የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊትም፣ ሆነ ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ አውሮፓን ያለማቋረጥ በስድብ ይወርፋሉ። ትራምፕ የአውሮፓ ሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገሮች ድርሻቸውን የማይከፍሉ ወሮበሎች (delinquent) እስከማለት ደርሰዋል። በተጨማሪም የአውሮፓ አገሮች ብዙ ስደተኞችን የሚቀበሉና የፍልሰተኞችን ሁኔታ መቆጣጠር ያቃታቸው ዳተኝ አገሮች በማለት በተደጋጋሚ ይተቿቸዋል። የትራምፕ አሜሪካና MAGA ተከታዮቹ ከአውሮፓ ጋር ያለባቸው ችግር ምንድነው?
አሜሪካና አውሮፓ ጠንካራ ትስስር ያላቸው የቅርብ አጋሮች እንደሆኑ ነው የሚታወቀው። አሜሪካ በሃያኛው ክፍለ ዘመን አብዛኛውን ዓመታት የምዕራቡ ዓለም መሪና መካች የመሆን ሚናን ስትጫወት ነበር። ከ2ኛ የዓለም ጦርነት በኋላ የሶቭየት ሕብረት ርዕዮተዓለም መንሰራፋትና ተጽእኖ መበራከት ያሳሰባት ጀመር፤ ሁኔታው ወዴት ያመራል በሚል ስጋትም በቅርበት ትከታተለው ነበር። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም የምዕራቡን ዓለም የመምራት አስፈላጊነት ተገንዝባና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ለአውሮፓ የደቀነውን ስጋት በመረዳት፤ አሜሪካ በግምባር ቀደምትነት ስትጋፈጥ ቆይታለች።
አሜሪካና አውሮፓ በታሪካቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ይስማማሉ ማለት አይደለም። አሜሪካ በ2003 ኢራቅን በወረረችበት ጊዜ፣ ለምሳሌ ፈረንሳይ ተቃውሞዋን አሰምታ ነበር።ይህ አሜሪካኖችንን በጣም አበሳጭቶአቸው እንደነበር ይታወሳል።
የሁለቱ አህጉሮች ዋነኛ የግጭት መንስኤ ግን የአውሮፓ የመከላከያ ወጪ አነስተኛ መሆን ነው።አሜሪካኖች የአውሮፓን ደህነነት ለማስጣበቅ የምንከፍለው እኛ ነን ይላሉ።የአውሮፓ ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እያደረጉ እንዳልሆነና ለድርጅቱ የሚያደርጉትን መዋጮ እንዲያሳድጉም ደጋግመው ይናገራሉ። ይህ የቆየ ክስ ነው። ከትራምፕ በፊት የነበሩ ሌሎች የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችም ተመሳሳይ አቋም ያንፀባርቁ ነበር። ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ይህን ጉዳይ ያነሱት በ1960ዎቹ ነበር። ከ50 ዓመታት በኋላ፣ በ2011፣ በባራክ ኦባማ አስተዳደር የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ሮበርት ጌትስ፣ የኔቶ አባል አገራት የመከላከያ ወጪያቸውን ካልጨመሩ የወደፉቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ጆ ባይደን ይህንን አቋም ማንፀባረቃቸውን ቀጥለበታል።
ያም ሆኖ ግን የትራምፕ የቅርብ ሰዎች፣ ለአውሮፓ ያላቸው ጥላቻ ከፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ስምምነቶች እና የኢኮኖሚ ሽርክናዎችን የዘለለ ይመስላል።የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ለወግ አጥባቂ እሴቶች ትኩረት መስጠት ከአውሮፓ ሊበራል ፖሊሲ የሚቃረን መሆኑ። የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ጄዲ ቫንስ የካቲት 2025 በጀርመኗ ሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አብዛኛዎቹ የአውሮፓ መንግሥታት ከእሴቶቻቸው አፈግፍገዋል፤ እንዲሁም የመራጮችን ስጋት ገሸሽ አድርገው በስደት እና በመናገር ነጻነት ላይ ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራትን ችላ ብለዋል ብለዋቸዋል።እንደ ሶርያ እና አፍጋኒስታን ካሉ አገሮች በጣም በርካታ ስደተኞችን መቀበላቸውን ተችተዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው በባህል ጦርነቶች ላይ እንዲሁም ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ባነሷቸው “ቅድሚያ ለአሜሪካ” ጭብጦች ላይ አትኩረዋል።የትራምፕ አሜሪካ ቀኝ ዘመም አስተሳሰብን ከሚያራምዱ ከአርጀንቲና፣ ሃንጋሪ፣ እና ጣሊያን መሪዎች ጠንካራ ወዳጅነት መሥርተዋል።

ትራምፕ በዳቮስ፣ ስዊዘርላንድ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር። “From the standpoint of America, the EU treats us very, very unfairly, very badly,” (ከአሜሪካ አንፃር፣ የአውሮፓ ኅብረት እጅግ አለአግባብ፣ እጅግ ክፉኛ አድርጐ ነው የሚይዘን፡) ብለዋል። ትራምፕ ከአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ 50 በመቶ ታሪፍ ሊጥሉ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል፡፡ዋሽንግተንና አውሮፓ ኅብረት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ፣ ፍልስጤም ጉዳይ፣ በዩክሬን እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ አውዳሚ ጦርነቶች፣ በተባበሩት መንግሥታት ሚና የተለያዩ አቋም አላቸው፡፡አሜሪካውያን የአውሮፓ አገሮች ለጋስ ዌልፌር ሥርዓት ቢኖራቸውም የደህንነት ጉዳዮች ሥራና ኃላፊነት በአሜሪካ ትከሻ ላይ የወደቀ ነው በማለት ያማራሉ። ይህንን የአሜሪካኖች ስሜት በአንድ የኢኮኖሚስት ጋዜጠኛ እንዲህ በማለት ነበር የተገለፀው። “Europe is like an ungrateful teenager — we pay for their rent, we insure their car, and they turn around and tell us how much they hate us.”
አውሮፓውያን ነገሩን የሚመለከቱበት በሌላ መንገድ ነው።አሜሪካውያን ታሪካቸውን እየረሱ መሆናቸው ግርምትን ፈጥሮባቸዋል።ከ1945 በኋላ አውሮፓውያን የኢኮኖሚ ጥምረት በመፍጠር ወደ አንድነት እንዲያመሩ ያበረታታችው አሜሪካ ነበረች። አህጉሪቱ ከበለፀገች ኮሚኒዝምና የአክራሪ ቀኝ ፖለቲካ እንዳይስፋፋ ይከላከላል በሚል ተስፋ። የአውሮፓ መንግሥታት ምጣኔ ሀብታቸውን፣ ማህበረሰቦቻቸውን እና ዴሞክራሲያቸውን የሚመሩበት መንገድ የትራምፕን አስተዳደር በጣም ያናደደው ይመስላል። ያ ማለት ቀደም ሲል አሜሪካ ታራምደው የነበረውን ስርዐት እርግፍ አርጋ መተዎን ያሳያል ሲሉ ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ላይ የጂኦፖሊቲክስ አዘጋጅ የሆኑት ዴቪድ ሬኒ ይገልፃሉ።ይህ ሁኔታ ለአውሮፓ ጥሩ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ይህ አቋም የአሜሪካ መንግሥት በዓለም አቀፍ ጉዳይ ላይ የሚያንፀባርቀው መሆኑ ብቻ ሳይሆን የዛሬዋ አሜሪካ ጥግ በረገጠ በሁለት ፅንፎች የተወጠረ መሆኑ ነው።