መልዕክተ ዘማሪ፣ ፉካሬ አዝማሪ

መልዕክተ ዘማሪ፣ ፉካሬ አዝማሪ

ታሪኳ ጌታቸው

እነዛ ቀደምቶች በላባቸው የሚያድሩ፣

ይታደሱ ነበር በህብረት ሲዘምሩ።

መጣር፣ መጋር ሲያርድ፣ ሲተሳሰር ጉልበት፣

ማንጎራጎር ነው ደግ፤ ያነቃል ከድክመት፤

አዝማሪም ዘማች ነው፣ ሲገባ ጦርነት።

ተማሪውም ሲጓዝ እፍኝ ቆሎ ቋጥሮ፣

እየዘገነ ነው ከግጥም ማሰሮ።

ያለአልቃሹ እንባ አይወርድም ኃዘኑ፣

አይፈርስም ድንኳኑ።

ዝምታ ይሰበራል፣ ባንድ ቅኔ ተዓምር፣

በብላቴና ይፈታል የሺ ወርቅ ድርድር።

ቋንቋው ቢፈታተል፣ በቀፎ ቢቋጠር፣

ቢራቆት…… ቢራቆት…….. የማይበርድ የኢትዮጵያ ሚስጥር፣

በሚቀጣጠል ሰም፣ ስብራትን መውገር፤

ፍ____ ብሎ በእፍታ፣ ቅርን ማረግ ፍቅር፣

ማ____ ብሎ በእማማ፣ አገር ማለት ማገር!

በአገር አይደክምም የዘፋኙ ዜማ

ከጃማይካ ሄዶ ያመጣል ለጅማ።

ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ…….የማይገጥም ለቅሶ አይቀርብም ዳኛ ዘንድ፣

ስነግርህ…………………………ጠላትም በቁራኛ ነው ለፍትሕ እሚሰደድ!

ለውይይት ትምህርት ያዘጋጀኧው ሕዝብ፣

ቁጭቱን ዘፍኖታል ሳያበዛ አጀብ!

የትዕግሥት ተመካሪው

ዛፍ ስር መካሪ ነው!

ቼ! ብሎ ባንድ ፊደል ጅማት፤

አስሯል የልቡን ምት!

“ኡኡታ” አቀብሎ ለማያበቃ አብዮት

ኢትዮጵያን ክሕመም ያድናል በጩኧት!

ልጅ እየተማከረ ስም አይወጣም፣

ሲጣራ አባይ ካለ እጅ አይነሳም!

መገጣጠም ቀርቶ በየዱራዱሩ፣

እደጅ ሲያድር ነው፣ የፈረሰው አጥሩ!

ለተሰደደ ቃል ቤት አይመታም ባገሩ!

እንባ አይን አይመርጥም፤

እናት ብትራብም፣ ለሙሾ አታንስም!

በጨው የራሰ አፈር፣ አይደርቅም በሞፈር፣

ቃል በቃል ሲውል ነው ቁስልም የሚሽር!

አንበሳ ሲያጓራ ድምፅ አያባክንም፣

በመላ የማለ ነጋሪት አያውጅም!

በቃል ያረፈ ድንበር በጉራ አይሸበር፤

በብዕር ብቻ ነው እውነት ሚመረመር!

በአዝማሪ ሰላምታ የታተመ ቀለም፣

ቢወድቅ ካፈሩ ነው፣ ያበራል ቢሞትም

በሊቃውንቱ ቀስም!

ሊያደማምቅ እንጂ በብራና ላባ

እሳት አያነድም ክንዱ በገለባ!

በሎሬቱ ቀመር የምትበራው ቀለም፣

የወንዙ ታሪክ ነው የታፈረ በደም።

ይሰቀል ይመስል በድንጋይ አሻራ፣

ይገንጠል ይላሉ ጠጠር ከተራራ!

አራዳ አይዳርግም ወንድም ለኪሳራ፣

በእምነት ሲታተብ ነው ፈጣሪ እሚራራ!

አንገትም ቢቀላ ከጎራዴው ጋራ፣

ፈረስ ቢወዳድቅ በተራ በተራ፣

ሀቅ ይተናነቃል በዘፋኝ ዳንኪራ !

በክብር ይነግሳል ባዝማሪው ፉከራ!

ይነዝራል መልዕክቱ የታላቅ አደራ!

ታሪኳ ጌታቸው (ሐምሌ 27 ቀን 2012፣ ኔዘርላንድ)

ክብር ለአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳ (ቴዲ አፍሮ)

Share this post