የትራምፕ የሰላም እቅድ እውነተኛ ገፅታ

የትራምፕ የሰላም እቅድ እውነተኛ ገፅታ

ዋል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ 

ሶስት ሃያላን የቢዝነስ ሰዎች፥ ሁሉት አሜሪካውያንና አንድ ሩስያዊ ፥ ባለፈው ወር በማያሚ ባህርዳርቻ ላፕቶፓቸውን ይዘው፥ ከሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም ዕቅድ እያወጡ ነበር።ነገር ግን ተልእኳቸው ከዚያም ያለፈ አላማን ያነገበ ነበር።በአውሮፓና በአሜሪካ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው የሩስያ 2 ትሪሊዮን ዶላር ተመልሶ እንዲንቀሳቀስ ማድረግና ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት፥ የአውሮፓ የንግድ ተቀናቃኞች ላይ ልዕልናን ማግኘት ነው። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ፥ የሪል ስቴት ባለቤት የነበሩትና ወደ ልዩ መልዕክተኛ የተሸጋገሩት ቢሊየነሩ ስቲቭ ዊትኮፍ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ኪሪል ዲሚትሪቭ የተባሉት የሩሲያ ሉዓላዊ የሀብት ፈንድ ኃላፊ እና የቭላድሚር ፑቲንን ቁልፍ ሰው ናቸው። እየተወያዩበት የነበረውን ሰነድ በአብዛኛው ያዘጋጁት የሩስያው ተወካይ ናቸው። የፕሬዚዳንቱ አማች ጃሬድ ኩሽነር፥ በአቅራቢያው ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱና የቢሊዮነሮች ምሽግ እየተባለ ከሚጠራው ደሴት ተነስቶ መጥቷል።ንብረትነቱ የሩስያ ማዕከላዊ ባንክ የሆነ በአውሮፓ ሀገራት የሚገኝ 300 ቢሊየን ዶላር ለአሜሪካና ሩሲያ ጣምራ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶች ላይ እንዲውል እና ጦርነቱ በዩክሬን ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመጠገን በአሜሪካ የሚመራ የመልሶ ግንባታ ሥራ እንዲቋቋም የሚያሳስብ ነው።የአሜሪካ እና የሩሲያ ኩባንያዎች በመቀናጀት በአርክቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ያለውን ግዙፍ የማዕድን ሀብት መጠቀም የሚችሉበትን መንገድ ያብራራል።ዲሚትሪቭ ሁለቱ ሀገራት በአንድ ላይ ተጣምረው በርካታ ነገሮችን ሊያከናውኑ እንደሚችሉ አፅንኦት ሰጥተው ይናገሩ ነበር።በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሁለቱ ሀገራት ሲፎካከሩበት የነበረው የጠፈር ምርምር፤ አሁን ግን ቅንጅት በመፍጠር ከኢሎን መስክ ኩባንያ የሆነው “ስፔስ ኤክስ” ጋር ወደ ማርስ ሊያመሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ተገልፆል።

ይህ ስብሰባ፥ ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት፥ ሩስያ ከአሜሪካ ጋር ለመቀራረብ ያዘጋጀችው ዕቅድ አካል ሲሆን፥ የተለመደውን የዲፕሎማሲ መንገድ ገሸሽ በማድረግ፥ የአሜሪካ አስተዳደር ሩሲያን ለሰላምና ፀጥታ ስጋት የምትፈጥር ሀገር ሳትሆን ለንግድ ትስስር የምትመች ምድር እንደሆነች ማሳመን ነው።ብዙ ቢሊዮን ዶላርን ያካተተ፥የከበሩ ማዕድናት እና የኢነርጂ ስምምነቶችን ለማድረግ ቃል በመግባት፥ ሞስኮ የአውሮፓን ኢኮኖሚያዊ ገጽታ መዘወር ትሻለች፤ በአሜሪካ እና በቀደምት የአውሮፓ አጋሮቿ መካከል ክፍተት እንዲፈጠር በማድረግ።

ዋል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ላይ የወጣው ይህ ሪፖርት፥ በሩሲያ እና በዩክሬን ለሚገኙ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከፍተኛ ትርፍ የሚያገኙበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት የተደረጉ፥ ሚስጥራዊ ስብሰባዎች እና እቅዶች ይዘረዝራል ።

Share this post