የዮናስ ጎርፌን “ፕሮቴስታንታውያን በኢትዮጵያ ፖለቲካ” የተሰኘው መጽሃፍ አነበብኩት።ሃይማኖት፣ ሃይማኖተኞችና ታሪክን ይሄሳል።’ተከድነው ይብሰሉ’ የተባሉ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን መጽሃፉ በድፍረት ቃኝቷል።ፈረንጅ ሚሽነሪዎች፣ የፕሮቴስታንት እምነትን በኢትዮጵያ ያስፋፉበት መንገድ በመጽሃፉ በስሱም ቢሆን ተዳስሷል።በሚሽነሪዎች ተኮትኩተው ያደጉት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ በ1966ቱ አብዮት ሰሞንና ማግስት ያመረሩ “የዘውጌ ብሄርተኛ” ለምን ሆኑ? ሲል ይጠይቃል።ባለፉት ስድስት ዓመታት ፕሮቴስታውያን እያደረጉት ያለው የፖለቲካ ተሳትፎና ድጋፍም በሃይማኖት አውድ ቃኝቶ ይሄሳል።ይሞግታልም።
ጴንጤቆስጤያውያን ሲባል?
መጽሃፉ ላይ አጽንኦት የተሰጠው አንዱ ጉዳይ፣ፕሮቴስታንታዊነት ብዙ አብያተ እምነቶች (denominations) እንዳሉት ነው። የአብያተ ክርስቲያናቱ አስተምህሮታቸው እና ሥርዓተ አምልኮታቸው ዋነኛ ልዩነታቸው ነው። ከእነዚህም መካከል እንደ መካነ ኢየሱስ፣ሙሉ ወንጌል፣ ሕይወት ብርሃን፣ ገነት ቤተ ክርስቲያን፣ቃለ ሕይወት፣ጴንጤቆስጤ… እንዲሁም የግል አብያተ ክርስቲያናት ተጠቃሽ ናቸው።
በመጽሃፉ ውስጥ እንደሰፈረው አሁን ላይ አንዱ ቤተ እምነት ከሌላው መለየት አስቸጋሪ ሆኗል።ይሄም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በደፈናው የ’ፕሮቴስታንት እምነት’ እየተባለ መጠራቱ ሥህተት ነው ይላል።አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የገነነው አስተምህሮትም “ጴንጤቆስጤያዊ” መሆኑንም በአጽንኦት ይገልጻል። እንዲያውም እስከ 1970ዎቹ ያለው የእምነቱ እንቅስቃሴ በፕሮቴስታንታዊነት በይኖታል። ከ1970 አንስቶ ያለው ደግሞ ጴንጤቆስጤያዊነት የገነነበትና ሌሎቹን ዓብይተ ክርስቲያናት ጭምር የዋጠበት ጊዜ ነው ይላል። ይህም ስለ አብያተ እምነቶቹና አስተምህሮታቸው ይበልጥ እንድናነብና እንድናውቅ የሚጋብዝ ነው።
ቤተክርስቲያንና ፖለቲካ
ዮናስ በመጽሃፉ የፕሮቴስታንት/ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን (ቤ/ክ) ምድራዊ በሆነው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ምን አይነት ሚና ሊኖራት ይገባል? ሲል ይጠይቃል።በተለይ ከፍተኛ የፍትህ መጓደል ሲኖር የቤ/ክ ምልከታ እንዴት ያለ ሊሆን ይገባል? የሚል ትንተናም ያደርጋል።የመካነ ኢየሱስ ቤ/ክ ቄስ የነበሩት ጉዲና ቱምሳን ሃይማኖታዊ እሳቤዎችን መነሻ በማድረግ ያቀረበው ሂስ ቀመስ ትንተና ብዙ የሚያወያይ ነው ።
የኢትዮጵያ ፕሮቴስታንት/ወንጌላውያን ከትናንት እስከ ዛሬ በማህበረሰባዊ ጉዳዮችና ከማህበራዊ ፍትህ ጋር በተያያዘ ቸልተኛ ሆነዋል ይላል።እንደ ታላቅ የሃይማኖት መሪና ሊቅ አድርጎ የሚመለከታቸው የቄስ ጉዲናን አስተምህሮት መነሻ በማድረግ፣ ቤ/ክ ከማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ችግር ራሷን ፈጽሞ ማግለል የለባትም የሚል አተያይ አለው።ቤ/ክ ‘ማህበራዊ ፍትህ ተጓደለ’፤ ‘ድሃው ተበደለ’ ብላ ካሰበች ድምጿን ማሰማት አለባት የሚል መረዳት አለው፡፡ በአጭሩ ቤተ እምነቶቹ ሰማያዊውን ዓለም ብቻ ሳይሆን፣ በምድር ላይ ሰዎች ሲኖሩ ፍትህ እንዳይጓደልባቸው፣ ሲጓደልም አጉዳዩን ሃይል የሚሞግቱበት ሥነ መለኮታዊ ዕይታ ሊኖራቸው ይገባል የሚል ነው።አሜሪካዊው የመጥምቃዊ ቤተ አምነት ቄስ የነበረው ታዋቂው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግን እና ኢትዮጵያዊው ቄስ ጉዲና ቱምሳን ለዚህ አይነቱ አካሄድ በአስረጅነት ይጠቅሳቸዋል።

በመጽሃፉ (ገጽ፣ 178) የቄስ ጉዲናን ጽሁፍ በመጥቀስ፤ “ፖለቲካ አልባ የኾነ ኑሮ ሙሉ ሕይወት ሊባል አይችልም፡፡ ገለልተኝነትም የሥነ ፍጥረትን መልካምነትና ምስጢረ ሥጋዌን መካድ ነው፡፡ዐሳባችን በመካከለኛው ዘመን የነበሩ ገዳማትን መልሰን አቋቁመን፣ ከሌሎች ተነጥለን መኖር ሳይሆን ክርስቲያናዊ ሃላፊነታችንን በመገንዘብ በየእለቱ በሚያጋጥመውና በተወሳሰበው በሕዝባችን ኑሮ ገብተን መሳተፍ ነው፤” ሲል በጉዳዩ ላይ አቋሙን የሚያጠናክርለት ሃሳብ አስፍሯል፡፡
ዮናስ ስለዛሬውም ሁኔታ ሲገልጽ፤ “ከአርባ ስድስት ዓመታት [ከቄስ ጉዲና ግድያ] በኋላ አሁንም ሀገሪቱ ሌላ ውዥንብር ውስጥ ስትገባ …አለን በምንለው በበሰለ የሥነ መለኮት ዕሳቤ ላይ ተመስርቶ መንግስትንና ማህበረሰቡን የሚሞግት አንድ ድምጽ ለመስማት አልቻልንም፡፡ ያውም የፕሮቴስታንታውያን/ጰንጠቆስጤያውያን ቁጥር ከ25 ፐርሰንት በላይ ነው በሚባልበት ጊዜ፡፡ የሚያሳዝን ጉዞ ነው!” (ገጽ፣ 180)፡፡
እዚህ’ጋ ዮናስ ቤ/ክ የመንግስት አካል ወይም የስልጣን ተጋሪ ትሁን እያለ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ቤ/ክ የመንግስት “ህሊና” ትሁን፡፡ ስሁት አሰራሮችን መሄስ ይኖርባታል፡፡ ከተበዳዮች ጎን መቆም አለባት የሚል አተያይ ነው ያለው፡፡ የሃይማኖትና የመንግስት መለያየት (የሴኩላሪዝም) ዕሳቤ የሚረዳው፣ መንግስታዊ ሃይማኖትና በሆነ ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ መንግስት አይኖርም ከሚል አንጻር ነው፡፡
ምንም እንኳ ዮናስ ይሄን ቢልም፣ በተለይ ሃይማኖትና መንግስት የተለያየ ነው ስለሚለው የሴኩላሪዝም እሳቤ ያለው ነገር የለም፡፡ እንደ ሃገር ሴኩላሪዝምን እንዴት እንረዳው? እንዴትስ ተረድተን ነው ገቢራዊ እያደረግነው ያለው? ህገ መንግስቱ ውስጥ ስለ ሴኩላሪዝም የሰፈረው አንቀጽ መንፈስ ምን ይላል? የሌሎች ሃገራት ተሞክሮስ ምን ይመስላል? የሚለው ጉዳይ አልተዳሰሰም፡፡ የመጽሃፉ አንዱ ውስንነት ነው፡፡
መጽሃፉ ውስጥ የቄስ ጉዲና ቱምሳን አስተዋይነትና ብስለት እጅግ አስደንቆኛል፡፡ከምንም በላይ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የተገነዘቡበት የዕውቀትና የሞራል ልዕልናቸው አስገርሞኛል፡፡ሳር ቅጠሉ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አነብናቢ በነበረበት በዚያ ዘመን፣ የጊዜውን ርዕዮተ ዓለም ከሚከተሉት ሃይማኖታዊ አስተምህሮት አንጻር ተንንተነው መጻፋቸው የብስለታቸው አንዱ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ያነሷቸው ሃሳቦች ዛሬም በሌላ አውድ ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በእውነቱ ቄስ ጉዲና ያልተዘመረላቸው ብልህ ጀግና ብያቸዋለሁ! ዮናስም ስራዎቻቸውን ይበልጥ እንድናነባቸውና እንድንመረምራቸው በሚያደርግ መልኩ ነው ቄስ ጉዲናን በመጽሃፉ ያቀረባቸው፡፡
ሌላው መካነ ኢየሱስ ቤተ እምነት ባዘጋጀው በዘጠነኛው የነጆ ጉባኤ (በ1970) ላይ ሁለቱ ወንድማማቾች (ባሮ ቱምሳና ቄስ ጉዲና ቱምሳ) ያደረጉት ክርክር ያስደንቃል፡፡ የመከራከሪያቸው መነሻ ሃሳብ “ሶሻሊዝምና ክርስትና” የሚል ነበር፡፡ ባሮ ቱምሳ ‘ቤ/ክ ዓለምን እያዳረሰ ካለው ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ጋር ራሷን እያስተካከለች መሄድ አለባት’ የሚል አቋም አራመደ፡፡ ቄስ ጉዲና ደግሞ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም እና ክርስትና ‘መቼም ወዳጅ ሊሆኑ አይችሉም’ የሚል ነበር አቋማቸው፡፡ ባሮ ኮምኒዝን ቄስ ጉዲና ደግሞ የመካነ ኢየሰሱስ ቤተ እምነት በመወከል ነበር ክርክሩን ያደረጉት፡፡ በነገራችን ላይ ቄስ ጉዲና የባሮ ቱምሳ ታላቅ ወንድም ናቸው፡፡ በወቅቱ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ካህንና ጠቅላይ ጸሃፊም ነበሩ፡፡ ባሮ ቱምሳ ደግሞ የኢጭአትና የኦነግ ፓርቲዎች መስራች ነበር፡፡ መቼም በዚህ ጊዜ እርስ በእርስ ከመዘላለፍ ባለፈ እንዲህ አይነት ደርዝ ያላቸው ክርክሮች ማየት ብዙም አልተለመደም፡፡ የወንድማማቾቹ ክርክር ብዙ አስገርሞኛል፡፡
ዮናስ በገጽ፣ 133 እንዲህ ሲል ይጠይቃል፤ “ከምር ያ ጴንጤቆስጤያዊ ትውልድ ሊጠየቅ የሚገባው ነገር ቢኖር፣ ከአቻዎቹ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በተለየ ኹኔታ ፀረ ፖለቲካ የሆነ ባህል እንዲያዳብር ምን ገፋፋው? አሁን ደግሞ ያን አመለካካት በብርሃን ፍጥነት ጥሎ ፖለቲካዊ አጋፋሪና ፊታውራሪ እንዲሆን የገፋፋውስ ምንድ ነው?” ….
በመጽሃፉ ትኩረት ያገኘው ሌላኛው ጉዳይ፣ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ያነበረው የዘውግ (ብሄር) ፖለቲካን ይመለከታል፡፡ የዘውግ ፖለቲካ የፕሮቴስታንቱ/ጴንጤቆስጤው ቤ/ክ መነሻ በማድረግ ከመጽሃፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አንጻር እንዴት ይታያል? በሚል ይሄ ነው የሚባል ትንተናም ሆነ ውይይት ባለመኖሩ ሂስ ያቀርባል፡፡
የመጽሃፉ አንዳንድ ህፀፆች
በመጽሃፉ ውስጥ አንዳንድ ህጸጾችን አስተውያለሁ፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘመናት የመጡት የፕሮቴስታንት ሚሽነሪዎችን ይመለከታል፡፡ በመጽሃፉ ሚሽነሪዎች በአንዳንድ ግለሰቦች አማካኝነት አልፎ አልፎ ከሚያደርጉት የፖለቲካ ተሳትፎ ያለፈ ‘ዓላማ አልነበራቸውም’ የሚል ድምጸት ይጎላበታል፡፡ በሌላ አገላለጽ በዋናነት “ወንጌል”ን ወይም የፕሮቴስታንት እምነትን ለማስፋፋት ጥረት ያደርጉ ነበር የሚል ቅኝት አለው፡፡
በመጽሃፉ የሚሽነሪዎችን ዓላማና ግብ ግልጽ አድርጎ አላስቀመጠም፡፡ እንዲሁም የሚሽነሪዎች በአፍሪካ “ወንጌል” የማዳረስ ተልዕኮ በተለይ ከቅኝ-ግዛታዊ ተዋስኦ (Colonial discourse) ጋር አስተሳስሮ አለመረዳቱ ትልቅ ውስንነት ነው፡፡እንዲሁም ለአውሮጳውያኑ ቅኝግዛታዊ ወረራ ስነ-ዕውቀታዊ ምክንያት ያላበሰውን “የማሰልጠን ተልዕኮ” (Civilizing Mission) የተረዳበት አግባብ ሲበዛ ውስንነት ይታይበታል፡፡
እዚህ’ጋ መታለፍ የሌለበት አንዱ ጉዳይ ሚሽነሪዎች በአፍሪካ ቅኝ-አገዛዝ እንዲስፋፋ ቁልፍ ሚና መጫወታቸው ነው፡፡ አፍሪካዊ ፈላስፋ ቫለንቲን ሙድምቤ ‘The Invention of Africa’ በተሰኘው መጽሃፉ ስለ ሚሽነሪዎች እንዲህ ይላል፤ “የአውሮጳ የአንትሮፖሎጂ አጥኚዎች የአፍሪካን ማህበረሰቦችና እሴቶቻውን ለመግለጽ ‘ሳቬጅ’ የሚል ተረክ ቀርጸዋል፡፡ ሚሽነሪዎች ደግሞ የ’ፓጋኒዝም’ ተረክ ፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ አሳሾችና አንትሮፖሎጂስቶች ‘ሳቬጅነት’ ለማለዘብ የምዕራቡን ሥልጣኔ ማዳረስ ያስፈልጋል፡፡ ምዕራባውያንም ይህን የማስልጠን ተልዕኮ ሊኖራቸው ይገባል በማለት ለቅኝ አገዛዝ መነሻ አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሃይማኖት ሰባኪያን (ሚሽነሪዎች) ደግሞ ፓጋን የሆነው የአፍሪካ ማህበረሰብ ክርስትና እንዲቀበልና የምዕራቡ ዓይነት የሕይወት ዘይቤ እንዲከተል ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ለቅኝ ገዢዎች መንገድ ጠራጊ ነበሩ፤” ይላል ( ገጽ፣ 29)፡፡
ሙድምቤ በመጽሃፉ፣ ሶስት ወሳኝ ሃይሎች “…አፍሪካን በቅኝ ግዛት ስር እንድትወድቅና ጨለማው አህጉር ወደ ሥልጣኔ እንዲሸጋገር የሚለው ትርክት መሬት እንዲረግጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ እነዚህም አሳሾች፣ ወታደሮችና ሚሽነሪዎች ናቸው፤”ይላል (ገጽ፣ 59)፡፡ ከዚህ አንጻር የሚሽነሪዎች እንቅስቃሴ ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ መንግስታዊ ተቋማትን በመመስረትና በማስተዳደር ሂደት፣ ትምህርት ቤት በመክፈት፣ በማስተማርና እምነትን በማስቀየር ትልቅ ተጽዕኖ በማሳደር ይታወቃሉ፡፡ የሚሽነሪዎች ተረክ ያ ትውልድ ያጋጠመው የማንነት ቀውስና ከገዛ የባህል እሴቶቹ የመነቀል (“Cultural dislocation”) አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ሌላው ሚሽነሪዎች እምነት ሲያስፋፉ ሥር-ነቀል የሆነ የባህል ልዋጤ (ከገዛ እሴት መነቀል) እንደሚያስከትል ደርዝ ባለው አኳኋን በመጽሃፉ አልተዳሰሰም፡፡ እንደሚታወሰው ሚሽነሪዎች አንድ ሰው ከነባር እምነቱ ወደ ፕሮቴስታንት እምነት የሚያደርገው ልዋጤ (Conversion) ፣ “ከጨለማ ወደ ብርሃን” ፤ “ከሰይጣናዊ ወደ መንፈሳዊ” መንገድ ሽግግር እንደማድረግ ነው የሚመለከቱት፡፡ ከዚህ አንጻር ልዋጤው ነባሩን የሃገር በቀል ባህል፣ ትውፊትና እሴት የሚያስተው ነው፡፡
ለዚህ እንደ አስረጅ አሜሪካዊው አንትሮፖሎጂስትና የታሪክ ተመራማሪ የሆነው ፕ/ር ዶናልድ ዶንሃምን እጠቅሳለሁ፡፡ ምክንያቱም በደቡብ ኢትዮጵያ የነበረው የሚሽነሪዎች እንቅስቃሴ በአይኑ ተመልክቷልና፡፡ ዶንሃም ደቡብ ላይ የታዘበውን “Marxist Modern: An Ethnographic History of the Ethiopian Revolution” በተሰኘው መጽሃፉ እንዲህ ሲል አስፍሯል፡፡ “In the process of conversion, admission to baptism became a test whether converts had in fact separated themselves from tradition.” (ገጽ፣ 97)፡፡
በዚሁ መጽሃፍ በማህበረሰቡ እሴቶች ላይ የማያባራ ጦርነት በሚሽነሪዎች መከፈቱን እንዲህ ሲል ይገልጿል፤ “Converts were expected not just to avoid traditional religion but to carry the war on custom into the very hearts of their communities.” (ገጽ፣96)
በጉዳዩ ላይ አንጋፋ ፖለቲከኞችና ቀደምት የሚሽነሪዎች ውሉድ የነበሩ ግለሰቦችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ዮናስ በመጽሃፉ አስፍሯል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የመካነ ኢየሱስ ቄስ የነበሩት የለታ ልጅ፣ ሌንጮ ለታ ይገኝበታል፡፡ የኦርቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንትና እስልምና መስፋፋት ሂደት በኦሮሞ ነባር ባህል ላይ ስላሳደሩት ተጽዕኖ የሰጠው አነጋጋሪ ምላሽ እዚህ ጋ እንጥቀሰው፤ “የኦሮሞን ባህል ለማዳከም እንደ ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ስራ የሰራ አልነበረም፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የክርስትና አስተምህሮን ከነባር ባህሉ ጋር አቀራርባ ነበር ያቀረበችው፡፡ የኦሮሞ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ከቅድመ አያቶቹ ሲያያዝ የመጣውን ባህላዊ እምነትና ዕሴት ሳይለቅ ነበር ክርስቲያን የሆነው፡፡ ፕሮቴስታንት ሚሲዮናውያን ሲመጡ ግን አባቶቻችንን ከኦሮሞ ባህላቸውና ዕሴታቸው አፋተው ትልቅ የባህልና የሥነ ልቦና ቀውስ ነበር በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያደረሱት፡፡…” (ገጽ፣209)፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት መጽሃፉ ካነሳው ጭብጥ አንጻር የሚሽነሪዎች ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ባህል፣ እሴት፣ የዘመናዊነት ፕሮጀክትና የሃገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ስላደረሰው ተጽዕኖ በሚገባ አልዳሰሰም፡፡ በተለይ ከቅኝ-ግዛታዊ ተዋስኦ አንጻር አለመመልከቱ ትልቅ ሕጸጽ ነው፡፡
በመጨረሻም
መጽሃፉ መነበብ አለበት፡፡ ተነብቦም መተቸት አለበት፡፡ የዮናስ አይነት የሂሶች መንገዶችም መለመድ አለባቸው፡፡ በእውነቱ የዮናስ ሂስ እጅግ የሚደነቅና የሚከበር ነው፡፡ ምክንያቱም ሃገሪቱ ውስጥ የጠፋው አንዱ ጉዳይ፣ ሃቀኛ የሆነ ማህበራዊ ሃያሲ ነው፡፡ እንዳለመታል ሆኖ እሱ ከቆመበት ዘውግ፣ ሃይማኖትና ርዕዮት ተሻግሮ ሚዛናዊ ሂስ የሚያቀርብ ሃያሲ አለን ለማለት አያስደፍርም፡፡
ዘመኑ ደግሞ ልክ እንደ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ አይነት ሃያሲ ይፈልጋል፡፡ በየቤተ እምነቱ ውስጥ ያሉ መምህራንና ልሂቃን የእምነት ተቋማቸው እውነተኛነትን ለማጽናት የሌሎችን ቤተ እምነቶች ላይ ዘለፋ ማቅረብ ይመስላል ሥራቸው፡፡ የዮናስ መጽሃፍ ግን ይሄን አካሄድ አጥብቆ ይተቻል፡፡ ይሞግታልም፡፡ ለዚህ ተግባሩም አክባሪው ነኝ!
እዚህ ላይ ጥሩ አስተያየት ተስጦታል https://youtu.be/CNncQ7K_PiY?si=qQEsY951f0s0Ia4P