ሐዘንሽ አመመኝ- ደበበ ሰይፉ

ሐዘንሽ አመመኝ- ደበበ ሰይፉ

ውል አልነበረንም የፍቅር ቀጠሮ
ቃልም አላኖርንም በወግ ተቀምሮ፤
እኔ አንቺን እንዳላይ
አንቺ እኔን እንዳታይ አምባችን ተቃጽሮ
ዕጣችን ተካሮ፤
ቀለምሽ ከዐይኔ አሻራሽ ከጣቴ ባይጠፋ ተማትሮ
(እትብት እምብርት ሁኖ እንዲኖር ደድሮ)
ይኸው አካሄደን በድንገት ዘንድሮ።

የገጽሽ ብርሃን ቢጠይም ፀዳሉ
ድምፅሽ ቢቀጥንብኝ ቢሠልብኝ ቃሉ
ወዘናሽ ቢማስን ዛሬ ያለውሉ
በእጆችሽ ጨበጠኝ ሐዘንሽ ሥዕሉ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
ጀንበር ነሽ አበባ ሕይወት ተስፋ ዘቦ

ፋሲካ ዕንቁጣጣሽ ማኅሌተ ገንቦ
በዬ ያወደስኩበት ታዘበኝ ዘመኔ የትላንታት ቀኔ ዛሬ ሊጮህብኝ ቅኔ እንዳይደል እውኔ፤

ሐዘንሽ አመመኝ ብሶትሽ ጠቀሰኝ።

የገደል ማሚቶን ታዘብኳት ተኝታ
በጩኽትሽ ማየል አኩርፋና ታክታ
ቃልሽ ያለፈበት በጭንቅ ተለውሶ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
ጽጌሬዳይቱ ንቦችሽ አለቁ ሰዎችሽ ደቀቁ
ጨፌ ላይ ተኝተው ባድማ ላይ ነቁ፤
ዐዋይን ሰማኋት ስታለቅስ በይፋ
ከጐጆሽ ስትወጣ ትቢያዋን አራግፋ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።

አላውቅልሽ ብዬ አታውቂልኝ ብዬ
እምነትሽን ጥዬ ፍቅርሽን ገድዬ
አኩርፌሽ ስቀመጥ ያው እንደ ባላንጣ
ይኸው ነጭ ማተብሽ ሊያስታርቀን መጣ፤
ሐዘን ነው ውበትሽ ውበት ነው ፍቅርሽ
ብርሃን – ጥለት አልቦ ከል ነጠላሽ
ዐይኔን የገለጠው ጥቁር ጨለማሽ፤…

ሐዘንሽ አመመኝ ብሶትሽ ጠቀሰኝ።

ግንቦት 1966 ዓ.ም.

(ደበበ ሰይፉ፣ የብርሀን ፍቅር፣ ገጽ 62-3)

.

Share this post