ዘመነ ስግጥና፤ አደንቁሮ መግዛት!

ዘመነ ስግጥና፤ አደንቁሮ መግዛት!

የዛሬው መልዕክተ ቅዳሜ እንደ ሌላው ጊዜ ብዙ አስቤበት የመረጥኩት ርዕስ ሳይሆን የበይነ መረቡ አየር አስገድዶኝ ያረፍኩበት ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ከወዲሁ እየጠቆምኩ ወደ ፍሬ ጉዳዮ ልግባ፡፡ እንደ አገር ጸረ እውቀት፣ ጸረ ትምህርት፣ ጸረ ግንዛቤ፣ ጸረ ሳይንስ በሌላ አገላለጽ ድንቁርና፣ አላዋቂነት፣ ይሉኝታ ቢስነት፣ አውደልዳይነት፣ ግድ የለሽነት፣ ህሊና ቢስነት በከፍተኛ ሁኔታ አደባባይ ለገበያ የቀረበበት፣ ይህ ሃሳብ ገዢ ሃሳብ ሆኖ የወጣበት፣ ያሸለመበት፣ የሚሊዮኖችን ቀልብ የሳበበት፣ ምሁራዊ የሚመስሉ የድጋፍ ትንታኔዎች የተሰጠበት፣ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ያገኘበት እና በተወሰነ ደረጃም መንግስታዊ ድጋፍና ቅቡልነት ያገኘበት ሁኔታን ስለታዘብኩ የዛሬን መልዕክተ ቅዳሜ ወደ አደንቁረህ ግዛ የትሸጋገርንበትን አደገኛና አስፈሪ ሁኔታ ለመዳሰስ ወደድኩ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ምሁር ጠል፣ እውቀት ጠል፣ ሳይንስ ጠል፣ ዲሞክራሲ ጠል ከሆነ ብዙ አሥርት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በሌላ አገላለጽ ፖለቲካችን ከሰገጠ ብዙ አሥርት አመታትን አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከምሁራን ይልቅ በጡንቻቸው የሚያስቡ ጉልበተኞች ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ በተቃራኒው ምሁራን ሲሳደዱ፣ ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ፣ ሲዋከቡና በአደባባይ ሲዋረዱ ነው የሚታየው፡፡ ደርግ ምሁር ጠል እና የጨካኝ ወታደሮችና አቢዮት ጥበቃዎች ስብስብ ስለነበር እስር ቤቶቹ ሁሉ በምሁራን የተሞሉ ነበሩ፡፡ ደርግን የተካው ወያኔም ሳይውል ሳያድር ነበር ከምሁራን ጋር ጸቡን የጀመረው፡፡ ወያኔ የተቀመጠበት የሥልጣን ወንበር ሳይረጋ ነበር በመላው አለም በእውቀታቸው የተመሰከረላቸውና በአሜሪካና በአውሮፓ ትላልቅ ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ያስተምሩ የነበሩ 44 የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህራንን በቂ እውቀት የላችሁም በሚል በአንዲት ነጠላ ደብዳቤ ያባረራቸው፡፡

አዎ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ድንቁርና ጎጆውን ከቀለሰ ብዙ አሥርት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ አዎ፤ ፖለቲካችን ምሁር ሆኖ ሳይንሳዊ በሆነ እውቀቱ እየተመራ እና እየተመራመረ እውነትንና ለአገር የሚጠቅም እውቀትን በድፍረት አደባባይ ወጥቶ የሚናገር ምሁር አይፈልግም፡፡ እውቀት ከሥልጣን የሚመነጭ የሚመስላቸው አንባገነኖች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት አገር ስለሆነ የሥልጣን አናት ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ሁሉንም አዋቂዎች ናቸው፡፡ ለነገሩ የሁሉም አምባገነኖች መገለጫና የወል ባህሪ በሁሉም ነገር ላይ አዋቂ ሆነው መከሰታቸው ላይ ነው፡፡ “አማካሪዎቼ እንደነገሩኝ ከሆነ” የሚል መንደርደሪያ አይጠቀሙም፡፡ በግብርናውም፣ በሕክምናውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በፖከቲካውም፣ በሃይማኖቱም፣ በፍልስፍናውም፣ በሕጉም፣ በማህበራዊ ሳይንሱም፣ በፊዚክስና ኬሚስትሪውም ሳይቀር አዋቂ መስለው ነው አደባባይ ላይ የሚከሰቱት፡፡ በሁሉም ጉዳይ ላይ ቁንጽል ነገር ይዘው አደባባይ በመውጣት ምሁራንን እና በየመስኩ ሰፊ ምርምር ያደረጉ ፕሮፌሰሮችን ጭምር ከእግራቸው ሥር ቁጭ አድርገው ሊያስተምሩና ሊመክሩ ይሞክራሉ፡፡ በቅርቡ አብይ አህመድ የሕክምና ዶክተሮችን ሰብስቦ ስለ አዕምሮ ቀዶ ህክምና ሲያብራራ እንደነበረው ማለት ነው፡፡

ፖለቲካችን እና ፖለቲከኞቻችን ከሰገጡ ወይም የድንቁርናን መንገድ ከመረጡና ረዘም ያለ ጊዜ ቢቆይም የ’አደንቁረህ ግዛ’ ሥልት ግን በዘመነ ብልጽግና የተዋወቀውንና የተበረታታውን ያህል በማንም ዘመን ሆኖ አያውቅም፡፡ ያለፉት የአገዛዝ ሥርአቶች ምሁር ጠል ቢሆኑም በዚህ ደረጃ ግን ትምህርትና እውቀት ጠል አልነበሩም፡፡ የብልጽግናን አስተዳደር ለየት የሚያደርገው ምሁራንን መጥላትና መፍራት ብቻ ላይ ሳይወሰን ትምህርትና እውቀትንም አብሮ የመጥላት እና ትውልድን ማደንቆር አንድ የአገዛዝ ሥልት አድርጎ መውሰዱ ላይ ነው፡፡ ይህን የምለው ከሰሞኑ ‘የሰግጥ’ ንቅናቄ ላይ ብቻ ተወስኜ ሳይሆን የአገዛዝ ሥርአቱ ከመጣ ወዲህ “አነቃቂ” የሚል ታርጋ የተሰጣቸውና አንዳንዶቹም በአደባባይ በአገዛዙ ሥርአት ሽልማት እና እውቅና የተሰጣቸው በርካታ ድንቁርናን፣ ዳተኝነትን፣ ከአገርና ከማህበረሰብ በፊት ራስን እና ረብጣን ማስቀደም አዋጪ መሆኑን፣ በጸሎት የባንክ አካውንታችሁን በሚሊዮን ገንዘብ እንሞላዋልነ የሚሉ ሰባኪያን ያፈራ ብቻ ሳይሆን ሆን ብሎም ያዘመተ ሥርአት ነው፡፡

ወጣቱን ትውልድ ከእውቀት፣ ከውነት፣ ከፍትህ ተቆርቋሪነት፣ ከአገር ፍቅር እና ለማህበረሰብ ጥቅም ተቆርቋሪ ከመሆን በማራቅ በራሱ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲጠመድ፣ ጊዜውን በቧልት፣ በስድብና ንትርክ እንዲያጠፋ እና በአደባባይ ማህበረሰብን በማዋረድ፣ የማህበረሰቡን እሴቶች በመናድ፣ ምሁራንን በመዘርጠጥና ጠያፍ የሆኑ ነገሮችን በመስራት የሚኮራ፣ ዝና እና ሃብት የሚያፈራ፣ ከዛም አልፎ በመንግስት መድረኮች ጭምር የሚሸለም ትውልድ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ እስኪ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የክብር ኒሻን የሸለማቸውን የሶሻል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ የተባሉ ግለሰቦችን ማንነት ዞር ብለን እንቃኝ፡፡ አንዳንዶች (ሁሉም አላልኩም) በተሳዳቢነታቸው፣ ሰዎችን በማዋረድ፣ የሃሰት ዜናዎችን በማሰራጨት፣ ማህበረሰብን በመዝለፍ እና በብዙ የነውር መገለጫ በሆኑ ባህሪያቸውን አደባባይ ይዘው ወጥተው ከእውቀትና ከእውነት የተጣሉ አስፈሪ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡

አዎ፤ በዘመነ ሰግጥ ብልግና እና ድንቁርና የክብር ሽልማት ያሰጣል፣ ካባ ያስደርባል፣ የኒሻን ሽልማት ያሰጣል፡፡ ደንቁሩ፣ ደድቡ፣ ከትምህርት እራቁ፣ ሰግጡና እውቅና አግኙ የሚል መሪ መፈክር የያዘ አንድ ዘሎ ያልጠገበ ጎረምሳ የአገሪቱን መገናኛ ብዙሃን ማነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ትምህርት ቤቶችን እየዞረ እንዲጎበኝና ሕጻናቶች ምሳሌ እንዲያደርጉት ሲደረግ፤ ከዛም አልፎ የአገሪቱ አየር ሃይል ካምፕ ውስጥ ተገኝቶ ያንን የተከበረ ተቋም በሚያዋርድ መልኩ “ሰግጡ” እያለ ወታደሮችን እንዲያነቃቃ ሲደረግ ይህ ጉዳይ አገራዊ ፕሮጀክት ተደርጎ የተወሰደ ‘የአደንቁረህ ግዛ’ ስልት መሆኑን ከማረጋገጥ ያለፈ ሌላ ምን መልዕክት ሊኖረው ይችላል፡፡ ከአሥር አመት ያላነሰ በሕክምናው ዘርፍ ተምሮ ስፔሻሊስት የሆነ ዶክተር የቤት ኪራይ መክፈል አቃተኝ፣ ዳቦ በሙዝ ነው በልቼ የምውለው፣ የትራንስፖርት አጥቼ በእግሬ ነው የምንከራተተው በሚልበት አገር ትምህርት ጠል የሆኑ የድንቁርና ሰባኪዎች በቪ 8 መኪና እና በጠባቂዎች ታጅበው የሚንፈላሰሱበት አገር ያገራነው ድንቁርናን የመግዣ መሳሪያ ያደረገ መንግስታዊ ሥርአት እንዲኖር ስለፈቀድን ብቻ ነው፡፡

እውቀት፣ መማርና መመራመር፣ ለአገር በእውቀት ላይ ተመስርቶ ማሰብና ማሰላሰል የሚያሳስር፣ የሚያሰድድ፣ የሚያደኸይ እና በማህበረሰቡም ዘንድ የማያስከብር ከሆነ ድንቁርና ወይም መደንቆር እንደ ጽድቅ ይቆጠራል፡፡ “Ignorance is bliss” የሚለው የ18ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ታዋቂ ገጣሚ Thomas Gray በ1742 እ ኤ አ በጻፈው ግጥም ውስጥ የተንጸባረቀው አገላለጽ ቦታ የሚያገኘውም በእንዲህ ያላ ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ድንቁርናን ካባ ማልበስ እና መሸለም የዛሬን ብቻ ሳይሆን የመጪውንም ዘመን ጨለማነትና አስፈሪነት ማሳያ ነው፡፡ ገጣሚው እንዲህ ይላል፤ “Where ignorance is bliss, ’tis folly to be wise”. መልዕክቱም ለምንም ነገር ግድየለሽ በመሆን ደስታን ብቻ ማጣጣም፣ እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ወደ ጎን ገሸሽ አድርጎ በመተው እና ምንም እንዳልተፈጠረ ያህል በመቁጠር የራስን ደስታ ብቻ ማጣጣም፣ በአገር ላይ ያንጃበቡ አደጋዎችን፣ የማህበረሰቡን ችግሮች፣ ያፈጠጡ ኢፍትሃዊነትን፣ በደልን፣ ጎልተው የሚታዩ ግፎችን እና መከራዎችን ምንም እንዳልተፈጠረ ያህል በመቁጠር ባልተጨበጠ ደስታ መናኘት፡፡

በትግራይ መከራ ውስጥ የተፈጠረው ይህ ግልብ ደንቁሩና ተደሰቱ የሚለው ወጣት በዚህ ደረጃ promote የተደረገው ያለምክንያት እንዳይመስላችሁ፡፡ ባሳለፍናቸው ጥቂት አመታት የአገሪቱ ወጣት በተለይም ጦርነት በተካሄደባቸው እንደ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና አፋር ያሉ ክልሎች ውስጥ ያሉ ወጣቶች በጦርነቱ አካላቸውን አጥተዋል፣ መቶ ሺዎች ሞተዋል፣ ሚሊዮኖች ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል፣ ለከፋም ድህነት ተዳርገዋል፡፡ ለአገዛዝ ሥርአቱ እነዚህ ወጣቶች ልክ እንደ ተጠመደና ሰአቱን እንደሚጠብቅ ፈንጂዎች ናቸው፡፡ በማናቸው ጊዜ የተጠራቀመ ብሶታቸውን ይዘው አደባባይ ከወጡ የሥርአቱ ዘመን ያከትማል፡፡ ስለዚህ እንደ አዶናይ አይነት ወጣቱን በደልህን እርሳ፣ አልተማርኩም ብለህ አትቆዝም፣ ሥራ የለኝም ብለህ፣ እራበኝ ብለህ፣ ትምህርት እድል ተነፈኩኝ ብለህ ከመንግስት ጋር አትጋጭ፡፡ ይልቅስ ድንቁርናህን፣ አለማወቅህን ተጠቅመህ ማናቸውንም አይነት የነውር አድራጎት ሳይቀር በመፈጸም እና እሱንም በድህረ መረቡ እያሰራጨኽ እውቅናን አትርፍ፣ ገንዘብም ሥራ፣ ሰግጥ እያለ ከህጻን እስከ አዋቂ፣ ከወታደር እስከ ምሁር ተከታይ እንዲያፈራ የተደረገው ያለምክንያት እንዳልሆነ ቆም ብሎ ማሰብ የግድ ይላል፡፡ ስገጣ ለአገዛዝ ሥርአቱ ትውልድን የማደንዘዣ ስልት መሆኑን መረዳትም የግድ ይላል፡፡

ለማንኛውም የሰግጥ/ደንቁር፣ እውቅና አግኝና ሃብት አፍራ መፈክር መነሻ ሃሳቡ እውቀት ጠል የሆኑ አንባገነናዊ ሥርአቶች መሆናቸውን መለስ ብሎ የአለም አምባገነኖች ታሪክን ማገላበጥ በቂ ነው፡፡ ዋና ሃሳቡ ከእውቀት ነጻ መሆን ከጭንቀት፣ ለአገራዊ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ ከመዳከርና ከመታገል የሚገላግል እና የከበደውን ህይወታችንን በድንቁርና ማቅለልና በደስታ መሙላት ይቻላል (A lack of knowledge prevents anxiety or concern, making life simpler and happier) ከሚል እሳቤ የሚመነጭ ነው፡፡ በዚህም አያበቃም፤ እውቀት፣ ሳይንስና ምርምር የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የነገውንም ተስፋና አደጋ በማመላከት የሚመጣውንም ዘመን እያሰብክ ዛሬ ላይ እንድትጨነቅና እንድትፈራ ያደርግሃል፡፡ በዛም የተነሳ ደስታህን ታጣለህ። ከሰገጥህና ከደነቆርክ ግን ስለነገ እያሰብክ የዛሬ ደስታህን አታጣም የሚል እሳቤንም ይይዛል።

እንቁርና እና አካባቢያችን ላይ ላሉ እውነታዎች እራስን በማበደን አልሰማም፣ አላይም ብሎ የመሸንገል ስልት (denial) ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው እውነተኛ ያልሆነ ሰላምና ደስታን ይፈጥርልናል፣ ከስጋት ቀጠናም በምናብ ደረጃ ያወጣንና ለላ ምናባዊ የሆነ ሁሉ የሞላበት ሰላም የሰፈነበት የደስታ ቅዠት ውስጥ ይከተናል፡፡ ልክ ስለሚኖሩባት አለም ምንም እውቀት እንደሌላቸውና አካባቢያቸው በአደጋ ተሞልቶም እነሱ በደስታና በጨዋታ እንደተዋጡ ህጻናት ለምንም ነገር ግድ የሌለን ደስተኞች ያስመስለናልም (carefree enjoyment)፡፡ ይህንን ምናባዊ የሚመስል የውሸት ደስታና ፍንጠዛ እንደ መባረክ ቆጥረው የሚሰብኩ አንቂዎች እንደ አሸን እንዲፈሉ ስለሚደረግ በዘመነ ስግጥና ድንቁርና እንደ Blessing ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ሁለተኛው ገጽታ ግን አፍጥጠውና አግጠው የሚታዩ እውነታዎችን እንዳላዩ መምሰል ወይም እንዳልተፈጠሩ መቁጠር ነገሮች እጅግ እየከፉ እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ የብልጽግና ተከፋኝ ከሆኑ ትውልድ አደንዛዥ አነቃቂዎች መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እየተንጎማለለ ጥጋብ ሊያፈነዳቸው የደረሱ ጉንጮቹን በገመጠው ዳቦ ሞልቶ “ኑሮ ተወደደ እያልክ አታማር፡፡ ይልቅስ ተነስና ዳቦ በሙዝ ብላ” እያለ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምክር ሲያስተጋባ ስታይ የአገዛዝ ሥርአቱ የፈጠራቸው አነቃቂዎች እየተጫወቱ ያሉትን የአደንዛዥነት ሚና ቁልጭ ብሎ ታየዋለህ፡፡ ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቱ ከመረጃዎች እንዲርቅ፣ ስለ አገሩ ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ እንዳያውቅ ማድረግ እና የአገሪቱን አንገብጋቢና እጅግ አሳሳቢ ችግሮች እንደገለባ ማቀለል (Downside) አንዱ ስልት ተደርጎ ትንሽ ማወቅ ወይም መደንቆር የደስታ ምንጭ ከመሆንም አልፎ የሃብት መሰላል ተደርጎ እንዲቆጠር ተደርጓል፡፡

ለማንኛውም አንዳንድ ፈላስፎች እንደሚሉት እንኳን ጥልቅ እውቀት ይቅርና በልምድና በህይወት ተመክሮ የሚገኝ እውነተኛ እውቀትና መረጃ (true wisdom) እውነታን ከመጋፈጥ የሚገኝ ሲሆን ዘለቄታ ላለው ደስታም ብቸኛው ምንጭ ማወቅ እንጂ መደንቆርና መሰገጥ አለመሆኑን በማሳሰብ መልዕክቴን ልቋጭ፡፡

መልካም ሰንበት!

Share this post