ግምገማ ሐተታ
- ፋሲል ይትባረክ። ምጥቀት በቅኔ አክናፍ፤ የኢትዮጵያዊው ባለቅኔ እና ጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን የሕይወት ታሪክ። ጃጃው ማተሚያ ቤት፣ 2017 ዓም [በ 2005 ዓም በእንግሊዝኛ ከታተመው ፋሲል የተረጎመው]
- Yitbarek, Fasil. Soaring On Winged Verse: The life of poet-playwright Tsegaye Gabre-Medhin. Tsehai Publishers & Distributors. 2013
- ሚካኤል ሺፈራው። ምሥጢረኛው ባለቅኔ። ፋሪኢስት ትሬዲንግ ማተሚያ፣ (2ኛ እትም) 2006 ዓም።
- Molvaer, Reidulf, K. Black Lions: the creative lives of modern Ethiopia’s literary giants and pioneers. The Red Sea Press, Inc., 1997 (በኢት. 1989). የአማርኛው ትርጉም “ጥቋቊር አናብስት” ተሰኝቶ ሽፋኑ ግራ ባጋባ ትክ ብሎ በሚያይ አንድ ዐይና አንበሳ፣ ከላይ በምንሊክ እና በአፄ ኃይለሥላሴ፤ ከመሓል በመንግሥቱ ኃይለማርያም፤ ከግርጌ በጸጋዬ ገብረ መድኅን እና በ በአሉ ግርማ ምስል አሸብርቆአል!
- ምትኩ አዲሱ። ‘ሕይወት ቢራቢሮ’ እንደ ክርስቲያናዊ ምናብ፤ 2010 ዓም፤ Ethiopianchurch
- Adisu, Mitiku. “Tsegaye Gabre-Medhin: Patriot and Pastoral Poet,” Ethiopia Observer 2020. —————–. “Now and Then Tezeta,” Borkena. 2022.
- ጸጋዬ ገብረ መድኅን። እሳት ወይ አበባ። ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት፤ 1966 ዓም
- Kavanagh, Mshengu, R. “TSEGAYE GEBRE-MEDHIN: LET HIS LIGHT SHINE.” Academia. 2020
- Garretson, Peter P. A Victorian Gentleman and Ethiopian Nationalist: The Life and Times of Hakim Wärqenäh, Dr. Charles Martin. James Currey, 2012.
ጸጋዬ ገብረ መድኅን (ጸገመ) ንውዮርክ አሜሪካ በህክምና ላይ እያለ፣ ፋሲል ይትባረክ የሕይወት ታሪኩን በእንግሊዝኛ እንዲጽፍለት በጠየቀው ጊዜ ደስታ እንደ ተሰማው፣ የኃላፊነቱን ክብደት በማጤን ደግሞ ፍርኃት እንደ ገባው፣ “ያልታሰቡ ክፍተቶችና የተዘለሉ ነጥቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ” በመረዳት ሥራውን እንደ ጀመረ ገልጾልናል። በእንግሊዝኛ መጻፍ ያስፈለገው “ለዓለም አቀፍ አንባቢያን እንዲዳረስ” ነው። ታሪኩ ከጸገመ ውልደት እስከ 1966 ዓም ድረስ ነው (ገጽ 11)። ፋሲል ይህንኑ መጽሐፍ “ምጥቀት በቅኔ አክናፍ” (ምጥቀት) አሰኝቶ ለተቀረነው በያዝነው ዓመት (2017 ዓም) በጣም ተነባቢ በሆነ አማርኛ ተርጒሞታል። ይህን በማድረጉ እንደ አገር እና የጸገመ የጥበብ ካፒታል ፋፍቶ እና ተስፋፍቶ ለማየት ለምንመኝ ትልቅ ውለታ ውሎልናል።
ይህ ግምገማሐተታ የእንግሊዝኛውን እያጣቀሰ በ “ምጥቀት” ላይ ያተኩራል፤ “ያልታሰቡ ክፍተቶችን” ቢያንስ ጥያቄ እና ተጓዳኝ አሳቦችን በመቀስቀስ ለመሙላት ይጥራል። የጸገመ ሥራዎች ብሔራዊ ቅርስ ብቻ ሳይሆኑ፣ የባህል ታሪካችን ተርጓሚዎች እና እንደ አገር እንደ ሕዝብ ደግሞ የማንነታችን መገለጫዎች ጭምር ናቸውና፣ ለምርምር ሥራ ጥራት እና ቀጣይነት እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎብናል። በተለይም ከአገር ውጭ በማስተዋወቅ ረገድ።
እዚህ ላይ የ ስቴለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ (ደቡብ አፍሪካ) እውቁ የቋንቋዎች የሙዚቃና የቴአትር ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሮበርት ካቨና ስለ ጸገመ የፃፈውን መጥቀስ ይኖርብናል፦ ፕሮፌሰር ካቨና፣ የጸገመ ሥራዎች ባመዛኙ በአማርኛ መፅፃፋቸው በተለይ ለአፍሪካ ስነ ጽሑፍ መዳበር ብዙ እንዳጎደለ ጠቅሶ፣ ጸገመን ከናይጄሪያዊው ባለቅኔና እና ጸሐፌ ተውኔት ዎሌ ሶይንካ (1934— በፈረንጅ የ 1986 ኖቤል ተሸላሚ፣ ከጸገመ ጋር ሮያል ኮርት ቴአትር ለንደን አብረው የተማሩ)፣ ከኬንያዊው ንጉጊ ዋቲዮንጎ (1938—
2025)፣ ከደቡብ አፍሪካዊው አቶል ፉጋርድ (1932—2025) እና ሌሎች ዋነኞች ተራ እንደሚመድበው ጽፏል። ሌላ ተስፋ የሚሆነን፣ ናፍቆት ታምራት በፈረንጆች 2018 የ “ከርሞ ሰው” ን ወደ እንግሊዝኛ መልሳ ለመታየት መብቃቱ ነው። ሌሎች ኢትዮጵያዉያን ብቅ ብቅ ይላሉ ብለን ተስፋ እናድርግ።
ጸገመ እና ፋሲል ለሁለት ዓመት ያህል እየተገናኙ ያወሩት ነው በቴፕ ተቀርፆ እና ታርሞ በመጽሐፍ መልክ የቀረበው። ጸገመ በጠቅላላው 8 ዓመት ንውዮርክ ኑሯል (ከ ሐምሌ 1990 ዓም እስከ የካቲት 1998 ዓም)። የሕይወት ታሪኩ በእንግሊዝኛ የታተመው ጸገመ ባለፈ በ7 ዓመቱ ነው። በአማርኛ ደግሞ፣ ጸገመ ባለፈ በ19 ዓመቱ፣ የእንግሊዝኛው በታተመ በ12 ዓመቱ።
ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ ቀድሞ ተጽፎ መታተሙ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የአማርኛው ቅጂ ምእራፍ በምእራፍ አንቀጽ በአንቀጽ ከእንግሊዝኛው መተርጎሙ ከአርትዖት ጉድለት ጋር ተደምሮ የእንግሊዝኛ ጠባሳ ትቷል፤ ጥቂቶቹን እንመልከት?
- “የኢትዮጵያዊው ባለቅኔ እና ጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን የሕይወት ታሪክ” ርእሱ፣ ለእንግሊዝኛ ብቻ ተናጋሪ ሲሆን “ኢትዮጵያዊው” ን መጨመር ተገቢ ነው ፤ አማርኛ ለሚያነብብ ግን አላስፈላጊ ድግግሞሽ ነው (በሌላ አነጋገር፣ ኢትዮጵያዊው ሀዲስ አለማየሁ አንልም!)።
- “ጎሮምቲ አዋቂዎችና ቂላቂሎች፣ ጤናማዎችና እብዶች፣
በእነዚህም መኻል የሚገኙየተለያዩ ዓይነት ሰዎች የሚኖሩባት ትንሽ ከተማ ነበረች” (ምእራፍ 7፣ ገጽ 65፣ አንቀጽ 1፣ መስመር 1 እና 2)። ያሠመርኩበት (in between) የእንግሊዝኛ ሐረግ፣ ለአማርኛ የማይገባ አባባል ነው። “Goromti was a small town, but it had more than its share of characters. There dwelled the sage and the simpleton, the sane and the insane, and everyone in between.” “ጎሮምቲ አዋቂዎችና ቂላቂሎች፣ ጤናማዎችና እብዶች፣ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች የሚኖሩባት ትንሽ ከተማ ነበረች” ይበቃል።
- “በአንድ በሆነ ቦታ በመንገድ አግኝቷት
ያለውን ድፍረት ሁሉ ሰብስቦሄዶ የታመቀ ስሜቱን ሲገልጽላት ይታየዋል” (ገጽ 152፣ የመጀመሪያው አንቀጽ፣ መስመር 1 እና 2)። ያሠመርኩበት ሐረግ በእንግሊዝኛው find courage/muster courage መሆኑ ነው፤ “ደፍሮ” ቢል በቂ ነው። ግድፈቶችን በተመለከተ ኋላ እመለስበታለሁ። ይህና የመሳሰሉት በ2ተኛው እትም ይታረሙ። - “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ በ1966 ዓም ወደቀ” (በእንግሊዝኛው fall/fell)፤ ወይስ አበቃ/አከተመ? (ገጽ 213፣ አንቀጽ 1)
- “[የኃይለሥላሴ] ባለሥልጣኖች ካድሬዎችን በከተማው አሰማርተው ነበር” በኃ/ሥ ዘመን “ሲአይዲ” “ነጭ ለባሽ” ወይም “ጆሮ ጠቢ” ነበር፤ “ካድሬ” በደርግ ነው (ገጽ 217፣ አንቀጽ 2፣ መስመር 5)
- “አንበሳው በአንድ ጀምበር አስፈሪ ጥርሱን ማጣቱን ተረዱ” በእንግሊዝኛው፣ the lion had lost its fearsome tooth overnight (ገጽ 218፤ መስመር 7-8)። አንበሳው አስፈሪነቱ አከተመ?
ፋሲል የአጻጻፉን ዝግጅት ሲገልጽ፦ ጸገመ እና እኔ “በቻልን ጊዜ ሁሉ በሳምንት አንድ ቀን ለሁለት ሰዓት ያህል በእሱ መኖሪያ ቤት ስንገናኝ እኔ ጥያቄ አቀርባለሁ፤ እሱ መልሱን ሰፋ አድርጎ ያብራራልኛል … የሕይወት ታሪኩን (የጸገመን) ለመጻፍ ለሚያስፈልጉኝ መረጃዎች ብቸኛው ምንጭ ጸጋዬ እንደሚሆንና መረጃው በአማርኛ ቋንቋ በቃለ ምልልስ መልክ ተሰብስቦ በቴፕ እንደሚቀዳ ከስምምነት ደረስን” (ገጽ 11፣ አንቀጽ 1፣ መስመር 5-7) ብሏል። ምልልሱ የተካሄደው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ቴፖቹ በሥርዓት
ተጠርዘዋል? በጸገመ ሥራና ሕይወት ዙሪያ ጥናት የሚያካሄዱ ቴፖቹን ማግኘት ይችላሉ? “ከተለያዩ የኅትመትና የበይነ መረብ ጽሑፎች” የተሰባሰቡት የትኞቹ መረጃዎች ከየትኛው ማኅበራዊ ሚድያ ነው? “በቅርቡ የሚያውቁት ሰዎች” እነማን ናቸው (መቅድም፣ ገጽ 11)? ሊጠየቁ ሲገባ ያልተጠየቁ ዋነኛ ጥያቄዎች እንዳይገኙ፣ ፋሲል ለጸገመ ያቀረበለትን ጥያቄዎች ከሌሎች ከእነ ማን ጋር መክሮ አመሳክሮ አደራጅቷል? ፋሲል ቤተኛ መሆኑ፣ የ “ምጥቀት” ኅትመት ከጸገመ ኅልፈት ጋር መያያዙ፣ የቤተሰብ
ተሳትፎን ጨምሮ በትረካው ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ አሳድሯል? ይህን ያነሳሁት፣ 2ተኛው ኅትመት ላይ ቢጠቅም ከማሰብ እንጂ መልስ ከመሻት አይደለም።
በሌላ አነጋገር፣ የጸገመ ቃል የታተመው በፋሲል አርታኢነት ተስተካክሎ፣ የተሟላ ትርጒም እንዲሰጥ ተደርጎ ነው። እቅዱ ተገቢ ቢሆንም፣ አንዳንዴ የጸገመን እና የፋሲልን ድምጽ መለየት ያዳግታል። ለምሳሌ፦ 1/፣ “… የአምቦ ነዋሪዎች ዊንጌትን “ወንጌል” ብለው እየጠሩ። ለነገሩ ግን ወንጌልና ዊንጌት ምን ለያቸው? ሁለቱም የእውቀት ማኅደር ናቸው። አንዱ የሰማያዊ፣ ሌላው የምድራዊ እውቀት” (ገጽ107፣ አንቀጽ 2፣ መስመር 6-8)። 2/ “ሰብአ ሰገሎች በሚያበራ ኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም
እንደደረሱ ሁሉ እነዚህ ሦስት አዛውንቶችም በሕይወት መቆየት እንደ መሪ ምልክት ሆኗቸው ከመንዝ ወደ ጎሮምቲ መጡ” (ገጽ 51፣ አንቀጽ 2)። ድምጹ የጸጋዬ ነው ወይስ የፋሲል? በነገራችን ላይ፣ “አዛውንቶችም በሕይወት መቆየት እንደ መሪ ምልክት ሆኗቸው ከመንዝ ወደ ጎሮምቲ መጡ” በሚለው ዐረፍተ ነገር፣ ፋሲል፣ ለሞት ካቃረበ ሽብር እና እርጅና ወደ አዲስ ልደት ወደ አዲስ ሕይወት (ወደ ተወለደው የዓለም አዳኝ) የተደረገን ሽግግር በመጠቆም የ“ምጥቀት”ን ዋነኛ አሳብ አሳምሮ አሰባስቦታል!
ምናልባት ይህን ክፍል የፃፈው በጌታ ልደት ሰሞን ይሆናል!
ፋሲል ባቀረበልን መልክ እና ሥልጣን ባይሆንም ስለ ጸገመ በየቦታው የተበተኑ አያሌ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። ጥያቄው፣ ፋሲል የማናውቃቸውን ምን አዳዲስ መረጃዎችን አቅርቦልናል የሚለው ነው (በተለይ ሚካኤል ሺፈራው ከ20 ዓመት በፊት በ1996 ዓም ካሳተመው “ምሥጢረኛው ባለቅኔ” እና ሞልቬር ከሠላሳ ዓመት በፊት ሌላ)። እያንዳንዱ አንባቢ በየግሉ መልስ እንዲሰጥበት ልተወውና፣ በኔ አስተያየት ጸገመን እና ሥራዎቹን በበለጠ ለመረዳት ጠቃሚ ናቸው ያልኳቸውን “ጥቃቅን” የሚመስሉ ነጥቦችን ልጥቀስ፦
1/ “ከሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ልጆች” የተጻፈው (ገጽ 1-10፤ 283-285)፣ አደባባይ የማያውቀውን የባለቅኔውን ሌላኛ ስብእና፣ እንደ አያት፣ አባት፣ ባል፣ ቤተ ሰብ/ቤተ ዘመድ ሰብሳቢ፣ እንደ ጎረቤት፣ ጓደኛ፣ የሥራ ባልደረባ፣ ታማሚ፣ ወዘተ፣ ማቅረቡ ለትረካው ህያውነትን አቀዳጅቶታል። ለምሳሌ፣ ፋሲል፣ ጸገመ የእግር አውራ ጣቱ ተገሽልጦ ደም በደም መሆኑን ተከትሎ ኳስ መጫወት ማቆሙን መጥቀሱ፦ “ጎል!” የተሰኘ ግጥሙን በአዲስ ጆሮ ለማድመጥ ረድቶናል፦
“ፊኛ በእንጨት ውል በገባ | ‘ጐበዝ’ አጉል እየባባ
ነገሩ እንዲህ ከጠነባ | አፍና ደም ከተቃባ….
ጭንቅላት እንደኳስ ሞልቶ፣ በኳስ ተሳክሮ ቢታወር
እርስ በርሱ ቢሰባበር | እረግ! እያልን የጎል መከር
ዝም ብለን ከማየት በቀር | አያስችለን የሱ ነገር፣
የተነፋ ሩር ማባረር።….”
2/ ጸገመ ንውዮርክ ስታርበክስ እና ለዳያሊሲስ ከሚመላለስበት ሐኪም ቤት ሠራተኞች እና ታካሚዎች ጋር ያበጀው ወዳጅነት፤ በተለይም እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ሳይበገር በፈጠራ ሥራው መጠመዱ፣ ለጥሪው የተሰጠን ሕይወት ያሳያል፤ ጥልቅ ስሜት ይፈጥራል (ምዕራፍ 40-41)።
3/ በጸገመ አባት እና አክስት (አዴ አርጋቱ) እና እናት (በወ/ሮ ፈለቀች ዳኜ) መሓል ስለ ስእለት እና ስለ ቤተ ክህነት ያላቸው ያልተጣጣመ መረዳት በጸጋዬ የፈጠራ አእምሮ እና ስነ ልቡና ላይ የተወው ተጽእኖ በቅኔዎቹ እና በቴአትር መድረኮች ገንፍሎ መውጣቱ ምንጩን ይበልጥ ለመረዳት አስችሎናል (“የስእለት ልጅ፣” ገጽ 33-43)። ባጭሩ፣ ጸገመ የአቡየ የስእለት ልጅ ሳይሆን የአለቃ ማእምር (ገጽ 84፣ 181)፣ የአፄ ኃይለሥላሴ (ገጽ 126፣ 128፣ 179-180) እና የእነ አፖሎ የእነ ዳየናይሥሥ ታማኝ
ጒዲፈቻ ልጅ ሆኖ እናገኘዋለን።
4/ ለአቶ ገብረ መድኅን፣ “ቤተ ክህነት ከቅድስና በራቁ እባቦች የተሞላች ነበረች” (ገጽ 37፣ አንቀጽ 1፣ መስመር 5)። በዚያው ልክ፣ አቶ ገብረ መድኅን የክርስቲያኑን እና የኦሮሞውን አምልኮ ሥርዓት አጣምረው ይዘውታል (ገጽ 57-63)።
5/ ስለ ግራዝማች ጫላ ባሪያ ስለ ኮደሌ (ገጽ 65-66) የተጠቀሰው፣ የባሪያ ንግድ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1934 ዓም በህግ እስከ ታገደበት ጊዜ ድረስ፣ በመላ አገራችን ጭሰኝነትን ተንተርሶ የተንሠራፋ ሥርዓት እንደ ነበር፤ ቤተ ክርስቲያን “በክርስቲያን አገር” በእግዚአብሔር አምሳል በተፈጠረ ሰው ላይ ይህ ዓይነት ጭከና ሲደረግ ለማስቀረት ያደረገቺው ጥረት ኢምንት መሆኑ (የሐኪም ወርቅነህ መጽሐፍ እንግሊዝኛ ቅጂ፣ በተለይ ምእራፍ 9 ይመልከቱ)። እንዳይኮበልሉባቸው አሳዳሪዎች የባሪያዎቻቸውን
ቋንጃ ይቆርጣሉ፤ ቆዳቸውን በጋለ ብረት ይተኲሳሉ። የኮደሌ ምላስ እኲሌታ ተቆርጦ ንግግሯ አይገባም (ገጽ 65)። ይህ ሁኔታ ጸገመ ስለ ፍትኅ፣ ስለ ተገፉት፣ ስለ አሳብ ነፃነት፣ ስለ ቋንቋ ኃይል እና መግባቢያነት፣ አልፎ፣ ሰቆቃ-ለበስ ሥራዎቹን እና ማንነቱን በብርቱ እንደ ቀረፀው መገንዘብ አያዳግተንም (ጸገመ በኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ግእዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ ይግባባል፣ ገጽ 324)።
6/ የጸጋዬ አባት አቶ ሮበሌ በ “ገብረ መድኅን” የክርስትና ስማቸው የመጠራታቸውን ምሥጢር ከምንሊክ ቤተ መንግሥት ጋር ያያይዘዋል። አባቱ፣ የምንሊክ ግብር አዳራሽ ሠራተኛ ነበሩና፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው ሮበሌ እንደ ማለት “ወሮበሌ” እያሏቸው ስለ ጎዷቸው ተቀይመው ነው (ገጽ 29፣ አንቀጽ 3)። በተራው ብሩኁ ወጣት ጸገመ በመምህሩ “ብሩኅ ጋላ” መባሉ ምንኛ እንዳስቆጣውና እንደ ጎዳው መገንዘብ ይቻላል (ገጽ 17፣ አንቀጽ 3፣ መስመር 1)። “አስተማሪው ‘ብሩኅ ኦሮሞ’ ሲሉት
የተቀበለው ጸጋዬ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የነበረው ግለሰብ ይህንኑ ቃል ሲጠቀም ምንኛ እንዳስቆጣውና እንዳናደደው ልብ ይሏል” ይለናል ፋሲል። አስተማሪው “ጋላ” ሲለው ጸገመ ሳያስቆጣው መቀበሉን እርግጠኛ መሆን እንዴት ይቻላል? የትምህርት ሚኒስቴሩ ድርጊት ካስቆጣው፣ ያልነበረ ቊጣ ኋላ ከየት መጣ? ፋሲል በግርጌ ማስታወሻ፦ “ኦሮሞ በማለት ፈንታ ሌላ ቃል እንደ ተጠቀሙ የታወቀ ነው። ጋሽ ጸጋዬ ሲተርክ የተጠቀመው ቃል ይህንኑ (ጋላ) ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ ኦሮሞ የሚለውን ስያሜ ለመጠቀም መርጠናል” ብሏል። ፋሲል በቅንነት፣ ስለቱን ለማዶልዶም ወድዶ፦ “ጋላ” ን (እንደ አውሮጳውያኑ) በ “ጋ*” በመተካቱ ቅራኔው በተቃራኒው ተባብሶ እንመለከታለን። ብንሸፋፍነው ከጀርባ ያለውን ሁላችን እስካወቅን ድረስ ትርፉ መሸነጋገል ነውና።
መፍትሔው፣ እውነቱን አለመፍራት፣ ነገሮችን አስፍቶ ማየት ነው፦ ጥላቻና ደግነትን በሞኖፖል የያዘ ጎሳና ሕዝብ የለም። ኦሮሞው አማራው ትግራዋዩ ወላይታው እርስ በርሱ፣ ፈረንጁ ተማሪው በሠፈር ልጅ ወንድ እና ሴቱ ወጣት ሽማግሌው ገበሬ ነጋዴው ጴንጤ ኦርቶዶክሱ ክርስቲያን እስላሙ ሺዓ ሱኒው ሃብታም ድኃው፤ በየትኛውም ትውልድ ማኅበረ ሰብ ከአዳም ጀምሮ ሲሻኮትበት የኖረ እና የሚቀጥል ነው። አሉታዊ ግንኙነቶቻችን ላስከተሉብን ውጤቶች በሌላው ላይ ከማሳበብ ይልቅ ሙሉ ኃላፊነት ወስደን ጥላቻን እየተዋጋን ወደ ፊት መገሥገሥ ነው፦ “ባንዳ፣ የሴት ልጅ፣ የደሃ ልጅ” ብለነው ያደገ፣ አቅም ሲያገኝ ቢበቀል ለምን ይደንቃል? “ሻንቅላ ባሪያ” ያልነው፦ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም በ1967 ዓም እንደዛቱት (ትክክል ናቸው ማለት አይምሰልብኝና) ልዕልቶችን እንደ ባሪያ “አስጎንብሰው እህል ስላስፈጩ” ለምን ይታማሉ? አብዛኞቹን ስህተቶች በራሳችን ላይ ያመጣን እኛው ነን። በዚያው ልክ፣ ሰው ከስህተቱ አይማርም የተባለ ይመስል፣ ዝንታለም በቀደመው ኃጢአት መወነጃጀል፣ በደልን ከትውልድ ትውልድ ከማዟዟር በተቀር ፋይዳው ምንድነው? ሰው ቀድሞ ትክክል ነው ብሎ የያዘውን አሳብና ልማድ ይተዋል፤ ይፀፀታል፤ ይታረማል። ዛሬም እርስበርስ ከመታገሥ፣ ከመተማመን፣ ከመቀራረብ፣ ከመተሳሰብ፣ ከመከባበር፣ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን ከመፍራት ውጭ አብሮ የሚያኖር ብልኃት የለም።
ጸገመ ይህንን የሕይወቱን ታሪክ ያጋራን በእድሜው ማብቂያ ላይ መሆኑን ልብ እንበል። ወደ ያኔው ትምህርት እና ስነ ጥበብ ሚኒስቴር፣ ለምዝገባ ሄዶ ያጋጠመውን ሌላ ሥፍራም ጠቅሶት ነበር፣ ስም፦ ጸጋዬ፤ የአባት ስም፦ ገብረ መድኅን፤ ብሔር/ጎሳ ለሚለው መልሱን ስላላወቀ መዝጋቢው፣ የአያትህ ስም ማነው? ባለው ጊዜ “ቀዌሳ” ማለቱን፣ መዝጋቢው፦ ቀዌሳማ “ጋላ” ነህ እንዳለው ተናግሯል (ጸገመ ከዚያ በፊት ከኢትዮጵያዊነት ውጭ የጎሳ/ብሔር ስም ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር ይለናል)።
ይኸ ዓይነት ገጠመኝ በአንዳንዶች ላይ ብርቱ ምሬት ፈጥሮ የኋሊት ብቻ እያዩ እንዲጓዙ፣ ለበቀል ሲያነሳሳቸው፣ ጸገመ ግን የጥላቻ እስረኛ ላለመሆን ሰብዓዊነቱን አጽንቶ፣ ነፃነቱን አውጆ የሕይወቱን ጥሪ ሳያጓድል ፈጽሞት እንመለከታለን። በሰዓሊ ባለቅኔ ከበደች ተክለአብ “የት ነው?” መጽሐፍ ሽፋን ላይ፣ ጸገመ ባሠፈረው አስተያየቱ፣ ስለ ገዛ ራሱ የሕይወት ጒዞ ምን እየነገረን ይሆን?፦ “[ከበደች] በልጅነቷ የ11 ዓመት ስደት፣ ግዞትና ወህኒ መክፈልቷን በሥነ-ግጥም ውስጣዊ ብርሃኗ ተቋቋመችው። ይህ ነው የቅኔ ብዕር መክፈልቷና ሚስጥሯ። ከመከራ ሕይወቷ ውስጥ በሥነ-ግጥም ብዕሯ እየታዘለች የሱማሌ ሕዝብን አዲስ ፍቅር ዳሰሰችበት፤ ታቀፈችበት እንጂ፣ የኢትዮጵያንና የሱማሌ ሕዝብን የባህል ድልድይ ቀመረችበት እንጂ፣ በወህኒ ዕድሜዋ የምሬት ባህር አልሰጠመችም።”
ህወሓት ባስነሳው የጎሳ አቧራ ትን ሲለን ሲያስለን ሰንብተናል። ኦሮሞነትን ከሌላው ለይተው ማየት ያበዙ፣ ጸገመ አማራ ነው፤ ወይም ንጹሕ ኦሮሞ አይደለም ለማሰኘት ሲጥሩ፤ አማራነት የበለጠባቸው ደግሞ ጸገመ አማራ አይደለም፣ “አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋው ሆኖ እንዴት እንደዚህ ሊጽፍ ቻለ? ምናልባት [አማራ ሚስቱ] ትሆናለች የምትጽፍለት” ወደሚል ተረት ተዛምተው ሰምተናል (ገጽ 3፣ አንቀጽ 3)። [ስለ እንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ምን እንደሚሉ እግዜር ይወቅላቸው!] ሰብዓዊነታቸውን በአንድ ትከሻ ብቻ ላነገቡ፣ መረማመጃቸውን ላጨለሙ፣ አንድ እውነት ግልጽ ሊደረግላቸው ይገባል፦ “ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ”ን ኦሮሞነት አማራነት ትግራዋይነት አይገድበውም፤ ትዝ አይለውም። ሰው ሆኖ የማያለቅስ የለምና፤ የሚያለቅስን ኦሮሞ ከሚያለቅስ አማራ ትግራዋይ ምን ለያቸው? ሁላቸውም ያለቅሳሉ፤ አብሮ እንደ ማልቀስ ደግሞ ምስኪንነትን የሚገልጥ ሰብዓዊነትን የሚያለመልም የለም! ዛሬ፣ ለየብቻ ማልቀስን መፈራራትን እንደ ኃይማኖት ተያይዘነዋል። የኔ ለቅሶ ካንተ ለቅሶ ይሻላል ተባብለናል። መፍትሔ የራቀብንም ለዚሁ ይመስለኛል። ጸገመ፣ “ዋቃ ገዲን፣ ነማ ኦሊኒ” ሲል፣ ደብረ ሊበን ሄዶ ስላገኘው አባ ገዳ ብቻ አይደለም። ነገሩ ከአባ ገዳ ያለፈ ነው፦ ስለ አንደበተ ርቱእነት ነው፤ በራስ ስለ መተማመን፣ ዓላማን ጠንቅቆ ስለ ማወቅ፤ ለዓላማ ፈጽሞ ስለ መሠጠት፤ ለሌሎች ስለ መኖር፤ በሥርዓት ስለ መተዳደር ነው። እነዚህ እሴቶች ለሁሉም እንጂ ለጥቂቶች ብቻ የተከለሉ እሴቶች አይደሉም።
ይህን ለምን አነሳሁት? እየተጋፈጥናቸው አልረግብ ያሉ ችግሮች ከግለ ሰቦች እንደሚጀምሩ፤ በምሬት በጥላቻ ተኮትኲተው አድገው ዛሬን ጭምር እንዳከሠሩን ተገንዝበን እርስበርስ አክብሮት ማሳየት ይገባናል ለማለት ነው። እግረ መንገድ፣ ይኸ ሁኔታ ባብዛኛው የጥቂቶች (ከተሜዎች) አምባጓሮ እንጂ ለብዙሓኑ ጉዳዩ እንዳይደለ፤ ቤተ እምነቶች ጭምር ፍቅርና መግባባትን፣ እውቀትና እውነትን እንደ መዝራት በጥላቻና በድንቊርና ተሳታፊ መሆናቸውን ለመጠቆም ነው።
7/ የጸገመን ግትርነት እና ቊጡነት በተለይ ፍትኅ ሲዛባ አይቶ አለማለፍ፦ ለንደን ለትምህርት ሄዶ፣ አንዲቷ የአብረን እንደንስ ግብዣውን እምቢ ስላለች ግብግብ ፈጥሮ፣ ለካንስ የራስ መስፍን ስለሺ ልጅ የጃራ ሚስት ኖራ፣ ሽጒጥ ተመዞበትም እንኳ “እስቲ ተኲሳት! እስቲ!” ይል እንደ ነበር (ገጽ 144 145)። ቤት አከራዩ፣ ኋላ ያገባትን፣ የሦስት ህፃናት እናት፣ ፈለቀችን በሆነ ባልሆነ ሲያዋክባት አይቶ “ከአሁን በኋላ ስታመናጭቃት ካየሁ …” ብሎ በኃይለ ቃል ሲናገረው (ገጽ 151-152)። የ1958 ዓም የቀኃሥ የስነ ጽሑፍ ሽልማት ለኔ እንጂ “ለጁጁ ተረት” ጸሐፊ (ጸገመ) አይገባውም እያለ ደጋግሞ የተሳለቀበትን “ዘመደ ብዙ፣ የመኳንንት ወገን” በተቀመጠበት በጥፊ ሲያጮለው (ገጽ 202-204)። በ1995 ዓም በሲዲ ባስቀረጸው ቅኔዎቹ መሓል፣ አንድ “የተበሳጨ ጀብራሬ” አቡነ ጴጥሮስ (ሐውልት) ላይ “አንተ ድንጋይ! እሸናብሃለሁ!” እያለ ሲሸና አይቶ ግብግብ መግጠሙ (ከ19:11—21፡07 ደቂቃ ባለው ጊዜ) ስብእናው የማይታገሣቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ይጠቊመናል። ጥቃትን አለመታገስ እና አቻችሎ ተቻችሎ መኖርን ከአባቱ እንደ ወረሰ ግልጽ ነው (አባቱ፣ ጃንሆይ ባሉበት፣ በኦቴሎ ቴአትር ገፀ ባህርይ ላይ ያሰሙትን ቊጣ፣ ገጽ 183-185)። በሴት ልጁ ሠርግ ላይ በተቀኘው ቅኔ፣ እንደ አገር ቤቱ ልማድ እልልታና ተኲሱን አስታውሶ ቢሆንም፣ እዚህ ግን ተኲሱ ቅርብ ቀን እቤቱ ደጃፍ ላይ በ41 ጥይት ተደብድቦ በግፍ የተገደለውን አፍሪካዊ ለማስታወስ ነው (ገጽ 5)።
የጸገመ ግትርነት በሁለት መልክ ሊታይ ይችላል፦ የሕይወቱን ሙያዊ ጥሪ በማሳካት ረገድ ግትርነቱ ጠቅሞታል። አፄ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤቱን በጎበኙበት ሰዓት፣ ባጭር ጊዜ መምህራኑን እና ጓደኞቹን አሳምኖ የመጀመሪያ ቴአትሩን አዘጋጅቶ ለመድረክ ማብቃቱ (ምእራፍ 12)! ጸገመ የሚፈልገውን ያውቃል፤ አጋጣሚዎችንም ይጠቀምባቸዋል፤ ካስፈለገ መስዋእት ይከፍልባቸዋል። ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ያደረገው ጥረት እና አብረው ከተጓዙት ከፕሮፌሰር ኦይናስኪ ምክር
ውጭ፣ ከወቅቱ ባለሥልጣኖችም ሳያስፈቅድ ወደ ፓሪስ መጓዙ (ምእራፍ 28) ውጤቱ ኢትዮጵያን አጎላ እንጂ አላሳነሰም። ግትርነቱ በጤናው ላይ ያስከተለበት ጉዳት (ምእራፍ 35)፤ በጊዜ ታክሞ ቢሆን ኖሮ የጸገመ ሞት እንዲህ አይፋጠንም ነበር። “ግዳጄን ጥዬ መሄድ አልችልም፤ ውል ተፈራርሜአለሁ” (ገጽ 243፣ አንቀጽ 2)። [በነገራችን ላይ፣ ሃያሲ እና ባለቅኔ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ታሞ በሞተበት ሕመም ምክንያት ሐኪም ቤት በሄደበት ወቅት፣ ሐኪሙ የጤና ምርመራ በቅርቡ ያደረግኸው መቸ ነው ባለው ጊዜ፣ ገና የ10 ዓመት ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ነው ብሎት ነበር!] የጸገመ ግትርነት በአንጻሩ፣ ባላመቸ የፖለቲካ ሥርዓት፣ በጀትና የሠለጠነ ሰው ኃይል በሌለበት፣ ሳያመኻኝ፣ ሳይገታ፣ ጥሪውን እውን ለማድረግ አስችሎታል።
የጸገመ ፈር ቀዳጅነት ምሥጢር፣ የሙያ ጥሪውን ጠንቅቆ ማወቁ፣ አክብሮ መያዙና፣ መስዋእት ቢያስከፍልም ለጥሪው መገዛቱ ነው።
የመጨረሻው ክፍል ይቀጥላል …
© September 2025 by Mitiku Adisu. All rights are reserved.