የሲአይኤ መጽሐፍ ክለብ

የሲአይኤ መጽሐፍ ክለብ

በ1950 በፈረንሳይ በስደት ይኖር የነበረው ፖላንዳዊ ጄርዚ ጊድሮይክ ሥነ ጽሑፋዊ ዳሰሳ የሚያደርግ መፅሔት ማሣተም ጀምሮ ነበር።ግን ወጪውን አልቻለውም። በተወሰነ መልኩ፥ የመፅሔቱ አላማ፥ ሀገሩ ፖላንድ ከወደቀችበት የኮሚኒስት ቀንበር ነፃ ማውጣት ነበር። በፈረንሳይ አገር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት አስቸጋሪ ሆነበት።ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፥ በፓሪስ ከተማ የሚኖሩት፥ የፖላንድ ዜጎች ለራሳቸው በድህነት የሚማቅቁ ነበሩ።የፈረንሳይ ምሁራን ደግሞ ከሶቭየት ሕብረት ጋር በፍቅር ተነክፈው ነበር።ስለዚህም ጊድሮይክ ማንም ሊያደርገው እንደሚችለው ሁሉ ፤ የአሜሪካኖችን በር አንኳኳ። ምላሹን ያገኘው ካልተጠበቀ አካል ነው።ከአሜሪካ የስለላ ተቋም!

የሲአይኤ አባላት ኩልቱራ የተባለውን መጽሔቱ ለመደገፍ በዓመት 10,000 ዶላር ለመስጠት ተስማሙ።ይህ ወደ አርባ ዓመታት የቆየ የጋራ ትብብር ሀ ብሎ የጀመረበት ነበር ይለናል በቅርቡ ለንባብ የበቃው የቻርሊ ኢንግሊሽ መጽሐፍ የሲአይኤ መጽሐፍ ክለብ (The CIA Book Club)። ፓሪስ ላይ መቀመጫውን ያደረገው፥ ኩልቱራ በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የሀገሪቱ ዜጐች ዋንኛ የመረጃ ምንጭና ሀሳብ መለዋወጫ መድረክ ሆነ።የሶቪየት ሕብረት ሳንሱርን ለማዳከም ቀንና ሌሊት ይሰራ የነበረው ሲ አይ ኤ በፈረንሳይም ሆነ በሌሎች ሀገሮች የሚገኙ ሌሎች ፖላንዳውያን አሳታሚዎችንና የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮችን መደገፍ ጀመረ፡ይህን ተልዕኮውን በማስፋፋት፥ ሲ አይ ኤ በድብቅ ወደ ፖላንድ መጻሕፍት ለሚያስገቡ አሳታሚዎች የገንዘብ ልገሳ ማድረግ ጀመረ። እንዳይነበቡ ማዕቀብ የተጣለባቸው መጻሕፍት በስፋት እንዲሰራጩ በድብቅ፥ በሻንጣ ውስጥ፥ በልብስ ተሠግስገው፥ በመኪና ሞተር ተደርድረው እንዲሁም በባቡር መፀዳጃ ቤቶች ጣራ ላይ ተንጠልጥለው ወደ ሀገሪቱ ይላኩ ነበር። መጻሕፍቶቹ ብዙ ዓይነት ነበሩ።የጆርጅ ኦርዌል “የእንስሳት እድር” (Animal Farm) እና (1984) የተሰኙት በርካታ አንባቢዎችን አግኝተዋል።ሌሎች ታግደው በድብቅ ይገቡ ከነበሩ መጻሕፍት መካከል የአሌክሳንደር ሶልዠኒትሲን “The Gulag Archipelago”፣ የኦልደስ ሃክስሌ “Brave New World” ፣ የቦሪስ ፓስተርናክ “ዶክተር ሺቫጐ” (Doctor Zhivago) እና የጆን ለ ካሬ (John le Carré) ና የሐና አረንት (Hannah Arendt) ስራዎች ይገኙበታል። አንዳንዶቹ መፅሓፍት፥ የተከለከሉት በግልፅ፥የኮሚኒዝምን ስርዐት ስለሚያወግዙ ሲሆን ገሚሶቹ ግን በቀጥታ ምንም አይነት ግንኙነት አልነበራቸውም።የማርጋሬት ሚቼል “ነገም ሌላ ቀን ነው” (Gone with the wind) የተሰኘው መፅሀፍ ከተከለከሉት አንዱ ነበር።በ1980ዎቹ የሲ አይ ኤ የገንዘብ ድጋፍ በፖላንድ በሕቡዕ መጻሕፍትንና መጽሔቶችን እንዲታተሙ ወሳኙን ሚና ተጫውቷል።በተጨማሪም የማተሚያ ማሽኖችን በመግዛት በማቀዝቀዣ መኪናዎች ውስጥ ተደብቀው ወደ አገር እንዲገቡ ያደርግ ነበር።ቀለም ሳይቀር በምግብ ቆርቆሮዎች ታሽጐ ይላክ ነበር። ምንም እንኳ ጊድሮይክ በፖላንድ ምሁራን ዘንድ ገናና ስም ያለው ቢሆንም ከሲ አይ ኤ ጋር የነበረው ግኑኝነት እምብዛም አይታወቅም።በጊዜው (QRBERETTA) የተባለ የሲ አይ ኤ ኮድ ስም እንደነበረው መጠቀሱ ፖላንድ ውስጥ በጣም ግርምትን ፈጥሮአል።ጊድሮይክ ይደግፋቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል ዊቶልድ ጎምብሮቪች (Witold Gombrowicz) የተባለው ጸሐፊ ይገኝበታል። በቦነስ አይረስ የባንክ ሥራ እየሠራ የሥነፅሑፍ ችሎታውን ማውጣት ያልቻለ።በኋላ ላይ በርካታ መጻሕፍትን ጽፏል። በአውሮፓ ዘመናዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ የሚጠቀሰውን Diary የተባለ ድርሰት እንዲፈጥር አስችሎታል። ሌላው ለኩልቱራ መጽሔት ጽሁፎችን ያበረክት የነበረው ቼስላቭ ሚልዎሽ (Czesław Miłosz) በሥነ ጽሑፍ የኖቤል የሽልማት ተሸላሚ እስከ መሆን ደርሷል።

የየሲአይኤ መጽሐፍ ክለብ (The CIA Book Club) ፀሐፉ ቻርሊ ኢንግሊሽ (Charlie English) የቀድሞ የጋርዲያን ጋዜጠኛ የነበረ ሲሆን፣ እንደ ስለላ ልብ ወለድ አድርጐ በመተረክ፥ በሲ አይ ኤ የአውሮፓ ነፃ ፕሬስ መጽሐፍ ማዕከል (Free Europe Press Book Center) ቢሮ ያስተዳድር የነበረውን ጆርጅ ሚንደን የተባለ አሪስቶክራት ያስተዋውቀናል። ጆርጅ ሚንደን ‘እውነት እንደተላላፊ በሽታ ይጋባል’ የሚል እምነት የነበረው ሲሆን፤ ጽሑፎች የሶቪየቶችን አፈናና ጭቆና መቋቋም እንደሚችሉ ያምን ነበር። በሲአይኤ ሚስጥራዊ ተልዕኮ፥ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት፥ 260,000 ቀለል ያለ ክብደት ያላቸው “የእንስሳት እድር” (Animal Farm) ቅጂዎች በፊኛ (ባሉኖች) ተጭነው ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ተልከዋል ። ሲ አይ ኤ የጆርጅ ኦርዌልን ስራዎች በሰፊው አሰራጭቷል ። ይሁን እንጂ ጆርጅ ሚንደን በምዕራብ የሚታተሙ ሳምንታዊ የአኗኗር ዘይቤ መጽሔቶች ሳይቀር Marie Claire ወይም Life እንዲላኩ ያደርግ ነበር ፤ ነፃነት በሰፈነበት ኅብረተሰብ ውስጥ መኖር ያለውን ጥቅሞ “በምርኮ ለተያዙ ሀገራት” ለማሣየት በሚል። መጽሐፍቱና መጽሔቶቹ አገሪቱ ውስጥ ከገቡ በሓላ፥ አንባቢዎች ከአንዱ ወደ አንዱ በመዋዋስ በተቻለ መጠን ለብዙ ሰው ያሰራጭዋው ነበር። የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከመጽሐፍ ክለቡ ጋር ቁርኝት ያላቸውን የዜና አውታሮች ራዲዮ ፍሪ አውሮፓን (Radio Free Europe)ና ቪኦኤን ባፈረሰበት ወቅት ይህንን መጽሐፍ ማንበብ በጉዱዩ ላይ ውይይትን ለመፍጠር ያግዛል።

The CIA Book Club: The Best Kept Secret of the Cold War by Charlie English William Collins £25, 384 pages

Share this post