የደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ”

የደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ”

ከመስፍን ወልደ ማርያም

(ይህ መጽሐፍ ግምገማ የተፃፈው ከዛሬ 54 ዓመት በፊት ሲሆን ታትሞ የቀረበው “ውይይት” ተብሎ ይታወቅ በነበረው በኢትዮጵውያን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር የሚታተም መጽሔት ቁጥር ሁለት ላይ ነበር።ፀሐፊው ነፍሰሄር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ ዲፖርትመንት መምህርና የክፍሉ ኃላፊም ነበሩ።የገመገሙት መፅሐፍ «የታሪክ ማስታወሻ» ለመጀመርያ ጊዜ ታትሞ የወጣው 1962 ሲሆን በዘመኑ በነበሩት የሚዲያ ህትመቶች አድናቆትን ያገኘ ሲሆን እስካሁንም ድረስ ብዙ የሚነበብና በማጠቀሻነት የሚቀርብ መፅሐፍ ነው።)

ደጃዝማች ከበደ ተሰማ የጻፉት «የታሪክ ማስታወሻ» የሚል 500 ገጾች ያሉት መጽሐፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በነፕሮፌሰር አፈወርቅና በነነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ተጀምሮ የነበረውን አዲስ የታሪክ አጻጻፍ የሚከተል ነው ለማለት ይቻላል፤ እንዲያውም ስሜትን በማስወገድና ቅዝቅዝ ባለ መንገድ ድርጊትን ብቻ በመግለጽ ደጃዝማች ከበደ ልዩ ችሎታ አላቸው፤ ልዩ ደረጃም ፈጥረዋል ለማለት ይቻላል ።
ሽማግሌው ደጃዝማች በ 1894 ዓ.ም ተወልደው ፤ በሁለት ዓመታቸው አያታቸው አዛዥ ተሰማ ከመንዝና ይፋት ወደ አዲስ አበባ አምጥተዋቸው ፤ ከአምስት እስከ ስምንት ዓመታቸው በአጼ ምኒልክ ግቢ ውስጥ አማርኛ ሲማሩ ቆይተዋል ። ግን በልጅነታቸውም ዝንባሌአቸው ወደ ነፍጠኛነቱ ስለነበረ አያታቸውን የእናታቸውን አባት አስመርረው ወደ አባታቸው አባት ኤፍራታ ተላኩ። ከዚያም ወደ አክስታቸው ተልከው እዚያ እንደምንም ዳዊት ደገሙና በ1907 ዓ.ም እንደገና ወደ አዲስ አበባ መጡ ። ወዲያውም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው የአውሮፓን ፊደል መቁጠር ጀመሩና ተውት ። ምክንያቱም በዚያን ዘመን በቤተ መንግሥት ከማደግ የበለጠ ትምህርት የለም ተብሎ ይታመን ስለ ነበረ ነው። አስተዋይ አእምሮና ታዛቢ ኅሊና ያለው ሰው በመሪዎቹ አጠገብ ሆኖ ትግሉን ፤ ክርክሩን ፤ ሙግቱንና ውሳኔውን በማዳመጥ ግሩም የሆነ የኑሮ ትምህርት ለማግኘት ይችል ነበር። በዐሥራ ሦስት ዓመታቸው በጽሕፈት ሚኒስቴር ውስጥ የጸሓፊነት ሥራ አገኙ ። በ1909 ዓ.ም በዐሥራ አምስት ዓመታቸው በንግሥት ዘውዲቱ ቤተ መንግሥት የእልፍኝ አሽከር ሆኑ ።
ከልጅነታቸው ጀምረው እስካሁን ድረስ ፤ በአጼ ምኒልክ ፤ በልጅ ኢያሱ ፤ በንግሥት ዘውዲቱና በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመናተ መንግሥት የሆነውን ሁሉ ከውስጥና ከቅርብ ለማየትና ለመረዳት ሙሉ ዕድል ነበራቸው ።
ኢትዮጵያ የተረት አገር ነች ፤ ከተረቶቻችንም አንዱ ማን ያርዳ? የቀበረ፤ ማን ይናገር? የነበረ ፤ ይላል ። «የታሪክ ማስታወሻ» ከ1907 ዓ ም ግድም ጀምሮ እስከ 1933 ዓ ም ግድም በኢትዮጵያ ላይ የደረሱትን ዋና ዋና ችግሮች ለመግለጽ የተጻፈ ነው ። በጣም ግሩም የሆነ ሙከራ ነው ። ታሪካችንን ፤ ባህላችንን ፤ ቋንቋችንን ፤ ሁለንተናችንንም የምንማረው «እግዚአብሔር እጆቹን ታጥቦ ከፈጠራቸው ነጮች» በሆነበትና የኢትዮጵያ ልጆች ዝብርቅርቁ በወጣባቸው ፤ በራሳቸውና በአባቶቻቸው የአላቸው እምነት በተሟጠጠበት ዘመን የደጃዝማች ከበደ መጽሐፍ የጮራ ፍንጣቂ ይሆናል ። ፍጹም ባዶ አለመሆናችንንም ያስረዳል ።

በኢትዮጵያችን እውነተኛነት ብርቅ ጠባይ ነው።ደጃዝማች ከበደ «የታሪክ ማስታወሻ»ን የጻፉት ከልባቸው እንደሆነና እውነቱንም እንደሚናገሩ አጻጻፋቸው ይመሰክራል ።ሆኖም ብዙ የቀረ ነገር እንዳለ ለመገመት አንባቢውን አያዳግተውም ። እንዲያውም መጽሐፉን አንብበው ከጨረሱ በኋላ ከአንባቢው አእምሮ የሚፈልቁት ብዙ ጥያቄዎች የተነበበው መግቢያው ወይም መቅድሙ እንጂ ዋናው ታሪክ እንዳልተጀመረ የሚያስመስሉ ናቸው ። ምናልባትም ደራሲው ራሳቸው ይህ ስሜት ሳያድርባቸው አልቀረም ፤ ወይም ይህ ስሜት የተሰማው አንባቢ ሳይገልጽላቸው አልቀረም ይሆናል ። በመግቢያቸው መጨረሻ ላይ «ለምን ሙሉ ታሪክ አልሆነም የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ከዚህ በበለጠ ለመጻፍ ባለመቻሌ መሆኑን በትህትና እገልጣለሁ ።» ብለዋል።
«ባለመቻሌ» ሲሉ ሁሉንም ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ማለታቸው ይሆናል እንጂ የማስተዋል ፤ የመገመት ፤ ድርጊትን የመግለጽ ችሎታቸውንማ አሳይተዋል ። ስለዚህም የቀረውን ለመጻፍ ጊዜና ሁናቴው እስቲያስችላቸው መጠበቅ አለብን ።
የታሪክ ማስታወሻ ሦስት መልእክትን የያዘ ነው ለማለት ይቻላል 1ኛ) ከአጼ ምኒልክ እስከማይጨው ጦርነት የነበረውን አጭር የውስጥ ትግል ታሪክ የሚገልጽ ነው ። 2ኛ) ከማይጨው እስከ ጃንሆይ መመለስ የነበረውን ችግርና የአርበኞችንና የስደተኞችን ንቅናቄ የሚገልጽ ነው ። 3ኛ) ደጃዝማች ከበደ እስካሁን ድረስ ያዩትንና የሰሙትን በማጠቃለል ለኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል
ያላቸውን ሥጋትና ምክር የሚገልጽ ነው። እነዚህን አንድ ባንድ እንመልከታቸው።
1ኛ ፤ ከአጼ ምኒልክ እስከማይጨው ፦ ስለአጼ ምኒልክ ዘመን ምንም ያህል የተነገረ የለም። ሆኖም ስለአንዳንድ የአጼ ምኒልክ ሹማምንት አጫጭር መግለጫዎች ሰጥተውናል ። እንዲሁም ንግሥት ዘውዲቱ የወረሱት አስተዳደር እንዴት ያለ እንደነበረ ትንሽ ፍንጭ ለማግኘት ይቻላል። ስለቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ መኳንንትና ከላይም ከታችም ስለነበረው የሥልጣን ትግል የተጻፈው በትንሹም ቢሆን ከዚያ ወዲህ በተፈጠረው ትውልድ ላይ ልዩ አስተያየትን የሚያሳድሩ ሳይሆኑ አይቀሩም ።ለምሳሌ ስለደጃዝማች ባልቻና ስለደጃዝማች አባውቃው የተጻፈው የሚያስገርም ነው። ስለደጃዝማች ባልቻ ደራሲው የጻፉትን ብቻ ያነበበ (ከሌላ ምንጭ ማስረጃ ሳያስፈልግ) የባልቻን መሠረታዊ ትልቅነትና ልበ ሙሉነት በቀላሉ መረዳት ይችላል ። ደራሲው ድርጊቱን ሁሉ በተቻላቸው እውነተኛነት ከገለጹ በኋላ «መቼውንም ቢሆን ትዕቢት ከልባቸው ያልጠፋላቸው ሽማግሌው ደጃዝማች» በማለት የግል አስተያየታቸውን ሲሰጡ አንባቢው ላይስማማቸው ይችላል ።በኩራትና በትዕቢት፤ በፍርሃትና በትዕግሥት ፤ በትሕትናና በውርደት መሀከል ያለው ልዩነት በጣም ረቂቅና ጠባብ ነው። ግን ይህን ያህል አያሳስትም ።በአደባባይ መሀከል ቅሬታቸውን ለማሳየት የሚያስደፍር ሃይማኖትና ኩራት ያላቸው ደጃዝማች አራት ዓመታት ያህል ክብር የሌለው ሁሉ ክብራቸውን ሲገፍባቸው ከሞከረ በኋላ ድንጋይ ተሸክመው ይቅርታ ቢጠይቁም ኩራታቸው እንዳልተሟጠጠ የዚያን ጊዜ ንግግራቸውና በኋላም ከግዞት ወደአርበኛነት መግባታቸው በቂ ምስክር ነው ። ደጃዝማች ባልቻ ተራ ሰው አልነበሩም ።

ደጃዝማች አባውቃው ሌላ ዓይነት ሰው ነበሩ። ቆራጥ፣ ጎበዝና ታማኝ ሎሌ ነበሩ ።ለመዋጋት የተዘጋጁት በኋላም የተጋዙት ለራሳቸው ክብር ሳይሆን የእመቤታቸው የንግሥት ዘውዲቱ ክብር የተነካ መስሎአቸው ነበር ። ለጣልያንም ያደሩት የራሳቸው ክብር እንዳልተነካ ስለተሰማቸው ሳይሆን አልቀረም ። ቢሆንም ቆራጥነታቸውና ታማኝነታቸው ጉልህ ሆነው ይታያሉ ። የሚያሳዝነው እንደፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ያሉ ታላላቅ ሰዎች በጥቅሻ ብቻ መታለፋቸው ነው። ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በጊዜአቸው የነበረውን የሥልጣን ትግል ሚዛን ወደፈለጉበት ለማጋደል የሚችሉ ከባድ ሰው እንደነበሩ ይተረካል ። ስለእሳቸው ባጭሩም ቢሆን ለማወቅ ብንችል ትልቅ ትምህርት ነበር ፤ ይህንን ተነፍገናል።
በዚህ የመጽሐፉ መጀመሪያ ክፍል ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ድርጊቶች ተገልጸዋል ። አንደኛ በገጽ 32 የሚከተለው ተጽፎአል ፡—
«በ1909 ዓ ም መስከረም 17 ቀን ሕዝብ ተሰብስቦ አቤቶ ኢያሱን ሽሮ ከመንግሥት ባስወጣቸው ጊዜ ወይዘሮ ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው የአባታቸውን የዳግማዊ ምኒልክን ዙፋን እንዲወርሱ እንዲሁም ደግሞ የሐረሩ ገዢ የልዑል ራስ መኰንን ልጅ ደጃዝማች ተፈሪ መኰንን ራስ ተብለው አልጋ ወራሽና እንደራሴ እንዲሆኑና የመንግሥቱን ሥራ እንዲፈጽሙ የሕዝቡ ጉባኤ ወሰነ።»

እኛ በኋላ የተፈጠርነው ሰዎች ሳንጠይቅ የማናልፈው ደራሲው «ሕዝብ ተሰብስቦ» ሲሉ «የሕዝቡ ጉባኤ» ሲሉ «በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ» ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ያን ጊዜ የምክር ቤት አልነበረም፤ ሕዝቡ የመረጣቸው እንደራሴዎች አልነበሩም ። ስለዚህ «የኢትዮጵያ ሕዝብ» በምን ዓይነት አኳኋንና ዘዴ ነው «አቤቶ እያሱን ሽሮ ንግሥት ዘውዲቱን ያነገሠው»? ደራሲው «የኢትዮጵያ ሕዝብ» ሲሉ መሳፍንቱንና መኳንንቱን ነው? ትክክለኛውን መልሱ ከመጽሐፉ ለማግኘት ያስቸግራል ።


ሁለተኛ ፣ በዚሁ እላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ ውስጥ አንድ ሌላ በኢትዮጵያ ያልተለመደ ሐሳብ አለ ። የደራሲው የግል አስተያየት ይሁን ወይም በጽሑፍ በዚያኑ ጊዜ የተገለጸ ለማወቅ አይቻልም ። ደራሲው የጻፉት ለእኔ እንደገባኝ የተደረገው ውሳኔ ንግሥት ዘውዲቱ የአገሪቱ የበላይ መሪ እንዲሆኑና አልጋ ወራሹ ደግሞ የመንግሥቱ መሪ እንዲሆኑ ይመስላል። ይህ በአገር የበላይ ጠባቂና በመንግሥት መሪ መሀከል ያለው ልዩነት በዚያኑም ዘመን ቢሆን ያልገባቸው ሰዎች ሳይኖሩ አልቀሩም ። ደጃዝማች በየነ ተገርፈው የታሰሩት ይኸው ልዩነት ግራ ገብቶአቸው ይመስላል ።የሆነ ሆኖ ደራሲው «አልጋ ወራሽና እንደራሴ ሆነው የመንግሥቱን ሥራ እንዲመሩ መወሰኑን» የሚያረጋግጥ ጽሑፍ መኖሩን ጠቅሰው ጽሑፉን በመጽሐፋቸው ውስጥ አለማሳተማቸው ቅር ያሰኛል ። (ገጽ 89) የሚያስገርመው ግን በዚያን ጊዜ የተጀመረው የአገርን የበላይ ጠባቂና የመንግሥትን መሪ ለመለየት የታቀደው አዲስ ሐሳብ ዛሬም በ1963 ዓ ም የማይገባቸው ሰዎች መኖራቸው ነው ። ለጊዜው ጠቃሚ መስሎ የታየ ሐሳብ እንጂ የሐሳቡ ቁም ነገር በኢትዮጵያ የቀረ አይመስልም ።
ሦስተኛ ፤ በ1910 የተደረገው የመሀል ሠፋሪ አድማና ውጤቱ በዚያን ጊዜ ባለሥልጣኖች የጀመሩትን የግል ሀብት ማከማቸትና የሕዝቡንም አስተያየትና ንቅናቄ በጉልህ ይገልጻል ። በዐሥራ ሁለቱ ሃዋርያት አምሳያ ተመርጠው የተሾሙት ሚኒስትሮች «ለአገር ልማት ፤ ለሕዝብ አንድነት በመምከር ፈንታ» የየራሳቸውን የግል ጥቅም በማሳደድና ሀብት በማከማቸት «12ት አጋንንት ስለሆኑ» እየዘረፉ «አገሩን አበላሹት እንጂ ለመንግሥት የጠቀሙትና የሠሩለት ጉዳይ የለም» በማለት እንዲሻሩለት ጠየቀ። መሀል ሠፋሪ እንደጠየቀው አልጋ ወራሹ ሚኒስትሮቹን ሻሩ ።ከዐሥራ ሁለቱ ሚኒስትሮች ውስጥ በመሀል ሠፋሪ ጥያቄ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ብቻ በሥልጣናቸው እንዲቆዩ ተደረገ ።

የመሀል ሠፋሪ ኃይል ከምን የመነጨ ነው? ጠመንጃ መያዛቸው ነው? ወይስ ከሕዝቡ ጋር ልዩ አግባብና ልዩ ግንኙነት ነበራቸው? ሚኒስትሮች እንዲሻሩላቸው አልጋ ወራሹን ሲጠይቁ ፤ አልጋ ወራሹ ንጉሥ እንዲባሉ ንግሥትን ሲጠይቁ ምን ወይም ማን እያነሣሣቸው ነው? መሀል ሠፋሪ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን ከሚኒስትሮቹ ለይቶ ጻድቅ ያደረጋቸው ለምንድን ነው?

ሌላም ጥያቄ አለ ። በየጊዜው አንዴ የመንግሥቱን ሥልጣን ለመንጠቅ በመከጀል ፤ አንዴ አገሪቱን በመሸጥና በሌላም ነገር መኳንንቱ አልጋወራሹን ሲያሙና ሲዶልቱባቸው መሀል ሠፋሪ ደግሞ በአልጋ ወራሹ ላይ ትልቅ እምነት የነበረው ይመስላል ። በአልጋ ወራሹ ላይ የመኳንንቱን ተቃውሞ የፈጠረውና የመሀል ሠፋሪን ድጋፍ ያስገኘላቸው ምንድን ነው? መኳንንቱን ምን በደሉአቸው? መሀል ሠፋሪንስ ምን ጠቀሙት?
ለነዚህና ለሌሎችም ብዙ ጥያቄዎች የሚገቡትን መልሶች ማግኘት የአሁኑ ትውልድ መብት ነው ።
በታሪክ ማስታወሻ ውስጥ ስለ ንግሥት ዘውዲቱም ቢሆን ሰፊ ሐተታ የለም ። ነገር ግን በአጭሩ ተቀምማ የተጻፈች አንዲት ኃይለ ቃል አለች ። በሙሉ ልጠቅሳት እፈልጋለሁ ። ደራሲው «የንግሥትን አስተያየትና ሐሳብ» በአጭሩ ለማስረዳት የሚከተለውን ጽፈዋል ።
«እኔን ሳያውቀኝና ላልጠቅመው የአባቴን ውለታና ወሮታ ለመመለስ ሲል የኢትዮጵያ መሳፍንት መኳንንትና ሕዝቡም በፈቃደ እግዚአብሔር ታዝዞ ለአባቴ ዙፋን ቢያበቃኝ ከኔ አስተዳደር አለማወቅ የተነሣ ሕዝቡ እርስ በርሱ ተፋጅቶ ከሚያልቅና ራሳቸውን አልቻሉም ተብሎ በዘመነ መንግሥቴ የባዕድ መንግሥትና ገዢ በኢትዮጵያ ላይ ከሚገባ እኔ የተጠየቅሁትን ሥልጣን እየለቀቅሁና እየሰጠሁ ነገሩን ማብረድ ይሻላል ።» በማለት ለጊዜው የሚገጥማቸውን ችግር ሁሉ ከፍ ባለ ትዕግሥት ያሳልፉት እንደነበረ በግልጽ ይታወቅ ነበር ።
ምንም እንኳን በዝርዝር ባይገለጽ ስለ ንግሥት ሥልጣንና ኃይል፤ ስለ ነበረባቸውም የሥልጣን ትግል ፍንጭ ለማግኘት ይቻላል
2ኛ ፤ ከማይጨው እስከ 1933 ዓ ም ይህ የመጽሐፉ ዋናው ክፍል ነው ። ደራሲው በተቻላቸው መጠን ከንቱ ውዳሴን ትተው እውነተኛውን ድርጊት በመግለጽና ብዙም ለማስረጃ የሚሆኑ ደብዳቤዎች በመጥቀስ በማይጨውና በሌሎችም ሥፍራዎች ስለተደረጉት ጦርነቶች ፡ በኋላም ጃንሆይ ከመመለሳቸው በፊት የተደረገውን የሕዝብ ስሜት መቀስቀስና የመጨረሻ ጦርነት ዝግጅት በሰፊው አትተዋል ።
ብዙዎቹን ድርጊቶች ሲያስረዱ የአንዳንድ ሰዎች ስም በመጥቀሳቸው የተጠቀሱት ሰዎች ወገኖች ደራሲውን እንደሚወቅሱአቸውና እንደሚያዝኑባቸው እንዳልሆነና ስለራሳቸውም «ከነቀፋው የማልለይ አንዱ ተነቃፊ መሆኔንም አምም ተገንዝበዋል።ደራሲው ግን ስም ጠርተው እውነቱን ቢጽፉ ወገንን ለመንቀፍ» ምክንያቱ ከታወቀ ሁሉም ያስብበታል በማለት ነው ። እውነቱ ተገልጾ መድኃኒቱናለሁ ፣ ነገር ግን በሽታው ካልታወቀ መድኃኒቱ አይገኝለትም እንደሚባለው ሁሉ ተገኝቶለት የሚድነው በሽታ በይሉኝታ ፍርሀት ተጋርዶ ብንደብቀው በሽታው አመርቅዞ የሚጎዳን እኛኑ ነው ።» ሲሉ አመልክተዋል ።

አንዳንዶች ሰዎች ስለዘመዶቻቸው በታሪክ ማስታወሻ ውስጥ የተጻፈው ስላላስደሰታቸው ደራሲውን ይወቅሱ ይሆናል ። ወቀሳው ከዝምድና ስሜት ብቻ የመነጨና የዘመዶቻቸው ታሪክ እነሱ እንደሚያስቡት አምሮና ደምቆ ባለመቅረቡ ብቻ ከሆነ በስሜታቸው አይፈረድባቸውም፤ ወቀሳቸው ግን ተደማጭ ሊሆን አይችልም ። የጎደለ ወይም የተወላገደ ነገር አለ ብለው ካመኑ ማስረጃውን እያቀረቡ ታሪኩን ለማሙዋላት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለባቸው። መቼም ቢሆን አንድ ሰው ታሪክን ሲጽፍ በተቻለው መጠን መርምሮና አጣርቶ በእሱ ግምትና አስተያየት እውነት ነው ብሎ የሚያምንበትን ነው። አንዱን ድርጊት ልዩ ልዩ ሰዎች በልዩ ልዩ መንገድ ሊመለከቱት ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ አደጋ ሲያጋጥመው ቢሮጥ አንዱ ተመልካች ሸሸ ብሎ እንደፈሪ ሊገምተው ይችላል ፤ ሌላ ተመልካች ደግሞ አመለጠ ብሎ እንደብልህ ሊገምተው ይችላል። እንግዲህ ድርጊቱ ማለት የሰውዬው መሮጥ ፦ እውነት ከሆነ ፤ ይህንን መሮጥ አንዱ ተመልካች ከፍርሀት ጋር አንደኛው ደግሞ ከብልሃት ጋር ቢያያይዘው የአስተያየት ልዩነት እንደሆነ ለማወቅ ከተፈለገ ስለዚያ ሰውዬ ሌላ ብዙ ነገር ማወቅ ያስፈልጋል ። ሙሉ እውነት የሚወጣው ብዙ ሰዎች በየበኩላቸው እንዳዩትና እንደሰሙት ሲናገሩና ሲጽፉ ነው ።
የታሪክ ጥቅሙ የቀድሞዎቹን ሰዎች ለማሞገስ ወይም ለመንቀፍ አይደለም ፤ ትክክለኛውን ሁናቴ በማፍታታትና እውነቱን በመግለጽ የወደፊቱን ትውልድ ከስሕተት ለማዳን ነው። የሚያሠጋውና የሚያሳስበው ያለፈው ሳይሆን ወደ ፊት የሚመጣው ነው ። ለምሳሌ ኢጣልያ ኢትዮጵያን ለመውረር የቻለችበትን ምክንያት ለማወቅ የምንፈልገው ለወደፊቱ እንድንጠነቀቅና እንድንደራጅ እንጂ ባለፈው እንድንተክዝ አይደለም ።

ኢጣልያ ኢትዮጵያን ለመውረር የቻለችበት በጦር መሣሪያዋ ዓይነትና ብዛት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ መታመምም ነው። የኢጣልያንን የጦር ኃይል ብልጫ ትተን ፤ ኢትዮጵያ የተሸነፈችበትን ምክንያት እንደሚከተለው በአምስት ለመተንተን ይቻላል።
ሀ) በአንዳንድ ክፍለ ሀገር የሚገኙ ሰዎች ባላባትና ገዢዎቻቸው ስለተገደሉባቸው ወይም ስለታሰሩባቸው በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ላይ ቂም ይዘው ስለነበረ የኢጣልያንን ጦር አልወጉም፤ ሲወጉም የግብር ይውጣ እንጂ በሙሉ ልብ አልነበረም ። በቋና ውጊያ ላይ የንግሥት ባል የነበሩት ራስ ጉግሣ ወሌ የቤጌምድሩ ጠቅላይ ገዢ በመገደላቸው የቤጌምድርና የየጁ ሰዎች ተቀይመው ነበር። ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖትም ሀብታቸውን ተወርሰው በእሥራት ላይ ስለነበሩ የጎጃም ሰዎች አኩርፈው ነበር።
ለ) አንዳንድ መኳንንት በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ላይ በልዩ ልዩ ምክንያት ቂም ይዘው ስለነበረ ከነወታደሮቻቸው ከድተው ለኢጣልያ መሣሪያ ሆኑ፤ ለምሳሌም ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ ተጠቅሰዋል ። «ሌሎችም እንደዚሁ የጠላትን የተንኰል መርዝ የቀመሱ ከፋን የሚሉ ሁሉ በግልጥ ባይከዱ አብዛኛዎቹ በጦርነቱ ጊዜ አገሬ ፤ ቤቴ ብለው ስለነፃነታቸው ያልተዋጉ መሆናቸው እር
ግጥ ነው ።»
ሐ) አንዳንዶቹ አዝማቾች በሙሉ ልብና በቆራጥነት እስከመጨረሻው ድረስ በመዋጋት ፈንታ ምናልባት በፍርሀትና በመባባት ቶሎ ለጠላት እጃቸውን በመስጠታቸው የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል አዳክመዋል ። ለምሳሌ በጅሮንድ ፍቅረ ሥላሴ ተጠቅሰዋል ።
መ) በአንዳንድ አዝማቾችና በበታች ሹማምንታቸው የነበረው የንቀት መንፈስ ፍጹም አንድነት በሚያስፈልግበት ጊዜ የሠራዊቱን ልብ ሳይከፋፍለው አልቀረም ። ከዚህም የተነሣ በሐረርጌ ፤ በኢሉባቡር በኩል ፤ በአሩሲና በባኮ የነበሩት ጦሮች የተጠበቀባቸውን ያህል ኃይል ሳያሳዩ ቀሩ ።
ሠ) አንዳንድ የጦር አዝማቾች በተሰጣቸው ሙሉ ኃላፊነት የሚገጥሙአቸውን ችግሮች ሁሉ የጦር ጊዜ በሚጠይቀው ጥድፊያ ወዲያው ውሳኔ እየሰጡ በማስወገድ ፈንታ ለንጉሠ ነገሥቱና ለጦር ሚኒስትሩ መልእክት እየላኩ ትእዛዝ ሲጠባበቁ ሳያውቁት ጠላትን ረድተዋል ። ከዚህም በላይ አንዳንዶቹ «ጠላትን አጥቅተው ሲመለሱ ያለፈቃድ ሄዳችሁ ለምን ተዋጋችሁ በመባል በጦር ሚኒስትሩ ተወቅሰው ዋስ የጠሩ» መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በያለበት በልዩ ልዩ ምክንያት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው በመጋደላቸውና ኃይላቸውን በመቀነሳቸው ለጠላት ተመችተዋል ። ይህ የሆነበትን መሠረታዊ ምክንያት ደራሲው አልተናገሩትም ። የኢትዮጵያ ሕዝብ የራስ እገሌ ወይም የደጃዝማች እገሌ አሽከር እየተባባለ ተከፋፍሎ ለአገርና ለመንግሥት የነበረው ስሜት ከግል ጥቅሙና ከግል ቂሙ ጋር የተወሳሰበ ነበር ። ስለዚህም ወራሪውን ጠላት የሌላ ሰው ጠላት አድርገው በመገመትና ያለፈው ጥቃታቸውንና ቂማቸውን ጠላት በወገናቸው ላይ በአመጣው ጉዳት የሚወጡት እየመሰላቸው «የበላ ይዋጋ» በማለት ገለል ያሉ ብዙዎች ሳይሆኑ አልቀሩም ። አስተዳደሩ ሕዝቡን ባሪያ አድርጎት ስለነበረ «የበላ ይዋጋ» በሚል የባሪያ ፍልስፍና ቢያምን አያስደንቅም። አንዱን ሰው ጠርተው የጦር መሪ እንዲሆን ጃንሆይ ቢያዙት «እስካሁን ያልታወቅሁ ዛሬ ነው ወይ የምታወቀው?» አለ ። ይህንን ሰውዬ ለመውቀስ ያላስቀመጡት አይገኝም የሚለውን እውነተኛ ኣነጋገር መካድ አለብን ። በሰላሙና በደስታው ጊዜ ያላቀረቡት ጎበዝ በመከራ ጊዜ ቢፈልጉት የአገሩ ክብር በኃ
ይል ተሰምቶት ወኔውን ቀስቅሶ የግል ስሜቱን በብሔራዊ ስሜት ካላሸነፈው በቀር ተራ ሰው ሆኖ ገለል ለማለት መብት ያለው ይመስላል ።
እርግጥ ነው ፤ አንድ ሕዝብ ለታሪኩና ለእምነቱም ሲል ከወራሪ ጠላት ይከላከላል። ግን በመሠረቱ አንድ ሕዝብ ወራሪ ጠላቱን እንዲከላከል ያለበት የኅሊና ግዴታ በሰላም ጊዜ ከአለው መብትና ኩራት ጋር የተሳሰረ ነው ። መብትና ኩራት የሌለው ሕዝብ የአገሩን ጠላት ሊያውቅና ታጥቆም በጦር ሜዳ ለመሞት የኅሊና ግዴታ ሊኖረው እንዴት ይችላል? ፊታውራሪ አያሌው መኰንን አንዱን ባላገር ሽማግሌ «አንተ ባንዳ እዚህ እኛን ያስተናገድህ እየመሰልህ ይህን ጊዜ ወደ የኅሊና ግዴታ ጠላት ዘንድ መላክተኛ ልከህ ይሆናል ፤ እመንገድ ዳር አንድ ነገር ያገኘን እንደሆነ ተመልሼ ነው የምለበልብህ ።» አሉት ። ሰውዬውም ሲመልስ «የመለብለቡ ነገር ከሁለታችሁም ወገን አንድ ነው ፤ የነፃነት ባንዲራ መመለሱን ብቻ እግዚአብሔር እውነት ያድርገው ።» አለ ። ዋናው ነገር ለዚህ ባላገር ወገኑ የሆኑትም ኢትዮጵያውያን ጠላቱ የሆኑትም ኢጣልያኖች መብቱን ባለመጠበቃቸው እኩል ሆነው ታይተውታል። ሚዛኑን ሊያጋድልለት የሚችለው የጊዜው ማመቸትና ሁኔታ ነበር ። ልዑል ራስ ኃይሉም ለደራሲው የጻፉት ደብዳቤ ይህንኑ አስተያየት ይደግፋል ።
ለዚሁ አስተያየት ሌላ ዓይነት ማስረጃ ሊሆን የሚችለው ጃንሆይ ደብረ ማርቆስ የገቡ ዕለት ሰንደቅ ዓላማ ከተሰቀለ በኋላ አርበኞች በጃንሆይ ፊት ሰልፍ ሲያሳዩና ሲፎክሩ «ከራስ ኃይሉ ጋር የነበረው ባንዳ ወታደር ማንንም ሳያስፈቅድ በሰልፉ ውስጥ ተቀላቅሎ እንደአርበኞችም ለመናገርና ጀብዱ ለመቁጠር በሥራው እያፈረ ቢቀርበትም ያለ ይሉኝታ በሰልፉ ተራ ገብቶ ሰልፍ ሲያሳይ» መዋሉ በአርበኛና በባንዳ መሀከል ያለውን ልዩነት የሚያሳየው ሚዛን መሰበሩን ነው ። ሁለቱም እኩል ተሰለፉ ። አርበኛም ባንዳ ፤ ባንዳም አርበኛ ሆነ ።የአርበኛው ክብርና ኩራት ከባንዳው ውርደትና ሐፍረት ጋር ተደባለቀ ።
አርኩም ይሄድና ንኬሉም ያልቅና ፤ ያስተዛዝበናል ይኸ ቀን ያልፍና ።

እየተባለ ተዘፍኖ ነበር ። ዘፋኞቹ የጠበቁት ትዝብት ቀረና ሌላ ትዝብት ተፈጠረ ።
ኢጣልያኖች በኢትዮጵያውያን ላይ ይፈጽሙት የነበረው በደልና ጥቃት አለፈና ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ ም ጃንሆይ አዲስ አበባ እንደገቡ በአደረጉት ንግግር «ሃይማኖትን የሚያስከብርና የሚጠብቅ መንግሥት በማቋቋም የሕዝብንና የኅሊናን ነጻነት በመፍቀድ ለሕዝብና ላገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ብርቱ ምኞታችንና ሐሳባችን ነው ።» ብለው ዕለቱ «ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ» መሆኑን አበሠሩ ።
3ኛ ፤ የደራሲው ሥጋትና ምክር ፦ ደጃዝማች ከበደ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቤተ መንግሥቱ በጣም ቅርባቸው ስለነበረ ብዙ ነገር እንዳስተዋሉ ግልጽ ነው ። የእሳቸው ትውልድ የነበረበትን ትልቅ ፈተናና ትግል ጊዜውና ሁናቴው በሚፈቅደው መጠን ለማስረዳት ሞክረዋል ። እንደሚመስለኝ የሚያሠጋቸው የእሳቸው ትውልድ ያየውን ፈተናና ትግል ያልቀመሰው «የአዲሱ ዘመን» ትውልድ
ነው ” አንደኛ በመግቢያው ውስጥ መጽሐፉ «ለልጆቼና ለእኔ ቤተሰቦች» የተዘጋጀ ነው ሲሉ ፣ ሁለተኛም ያሳተሙትን በሙሉ ለወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (የወጣቶች ሴቶች ክርስቲያናዊ ማኅበርን እንዴት ረሱት) ሲሰጡ አንባቢዎቻቸው «የአዲሱ ዘመን» ትውልድ ወንዶች እንዲሆኑላቸው የመረጡ ይመስላሉ ።
በዚህም ጉዳይ ላይ አንዳንድ በጣም የሚያሳስቡ አስተያየቶች አመልክተዋል። እነዚህን አስተያየቶች አንድ ባንድ ባጭሩ እንመርምራቸው ።
ሀ) ደራሲው «በአገራችን ውስጥ የሚገኙትን የውጭ አገር ተወላጆች እንውደዳቸው እንጂ አንመናቸው ።» (ገጽ ፬፻፵፯) ብለዋል ። ለዚህም ዋና ምክንያት ያደረጉት አንድ «በኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ውስጥ መወደድን ብቻ ሳይሆን መታመንንም አግኝቶ የኖረ ግሪክ «የአገሪቱንና የንጉሠ ነገሥቱን በዘመኑም የነበሩትን የባለሥልጣኖች ስም እያከፋና እያበላሸ ለጠላት መሣሪያ» የሚሆን ጽሑፍ በመጻፉና በማንበባቸው ነው። ይህ ብቻ አይደለም ። ደራሲው ያለፈውን በማስታወስ ኢጣልያ ኢትዮጵያን የወረረችው በጦር ኃይል ብልጫ ብቻ ሳይሆን «ቀደም ብላ በኢትዮጵያ ውስጥ ባቋቋመቻቸው የዲፕሎማቲክ ሠራተኞችና ሚሲዮናዊያኖች አማካይነት የሀገሪቱን ታላላቅ ሰዎች እርስ በርስ በማጋጨትና በማጣላት ኃይል እንዲቀነስ ታደርግ በነበረው የተንኰል ምክንያት ነው ።» (ገጽ ፻፲፭)ብለዋል ። በተጨማሪም እኛ ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ ልናስታውሰውና ልናስብበት የሚገባን «ጠላት ያለን ሰዎች መሆናችንን ነው ።» (ገጽ ፬፻፵፭) ብለው ፤ለወደፊቱም የሚያስፈልገን «ጠላት መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ መከላከልና መጠ
ንከር» (ገጽ ፬፻፵፫) መሆኑን አመልክተዋል ።
በዚሁ ሁሉ ከደጃዝማች ከበደ ጋር የማይስማማ ማሰብ የሚችል ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን በዚህ ረገድ የደራሲው መልእክት ለመንግሥቱ ታላላቅ ባለሥልጣኖች ነው እንጂ ለተራው አንባቢ ሊሆን አይችልም ። ደራሲው የጠቀሱትን ግሪክ ቤበተ መንግሥቱ ምስጢር ተካፋይ ባለሟል ያደረገው ማንነው? ደግሞስ በእውነቱ ከባለሥልጣኖቹና ከተራው ሕዝብ የበለጠ ፈረንጅ አምላኪ ማን ነው?
አንድ የጥናት ጓድ ይዤ ወደ አንድ ቦታ ሄጄ ፤ በጥናት ጓዱ ውስጥ አንድ አሜሪካን ነበረ። የወረዳው ገዢ የነበሩ አንድ ሽማግሌ ባላምባራስ በሜዳ ላይ ጠሩኝና «አለቃው ማን ነው?» ብለው ጠየቁኝና እኔ እንደነበርሁ ነገርሁአቸው ።በጣም ተናድደው ፤ «ፈረንጅ እያለ ደሞ አንተ ብሎ አለቃ!» ብለው እንድታሰር ለፖሊሱ አዛዥ ትእዛዝ ሰጥተው በፖሊስ ጣቢያ ታስሬ አድሬአለሁ ። ተመሳሳይ የሆነ በደል ደግሞ አንድ ሌላ ፊታውራሪ እንደራሴ ፈጽመውብኛል ። ይህን ዓይነት ሁናቴ በየዕለቱ የሚያጋጥመን ነው ። የቤት ኪራይም በምንፈልግበት ጊዜያላንዳች ሀፍረት «ለአበሻ አይከራይም» የሚሉ ሞልተዋል። በሥራም ላይ ቢሆን አንድ ኢትዮጵያዊ አጠናቅቆ አጥንቶ ከሚያቀርበው ጥናት አንድ ፈረንጅ የሚቀባጥረው የበለጠ ተደማጭነት እንዳለው በይፋ የሚነገር ነው።እንዲያውም በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ አእምሮአቸው የዛገ ፤ ከነጭነታቸው ሌላ ተፈላጊ ነገር የሌላቸው አማካሪዎች በብዙ ሺህ ብር እየተቀጠሩ የራሳቸውን ሰዎች (ራሳቸውንም ጭምር) ለሚንቁ ባለሥልጣኖች ማታለያ የተቀመጡ መኖራቸው የታወቀ ነው።

አንዳንድ ጊዜም ለልዩ ልዩ ዓይነት ጥናት እየተባለ ጥቂቶች የውጭ ሰዎች መጥተው ፤ ማናቸውንም ነገር ከኛው ሰብስበው በሚያምር ሁኔታ ጠርዘው ለመንግሥቱ ባለሥልጣኖች አቅርበው በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ተሸክመው አገራቸው ይገባሉ። ያገሩን መሬት ባገሩ በሬ የሚባለው ተረት ብቻ ነው ።
ስለዚህ ነጮችን ማምለክ የተጀመረው ከላይ ነው “በኢትዮጵያዊነት ኩራት ተወልዶ በኢትዮጵያዊነት ኩራት ያደገው ትውልድ አልፎአል ፤ ወይም ወደማለፉ ላይ ነው። የዘመኑ ትውልድ ስለአገሩና ስለሕዝቡ የሚማረው ነጮች እያጠናገሩ ከጻፉአቸው መጻሕፍት ነው። እግዚአብሔር ሲፈጥረን አእምሮ ያጎደለብን ይመስል የማሰብን ተግባር ለነጮች ትተነዋል ።
በእንደዚህ ዓይነቱ ሁናቴና አካባቢ የሚያድጉ ልጆች በአገራቸውና በወገኖቻቸው ቢያፍሩና ነጮችን ቢያመልኩ ምንም እንኳን የሚያስከፋ ቢሆን አያስደንቅም። ማንን አብነት አድርገው ይደጉ? አባቶቻቸው የተውትን ወግና ሥርዓት ማን ያስተምራቸው? የማናቸውም ነገር ሚዛን ብርና ሣንቲም ብቻ በሆነበት ዘመን የክብርንና የኩራትን ዋጋ ማን ያሳያቸው? የአፍ ጮሌነት፤ ውሸትና ማጭበርበር በሚያይሉበት ማኅበር ማን ደፍሮ እውነቱን ይስበክላቸው?
ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን በቀር ለሌላው ሁሉ የምትመች ሀብታም አገር ነች ።
ከወደቅንበት የውርደት አዘቅት ለመውጣትና ክብራችንንና ኩራታችንን ለማደስ ትልቅ ኃይል ያስፈልገናል። ለዚህም ኃላፊነቱ የማን እንደሆነ ግልጽ ነው ። ደራሲው እንዳመለከቱት «የአገሩ ተወላጅ የአገሩ ጌታ ሆኖ ከአገሩ ላይ በሚገኘው ሀብት ሊአዝበት መብትና ሥልጣን» እንዲኖረው ያሻል ።
ለ) ሌላው የደራሲው ቅን ሐሳብ እኛው እርስ በርሳችን ሊኖረን የሚገባን ግንኙነት ነው። በመፈራራት፤ በመናናቅና በመተፋፈር እንደባዕድ ከአንገት በላይ መሸነጋገሉን ትተን የአንድ አገር ሕዝብ መሆናችንን በመገንዘብ ለአንድ የጋራ ዓላማ በግልጽ መመካከርና ሐሳብ መለዋወጥ አለብን። የሚከተለው ኃይለቃል ልናስብበት የሚገባን ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ነው ።
«በእውነት ተግባብቶ ከልብ ከሆነ ፍቅር ጋር ከተመካከሩበት በአገሩ የውስጥ ጉዳይ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ይገኝ አይመስለኝም እኛም መቼውንም ቢሆን የጎዳንና የሚጎዳንም የርስ በርስ አለመስማማትና አለመተማመን ተባብሮ የአገርን ጉዳይ የራሴ ነው ብሎ ገልጦ አለመምከርና አለመሥራታችን ነው አላዋቂ የሚያደርገንና ወደ ኋላም የሚአስቀረን።አገርንና ነጻነትን በሚአጠፋ ጉዳይ ይሉኝታን እየፈሩ ምንቸገረኝ በማለት እስከመጨረሻው ጥፋት መቆየት የሰብአዊ ተግባር አይሆንም ፤ እስከ መጨረሻ ሞቱ ድረስ ሳር እየበላ ተነድቶ እንደሚታረደው በሬ መሆን አይገባንም ።»
የነገይቱ ኢትዮጵያ የምትታነጸው በዛሬው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ። ዛሬ ዝም በማለት ፤ በቸልተኛነት ወይም በግዴለሽነት የምናሳልፈው ክፉ ነገር ሁሉ ነገ የእኛን የራሳችንንና የልጆቻችንንም ሕይወት ማበላሸቱ አይጠረጠርም ።

ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚበጀውን ዕውቀት ሁሉ ከእግዚአብሔር ለብቻው የተቀበለ ማንም ሰው የለም። ይህ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው ።ሁሉም በየበኩሉ እንደተገለጸለትና ፡ እምነቱ፤ እውቀቱና ትምህርቱ በፈቀደለት መጠን
ሐሳቡን እንዲገልጽና ድርሻውን ግዴታ እንዲፈጽም ዕድል ማግኘት አለበት ።
ሁላችንም በአገራችን ጉዳይ የሚያገባን ካልሆንንና ግዴታችንም በጥልቅ ካልተሰማን አንድ ሕዝብ ልንሆንና ተደጋግፈን ልንራመድ አንችልም።ሁሉም በየፊናው ጥምብ እንዳየ ጭልፊት ለሆዱና ለግል ጥቅሙ መሯሯጥ ለሕዝብነታችን መርዝ ነው። ጠላት ወዳጅ መስሎ ልፋጭ ሲያሳየን በተስገበገብን ቁጥር ከመዋረዳችንም በላይ በታሪካችን የቆየን የሕዝብነት ኃይል እየመነመነ እንደሚሄድና የጠላትን ግፊያ ልንቋቋም የማንችል ደካሞች እንደምንሆን አይጠረጠርም።
እኛ ያለፉት አባቶቻችንን ስናስታውስ ልባችን በኩራት የሚሞላውና ክብር የሚሰማን (የኩራትና የክብር ቋታችን ያልተሙዋጠጠብን) መንፈሳቸውን ሳያዋርዱ ፤ እምነታቸውንና የሰውነታችን ልክ በጊዜአዊ ጥቅም ሳይለውጡ ወይም በኃይል ሳያስደመስሱ በቁም ነገራቸው ጸንተው አገሪቱን ስላቆዩልን ነው።ድሆችም ቢሆኑ ነፍሳቸውን የሚያጫርቱ አልነበሩም ። የጦር መሣሪያቸው በዓይነትም በብዛትም ዝቅተኛ ቢሆንም እነሱ ደካማዎች አልነበሩም።አካላቸው ለዓይን የሚሞላ መስሎ ባይታይም የመንፈሳቸው ግርማና ብርታት የማያስደፍራቸው ነበር። ባይማሩም አላዋቂዎች አልነበሩም ። ሰውነታቸውን ያወቁ ሰዎች ነበሩ ።

እነሱ አደራቸውን ጠብቀው ለኛ ያስተላለፉልንን ቅርስ እኛም አደራው ተሰምቶን ለሚመጣው ትውልድ ኩራትና ክብር ያለበት ቅርስ ለማስተላለፍ ብቁዎች ነን ወይ? የነገይቱ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አገር እንደምትሆን ለመገመት በማናቸውም ደረጃ ይነስም ይብዛም የመሪነት ኃላፊነት ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ራሳቸውን ሳያታልሉ ይህንን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋቸዋል ።
የታሪክ ማስታወሻን ያነበበ ሁሉ ደራሲውን ደጃዝማች ከበደ ተሰማን የሚወቅስበት ዋናው ምክንያት በጻፉት ሳይሆን ባልጻፉት ነው ። ብዙ ነገር ነፍገውናል የማለት እምነት አለ። ወቀሳው መቼም ትክክለኛ ነው።ይህም የሚያሳየው የኛው ሽማግሌዎች የሚጽፉትን ማስታወሻ ለማንበብ በአዲሱ ትውልድ ላይ ያለውን መጓጓትና መራብ ነው ። ምናልባትም ፡ «ነገ ዓይንህ ይበራል ፤» ቢሉት «የዛሬን እንዴት አድሬ!» እንዳለው የዓርባ ዓመት ዕውር መንፈሳችን ተጨንቆ ይሆናል ” ሁልጊዜም ስለራሳችን ለማወቅ ስንፈልግ ወደ ውጭ መመልከቱ በጣም ታክቶናል። ውስጣችንንም ወና ስላስመሰለብን አሳፍሮናል። የደጃዝማች ከበደ የታሪክ ማስታወሻ ጥያቄአችንን ሁል አይመልስልንም ፤ የዕውቀት ራሀባችንን አያጠግብልንም።ነገር ግን የመንፈሳችንን ጭንቀት በአለኝታና በተስፋ ትንሽ ያቀልልናል ።

አንዱ ትውልድ ሌላውን ትውልድ የሚንቀው ብዙውን ጊዜ ባለማወቅ ነው ። አዲሱ ትውልድ ስለአሮጌው ትውልድ በደንብ አለማወቁ የአዲሱ ትውልድ ጥፋት አይደለም።አዲሱ ትውልድ ተቀባይ ነው እንጂ ሰጪ አይደለም። ይህንን ለመረዳት አያስቸግርም።

አስቸጋሪው ሁሉም በአለው ችሎታ ለኢትዮጵያ መቆርቆሩን በገቢር ፤ በንግግርም ሆነ በጽሑፍ መግለጹ ነው።የታወቁ አርበኞች የኢትዮጵያ ነጻነት መቃብር ውስጥ እንዳይገባ በቆራጥነትና በጀግንነት የተዋጉ ሰዎች፣ እስቲ ለተማሪዎች ንግግር አድርጉ ወይም ሥራችሁ ለአዲሱ ትውልድ አርአያ እንዲሆን ጻፉ እና እናንብበው ሲባሉ «ምነው ምን አልኩህ? ምን አጠፋሁ? እንዲያውም አርበኛ አልነበርኩም! እረፈው» እያለ የሚያንገፈግፋቸው አጋጥመውኛል።ለምን እንዲህ እንደሚሆኑ መጠየቅ አያሻም፤ ባንድ በኩል እንጀራቸው ውሸት መሆኑን ባንድ በኩል ደግሞ የእውነትን ግርማና ሥቃይ ያውቁታል ።የሚናገርና የሚጽፍ ሰው ከሌለ እውነቱን ከውሸቱ፣ ታሪኩን ከተረቱ ለመለየት አይቻልም ።
ስለዚህም ምንም እንኳን ባያጠግበን የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ማስታወሻ አዲስ በርን በመክፈት፤ ብዙ ጥያቄዎችን በማንሣትና ለሌሎችም አርአያ በመሆን የሚያስመሰግን ሥራ ነው። ደጃዝማች ከበደም የጀመሩትን እንደሚቀጥሉ፤ ሌሎችም ጓደኞቻቸው የየራሳቸውን ማስታወሻ ለመጻፍ እንደሚነሳሱ በተስፋ እንጠብቃለን።

Share this post