሳቤዎቻችንን እና እርምጃዎቻችንን፣ እርስ በርስ ያለንን መከፋፋት፣ መናናቅና መፈራረጅ እጅግ ሊያባብስ የሚችል የፖለቲካ አውድ ውስጥ መቆየታችን ምን ያህል እየጎዳን እንደሆነ ከላይ የጠቀስኳቸው አይነት ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ እችላለሁ፡፡ አንድ የጭካኔ ድርጊት የኦሮሞ ተወላጅ ላይ ሲፈጸም የሚጮኸው ኦሮሞ ብቻ ከሆነ፣ እንዲሁ የአማራ ሴት ስትደፈር፣ ሕጻናት ሲገደሉ፣ የአማራ ተወላጆች በጭካኔ ሲሳደዱና ሲገደሉ ድምጹን የሚያሰማው አማራው ብቻ ከሆነ፤ የትግራዋይ ሴቶች ሲደፈሩና ሲገደሉ እንዲሁ ጉዳዩን ለትግራይ ተወላጆች ብቻ የምንተወው ከሆነ፣ ወላይታው ሲቸገርና ሲሳደድ እንዲሁ ለወላይታው ከተውነው፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በማንነቱ ሲጠቃ እንዲሁ የራስህ ጉዳይ በለን ፊታችንን ካዞርን ጭካኔ በሁላችንም አዕምሮ ውስጥ ጎጆ ቀልሷል ማለት ነው፡፡ ተቆርቋሪነታችንም ከሰውነት የመነጨ መሆኑ ቀርቶ ከብሄር ወይም ከሃይማኖት መቧደን ጋር ተያይዟል ማለት ነው፡፡ ይህ አይነቱ አደገኛ እሳቤ በመንግስታዊ ተቋማት ሲደገፍና በሹማምንቶች ሲቀነቀን ደግሞ የአገሪቱ ፖለቲካ ጭካኔን ያማከለ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ጭካኔን ያማከለ ፖለቲካ ዋነኛ መገልጫዋ ሆኗል፡፡ ጨካኝ የአገር መሪዎች፣ እጅግ ጨካኝ የሃይማኖት አባቶች፣ እጅግ ጨካኝ ልሂቃን፣ እጅግ ጨካኝ የአገር ሽማግሌዎች፣ እጅግ ጨካኝ አባገዳዎች፣ እጅግ ጨካም ምሁራን፣ እጅግ ጨካኝ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ እጅግ ጨካኝ ፖለቲከኞች ነግሰውባታል፡፡ በጭካኔዎቻችን ደረጃ ልክ እንፎካከራለን፡፡ በጭካኔዎቻችን እንበሻሸቃለን፡፡ በነውሮቻችን ልክ ቁመት እንለካካለን፡፡ ጭካኔ ገበናችን ሆኗል፡፡ የሌላው የጭካኔ እርምጃ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ እና ማነወሪያችን ሆኗል፡፡
የጭካኔን እርምጃ በባህሪውና በአድራጎቱ ብቻ ድርጊቱን ማንም ይፈጽመው፣ ለምንም ተልዕኮ ወይም ቅዱስ አላማ ማሳኪያ ያድርገው፣ በማንም ላይ ይፈጽመው (እጅግ በመንጠላው ሰው ላይም ቢሆን እንኳ) ልናወግዘው እንጂ ልንላመደው አይገባም፡፡ አድራጎቱን እና አድራጊዎቹን ያለ ምንም ቅደም ሁኔታ ልንጠየፋቸው፣ ልናወግዛቸውና ልንፋረዳቸው ይገባል እንጂ ልንከላከልላቸው አይገባም፡፡ ጭካኔን የተላመደ ሕዝብ፣ ለጭካኔ እርምጃዎች ማስተባበያ ወይም መከላከያ የሚሰጥ ማህበረሰብ እጣ ፈንታው መጠፋፋት ብቻ ነው፡፡ ሊያውም እጅግ ዘኛኝና ዘር ተኮር የሆነ ጥቃትና ጭካኔ ብሄራዊ ቅርጽ ከያዘ ያ አገር መቼም ቢሆን ለማንም ሰው ከለላ ሊሆን አይችልም፡፡ ዛሬ ችላ ያልነው ጭካኔ ነገ ሁላችንንም ይበላል፡፡
ጭካኔን ማዕከል ካደረገ የመጠፋፋት ፖለቲካ ኢትዮጵያንም ሆነ እራሳችንን ለመታደግ ዛሬም አልረፈደም፡፡ የጭካኔ አድራጎቶችን እንጠየፍ፣ በአንድ ድምጽ እናውግዝ፣ ጨካኞችን እናግልል፣ ተጠያቂሚ እናድርግ፡፡
መልካም ሰንበት!