የከረመ ፈረስ

የከረመ ፈረስ

በማር መጥተውባት፣ መሯት። ንቢት ንዴት አሳብዷት ቀፎዋን ጥላ ቱር አለች። በመስኮት ገብታ የአቶቡሱን ሾፌር አፍንጫው ላይ ነደፈችው። ሾፌር አፍንጫው ከምኔው ረዛዝሞ ዐይኑን ሲያጥበረብረው። መርዙ እ ንደ እልህ እንደ ቂም እንደ ጥላቻ እንደ አጋንንት ሳቅ ተሠራጭቶ እንደ እብድ እንደ ሰካራም ሲያደርገው። እንጦርጦስ እንደሚወርድ ተሳፋሪ ይዞ ሲምዘገዘግ። ከመንገድ ወጥቶ፣ ሙቶ የከረመ ፈረስ ጨፍልቆ በስንት የአሣር ተኣምር እርሱም መንገደኛውም ተረፉ።

የፈረሱ አሟሟት። ማገዶ በጋሪ ሠፈር ለሠፈር እየጎተተ ሲያቀርብ። ከባለቤቱ አስበልጦ ሠፈርተኛ ሲያደንቀውና ሲያፈቅረው፤ ልጅና አዋቂ ፊት አንገቱን እየደባበሰ “ደንበል፣ ደንበኛ” እያለ ሲያቆላምጠው። ከማን ቤት ሲደርስ በራሱ አውቆ ሲቆም፤ በራሱ አውቆ ወደሚቀጥለው ሲጓዝ። አስቤዛ ማገዶ ሲያራግፍ፤ ሲያግዝ ሲያጋግዝ ሲጓዝ። የረሃብ ዘመን መጣ። ማገዶ የሚገዛ ታጣ። እህል ሳይኖር ማገዶ፣ ጠኔ ጣዕርና በደል ለማንደድ ካልሆነ ለምን ፈይዶ? ደንበል ጒዞው ተራዘመበት፤ የሚያናግረው የሚደባብሰው እጅ አጠረበት። በፊተኛው ግራ እግሩ ማንከስ ጀመረ። ወለምታ ይሆናል ብለው የፊየል ሞራ ቀብተው አምቾ ከሥር ጎዝጒዘው በቀርቅሃ ጠፍረው አሠሩለት። ባሰበት። ተጋድሞ አልነሳ አለ። እግሩ ያበጠው በወለምታ ሳይሆን፣ ሳያውቊለት ቀርተው እሾክ ገብቶ መግል ቋጥሮ ተልቶ። ሐሙስ ሌሊት ሙቶ አደረ። ዐርብ ቀትር ላይ፣ አልጋ አንጣፊው ከዲር ተፈልጎ ተጠራ። ብር ከአላድ ተከፍሎት ጎትቶ እዚያ ጋ አጋደመው። ከዲር ከሄደበት ሲመለስ ግርግሩን፣ አውቶቡሱ ያደረሰውን ተመለከተ። ከባለ ፈረስ ጋር ተስማምተው ክስ መሠረቱ።

© 2021 by Mitiku Adisu. All Rights Reserved. ምትኩ አዲሱ፣ 2010 ዓ.ም.፤ ኲኲሉ በምሽት፣ ገጽ 47-48

Share this post