ሐብል፣ አምባር፣ ጒትቻ ስልክ እና ጸሎት

ሐብል፣ አምባር፣ ጒትቻ ስልክ እና ጸሎት

እንደ ዘመኑ ሰው ስልኩም ወሬኛ ወረተኛ ሆነ። የፈረንጅ ስልክ አገራችን ከመግባቱ በፊት ሰው ከወዲያ ወዲህ ተጠራርቶ መጫጯህ ወጉ ነበረ፦ “ወይፈኑ ከጊደሮችህ ጋር መጥቶ ይሆን? …ኡዉይ! … ጠበል ቅመሱ! ቡና ጠጡ! …ኡዉይ! … ወንዙን እንደ ተሻገራችሁ፣ ከጒብታው ላይ ኢየሱስ ይታያችኋል፤ በስተቀኝ የአቶ እከሌ ቤት ከፊት ለፊቱ የሾላ ዛፍ አለ። አደራ አደራ፣ ይህን አድርሱልኝ፤ እንዲህና እንዲህ በሉልኝ…”

ከዚያ ስልክና ስልከኛዪት ዛኒጋባቸውን ቀልሰው እንደ እንጒዳይ በየጠቅላይ ግዛቱ ፈሉ። ጒድ አፈሉ፤ ተዘግቶ ተዘልሎ የኖረን ዓለም አጠላለፉት። ግሉኮስ እንደ ገባለት ህመምተኛ አንዱን ሽቦ ነቅላ ሌላውን ሰካካች። ጆሮዋን ደፍና ዛኒጋባዋ እስኪሠነጠቅ አስካካች። ይህን ሸኝታ ያን አስታመመች። ከአንዱ አፍ ቀምታ ከሌላው ጆሮ ሹክ አለች። በርሷ በኩል ካልሆነ፣ ሰው ማግኘት የማይታሰብ ሆነ። ከለታት አንድ ቀን የስልክ ንግስቲት ይህን ትመስል ነበር። የዛሬን አያድርግና የሠፈር ጌጥ ነበረች። ሰውን ከሰው፣ መንደርን ከመንደር አገናኝታ አለፋለፈች፤ ያስቀየማትን ፊት ነሳች፣ ምሥጢር ያለበትን ድምጽ አስጠፋች፣ አሰገደች።

ከዚያ ባለ ሰንዱቅ ስልክ ከመንገድ ላይ በቀጭን ሽቦ ተጠልፎ እንደ ሌማት ጠረጴዛ ላይ ዳንቴል ለብሶ እንደ ጌቶች በቅሎ ልጓም እንዳያሳብቅ አገልግል ቁልፍ ጎርሶ ተኮፈሰ። አንዳንዱም ከመንገድ ዳር ኪዮስክ ውስጥ ግድግዳ ላይ ከደጅ እንደ ወንጀለኛ በአደባባይ ማንም የጎረምሳ ኮረዳ የሚንጠላጠልበት ሆነ።

በስልክ አነጋግሪኝ (በስልክ አነጋግረኝ) በቀጭኑ ሽቦ … ተባለ። ያም አለፈ። ጊዜ አለፈበት። “መልክት ተውልኝ፣ መልሼ እደውላለሁ” የሚል አፈኛ መጣ። እንደ መሐረብ በኪስ የሚያዝ መጣ። እንደ ዝናር በወገብ የሚታጠቅ። እንደ ዳዊት ከደረት ኪስ የሚያዝ። ስልከኛዪት ድረስ የያዙትን ጥሎ መደናበር፣ ጎረቤት ማስቀናት፣ ሠፈር ለሠፈር መሯሯጥ ቀረ።

“ሃሎ ይበሉ …
ሃ ሃሎ! ሃሎ፣ ሃልዎ። አይሰማም!
(መነጋገሪያውን ገለበጡት እኮ እንዴት ይሰማ? … አሁን ሃሎ ይበሉ!)
ሃ ሃሎ! ሃሎ! ማ ልበል!
ይሰማል? ይበሉ
ይሰማኛል፤ ይሰማል? … እሰማለሁ፣ እሰማለሁ፣ ዉይ ሚጡ ነሽ እንዴ! ሚጡዬ!” እያሉ መጯጯህ ቀረ። ያን ዘመን የሚያስታውሱ፣ ጆሮ መች ሰምቶ፣ ቢጠሩ አይመልሱ ሆኗል ነገሩ።

“እከሊት ስልክ ተደወለላት እኮ … ማን ይሆን ሮብ ሮብ የሚደውል?”
“ወንድሟ ነዋ! ካዲሳባ …”
“ወንድም አላት እንዴ አዲሳባ? … ኧረ እኔ አልመሰለኝም” እየተባለ አጣቀሰ፣ አነጋገረ።
“ልጅዎ ደውሏል? ደህና ነው? ሥራ ይዟል? ገንዘብ ይልካል?”

“ሳይደውል ቆየ፣ ምን እንደ ነካው አላውቅም”
“ምን ይሆናል ብለው ነው? ክፉ ወሬ አይደበቅ። ዛሬ ዘመን ልጅ ከተማ ገብቶ … ወይ ሥራ በዝቶበት ይሆናላ …እንጂ … እርሱ እንኳ ያለ እድሜው አስተዋይ ልጅ ነው” መባባል ቀረ። ሁሉም የእጅ ስልኩን ይዞ ለየብቻው። ከማን ጋር ምን እንደሚያወራ የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው … ሁሉም በገዛ መንገዱ ነጎደ …

ያዲሳባን ስልከኛ ምሽት አውላላ ሜዳ ላይ ማሰባሰብ ቢቻል። ተጯጯሁ እንጂ አልተደማመጡም ይተረት ነበር።

በፈረንጅ ስልክ፣ አፍና ጆሮውን ያሟሸ በይበልጥ ጒረኛ ከተሜ ነው። አብዛኛው ሰው ከአዳም ጀምሮ እንደ ኖረው ኖሮ የዛሬን ሥልጣኔ ሳያይ አልፏል። የጒትቻ ስልክ ስላላየ ምን ቀረበት?

ሐብል፣ አምባርና እና ጒትቻ ስልክ መጣ፤ ጒድ መጣ! ተባለ። ሁሉም በጊዜው ጒድ እንዳልተባለ፣ የኋለኛው ዕፁብ ድንቅ ተባለ። አዲሱ ትውልድ ራሱን ከአባቶቹ እንደሚሻል አድርጎ ባይቆጥር ምን አለበት? ቊጭ ብሎ ማውራት ቀረ፤ እየተጓዙ ማውራት፣ በሁዳዴ ሳይቀር መለፋለፍ መጣ። የስልክ ገመድ ከቀዬው ጋር አጣብቆት የኖረ፣ ተተርትሮ ባዕድ አገርና መንገድ ዳር ዘረገፈው፤ በየስርቻው በየዋሻው ወስዶ ወሸቀው። የብሔር አፍ እንጂ የማይናገር የማይሰማ ዲዳ ስልክ ነጋሪት እየጎሰመ መጣ! ይህንን ነጻነት፣ እሥራት፣ ወይስ መረን መውጣት እንበለው?! ጥንት ከባልንጀራ ጋር ዐይንላይን እየተያየ ግንባር ለግንባር አፍላፍ ነበር ወሬ። ዛሬ አብሮ እየተራመደ ምን እንዳለበት ተራርቆ ተካለለ። በተውሶ ሥልጣኔ እንደ አገራችን ፈጥኖ የገሠገሠ የለም። ስልኪትን የፈጠሯት ፈረንጆች እንኳ ጒትቻ ስልክ ጋ ለመድረስ ቢያንስ 200 ዓመት ፈጅቶባቸዋል።

እምዬ ምንሊክ በ 1886 የተከሉልንን ባለ መዘውር ስልክ ፋሺስት ኢጣልያ የሃምሳ ዓመት ቂም ይዞ እርሳቸው እስኪሞቱ ጠብቆ መጥቶ ነቃቀለው። ይንቀለውና፣ መድኃኒዓለምን የታመኑ እናት አባት ወንድም እህት አርበኞች አምስት ዓመት ታገሉት፤ ፈረጠጠ። እየዘረፈ፣ እየዘረገፈ፣ እሾኽ እየዘራ በሰሜን ምሥራቅ በር ወጥቶ ሸመጠጠ። በአርባ አምስት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደገና አሳምረው ዘመናዊ መገናኛ መሠረቱልን። በስድሳ ዓመት እኛም ወግ ደረሰን። እነሆ፣ ሠርግ ሳይደገስ፣ ከበሮም ሳይደለቅ፣ ባለ ጒትቻና ባለ ሐብል ስልክ አንጠለጠልን፤ ባለ አምባር ስልክ አጥልቀን ተዋብን። ሃሎ! ሃሎ? አልሰማህም! አልሰማህም! ለምን አትሰማኝም? ተባባልን።

ጥንት አዛውንት መንገድ ላይ ሲረማመዱ አፋቸው መላወሱ የተለመደ ነበር፤ እየጸለዩ ነው ይባላል። ማቋረጥ እንደሌለበት ሰው ሁሉ ያውቃል። ከማንጎላጀትና ከወሬ ይልቅ ጸሎት ተሽሏልና። ወይ አሳብ ገብቷቸው ነው ይባላል። ጎልማሳ ግን አፉ ሲላወስ ከአዛውንት ተግሣጽ ይደርስበት ነበር፦ መንገድ ለመንገድ አጋሠሥ ይመስል እያመነዠክ የምትሄድ ምን መዓት መጣ? ይልቅ ምች እንዳይመታህ ቡዳ እንዳይበላህ ይባል ነበር። ጎበዙ ከራሱ ጋር ከሆነ ንግግሩ “ውይ! ውይ! ምጽምጽ” ይባልለታል፣ ጸሎት ብጤ፣ ትፍትፍትፍ ጠበልም ይመረቅለታል።

በስድሳ ስድስት አብዮት መጣ። ጸሎት የሚጠላ አብዮት፣ ከምኑ ጋርርር የተጣላ አብዮት መጣ። ሁሉን በዐይነ ቊራኛ የሚያይ። ዐይን ያወጣ ዐይን የሚያወጣ። ጆሮ የሚጠባ። እግዚአብሔር ስለሌለ የምትጸልዩት ወደ ማን ነው? እኛ እዚሁ እያለን ወደ እግዚአብሔር? ምን አደከማችሁ? ቆይቶ፣ አትጸልዩ መጣ። ከሠርጎ ገቦች ከአድኃርያን ቀልባሾች ከቦርቧሪዎች ይልቅ ጸሎት ተፈራ። የጻድቅና የምስኪን ሰው ጸሎት ከታላቁ መሪ ድንፋታ፣ ከካድሬ ጩኸትና ከኮሚሳርያቱ ትዛዝ ይልቅ አስፈራ። የዜጋን የጸሎት ቋት በአብዮታዊ መፈክርና በእርግማን ለመድፈን ትዛዝ ወጣ።

ከቀይ ሽብር መልስ ብዙ ወጣት ተረፍርፎ ከተረፈው አንዳንዱ በየአውራ መንገዱ ላይ ከናፍርቱ እየተላወሱ ሲረማመድ ማየት ተለመደ። ሲቀረብ ግን እንደ አባቶቹ በለሆሳስ ወደ ፈጣሪ ሳይሆን፣ ድምጽ አጥፍቶ ብሶቱን ለሚሰማው ተላላፊ መንገደኛ ያፈስ ነበር። የብሶቱም ምንጭ መንግሥት፣ የዜጋ መብት አለመከበር፣ ብልሹ አስተዳደር ነበር። “ጸሎተኛውን” ሁሉ መተማመን አይቻልምና እንዳልሰማ እንዳላየ ፈጠን ፈጠን ብሎ መንገድ አቋርጦ፣ አድነኝ፣ ከወጥመድ አውጣኝ እያሉ መሄድ መፍትሔው ነበር።

የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ብዙ አዛውንት አልቀረላትም። የአዲሱ ዘመን ወጣት በሹክሹክታና በጩኸት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ያለ ኃፍረት፣ ብቻ የሚያናግር ጸሎት አይሉት እብደት ተጠናውቶታል። በጣት ጥንቆላ የሚያናግር። በስውር ማህበር መሥርቶ የብሶቱን ጽዋ ይቃመሳል፤ መንግሥትን ያማል፤ እርስበርስ ይናቆራል። ጥላቻና ውሸት ዘርቶ መልካም መከር ይጠብቃል። መንግሥት፣ ከሠረገላ ቊልፍ በባሰ ምትሃት፣ ዜጋ ስልኪትን ወደ ጆሮው ሲያስጠጋ በስውር፣ ወዳጅ መስሎ ተጠግቶ ያደምጣል፤ ሲሻው መስመሩን ቊርጥ … አኳኋንህ ማንነትህ የዐይንህ ቀለም አልተስማማኝም። ሃሎ? … ኧረ ሃሎ! … ሄሎ? ሃ..ሎ.. ሃ…!

ጥንት ሥራ የፈታ መነኲሴ ነበር ቆቡን ቀዶ የሚሰፋ። በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ቅዳሴ የሰለቸው ቄስተዲያቆን፣ ጥግ ይዞ ሴልፎኑን እሽሩሩ ይላታል። ብሔሩ ቅርብ እያለለት እግዜሩ ጋ ምን አደከመኝ ብሏል! ሥራ የፈታ ጴንጤ የራሱን ምስል ይስላል፤ እግዚአብሔር ቴክስት አረገልኝ ይላል። ከሚያብረቀርቅ ከሚጤስ ከሚያስገመግም የመድረክ ተራራ፣ ሰላም ነው! ሁሉ ሰላም ነው! ይላል። እግዚሐርን፣ አንዴ ያዝልኝ፣ ስልክ መጣብኝ!

_________

በአሜሪካ የመናፈሻ ወንበር ላይ ዛፍ ተተግኖ የተቀመጠ ሰው መሳይ ከሩቅ አልፎ አልፎ ይታያል። በቀረቡ ቊጥር ከላባ የቀለለ ድምጽ ያሰማል። ሁለት ሆነው እያወሩ ነው? ጒድ ነው፣ የሚያወራው ብቻውን ነው! እየጸለየ ስለሆነ እንዳያቋርጥ፣ እንዳያፍር፣ ለምን ታየኛለህ እንዳይል ትክ ብሎ ላለማየት ኮሽታ ላለማሰማት ዝግ ይላል። ነገረ ቃሉ ግን ሲደመጥ ጸሎት አይመስልም። ከውቃቢው ጋር እያወራ ነው? ፈረንጅም እንደ እኛው! ውቃቢ አለው? አላስችል ብሎት ገልመጥ ሲል ነገሩ ሌላ ነው። ለካንስ ወሬው ከጒትቻ ስልክ ጋር ነው፣ ከሐብል እና ከአምባር ጋር ነው።
ከበስተጀርባዬ “ሄሎ!” ሰማሁና። ማነው የግዜር ሰላምታ የሚያቀብለኝ ብዬ ዞር ስል፣ ነገሩ ሌላ ነው። ሌላ ቀን፣ ጀርባውን ሰጥቶኝ የሚራመድ፤ “ሄሎ!” አለ። እያወራ ስለሆነ አላቋርጠውም ስል፣ ቀድሞ አይቶኝ ኖሮ፤ እኔን ነው! ጒድ ነው!
ጎን ለጎን ይራመዳሉ፣ የማይታይ ወዳጅ ይሁን ባላንጣ መሓላቸው ገብቷል። ባንድ ቤት ይኖራሉ፣ ባንድ መኪና ይጓዛሉ፣ ካንድ ገበታ ይቆርሳሉ፣ ባንድ መኝታ ያድራሉ፣ ቤተክርስቲያን አብረው ይሳለማሉ። ተንጠራርተው ተላልፈው ከወዲያ ወዲህ ያወጋሉ፤ ጒድ ነው!

© ከ “ዘንድሮስ አልዋሽም” 2002 ዓ.ም. / በመጠኑ ታርሟል። © 2013 by Mitiku Adisu. All Rights Reserved.

Share this post