ከአሜሪካውያን ዘንድ ለእስራኤል የነበረው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸው ኔታንያሁ ገለፁ።

ከአሜሪካውያን ዘንድ ለእስራኤል የነበረው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸው ኔታንያሁ ገለፁ።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ለሀገራቸው የነበረው ድጋፍ በአሜሪካውያን ዘንድ እየቀነሰ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸው ገለፁ።ኔታንያሁ ከዚህ ቀደም በአሜሪካና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት እንደ ግራናይት ድንጋይ ግድግዳ የጸና ቢሆንም፣ አንዳንዶች ስንጣቂ ለማግኘት የሚሞክሩ አሉ ብለው ነበር።

በቅርቡ የተደረጉ የሕዝብ አስተያየት ጥናቶች በአሜሪካውያን ዘንድ ለእስራኤል የነበረው ድጋፍ መቀነሱን አመልክተዋል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወደ ዋሽንግተን ያመሩት ኔታንያሁ፣ ኤቢሲ ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ አሉታዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች መበርከት ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንዳንድ መንግሥታት የተደራጀ ዘመቻ በቦት መረቦች (bot farms) ፀረ-እስራኤል አቋሞች እንደሚሰራጭ ተናግረዋል። “በእነዚህ የማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን መልዕክቶች መስፋፋትና ለእስራኤል ያለው ድጋፍ መቀነስ መካከል ቀጥተኛ ተያያዥነት እንዳለ እያየን ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። “በጋዛ ያለው ጦርነት፣ እዚህ በተሳሳተ መንገድ የቀረበበት ሁኔታ እና የተሰራጩት የተሳሳቱ መረጃዎች አስተዋጽኦ አላደረጉም እያልኩ አይደለም” በማለት አክለዋል። “ለማለት እየሞከርኩ ያለሁት፣ አሜሪካን የሚጠሉ እስራኤልንም ይጠላሉ። እስራኤልን የሚጠሉ አሜሪካንን ይጠላሉ።ይህ የተከፈተብን ሰፊ ውጊያ አካል ነው” ብለዋል።

ጋዜጠኛዋ፣ የዘር ማጥፋት ጥናት ባለሙያዎችንና የተባበሩት መንግሥታትን ሪፖርቶች በመጥቀስ፣ እስራኤል በጋዛ የጦር ወንጀል መፈፀሟ አስተዋጽኦ አድርጎ ቢሆንስ ስትላቸው፣ “ይህ ሐሰት ነው ብዬ አምናለሁ።”የዘር ማጥፋት ነው” ይላሉ፤ እሺ። ግን በመጀመሪያ ይህን ክስ የሚያቀርበው ማን ነው? የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ነው። የዘር ማጥፋት ማለት አንድን ሕዝብ ለማጥፋት ማለም፣ ይህንን ለመፈፀም ዕቅድ ማዘጋጀት እና በዚያ ዓላማ መሠረት የሚፈጸሙ ተግባራትን ያካትታል።ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጽሑፍ መልዕክቶችንና የስልክ ጥሪዎችን በማድረግ፣ የፍልስጤም ሲቪሎች ከጉዳት አካባቢዎች እንዲርቁ አሳስበናል። በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተደብቀው የነበሩትን የሃማስ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ እንዲቻል።የዘር ማጥፋት ዓላማ ካለን፣ ያንን ለምን አደረግን? “ሲሉ ጠይቀዋል።

ኔታንያሁ ወደ ዋሽንግተን የመጡት ባለፈው ሳምንት ሕይወታቸው ያለፈው ሪፐብሊካን የኮንግረስ አባል ሊንዚ ግርሃም ቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው። የትራምፕ የቅርብ አጋር የነበሩት የኮንግረስ አባሉ ሊንዚ ግርሃም፣ የእስራኤል ቀንደኛ ደጋፊ ነበሩ። የእስራኤሉ መሪ ከኤቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የኒው ዮርኩን ከንቲባ  ዞህራን ማምዳኒን፣  “ጥላቻ በመቀስቀስ” ወንጅለዋል።

አሜሪካ ለእስራኤል ዋነኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢ ስትሆን የእስራኤል ጦር በጋዛ በሚያደርገው የተቀናጀ ጥቃት ከአሜሪካ የሚደርሰውን የጦር አውሮፕላኖች፣ ሚሳኤሎች እና ሌሎች መሳሪያዎችን ይዞ ነው።

በቃለ መጠይቁ ኔታንያሁ፣ ትራምፕ ከኢራን ጋር ወደ ጦርነት እንዲገቡ የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ እና በቀላሉ ድል እንደሚገኝ ቃል በመግባት አሳስተውታል የሚለውን ክስ አስተባብለዋል። ኔታንያሁ ደጋግሞዉ የፎከሩት የኢራንን ሥርዓት የመቀየር ወይም የኢራንን ሕዝብ በአያቶላሆቹ ሥርዓት ላይ የማሳመፅ ዕቅድ ባይሳካም ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመጠቀም በዓለም የነዳጅ ዋጋ ገበያ ላይ ጫና የማሳደር ብቃቷ እንደሚዳከም ገልጸዋል።ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚመነጨውን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ በአረብያን ፔንኑስላ አቋርጦ ወደ እስራኤል ወደቦች የሚደርሱ የነዳጅና የጋዝ ቧንቧዎች በመገንባት፣ የሆርሙዝን ወሽመጥን ሳይጠቀሙ ሊጓጓዙ እንደሚችሉ፣ ይህም ኢራን በሆርሙዝ መስመሮች ላይ የበላይነት ለማግኘት የምታደርገውን ሙከራ ለመግታት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

Share this post

Post Comment