የሀዲስ አለማየሁ የሱዳን ቆይታ

የሀዲስ አለማየሁ የሱዳን ቆይታ

በጎጃም ክፍለ ሃገር ጎዛመን ወረዳ እንደዶም በተባለ መንደር 1902 የተወለዱት ክቡር ሀዲስ ዓለማየሁ የስድስት ዓመት ልጅ እንዳሉ በእናታቸው አባት ሥር ሆነው ዜማን ማጥናት ጀመሩ።በደብረኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና በዲማ እየተዘዋወሩ ለአስራ ሁለት ዓመታት ቅኔንና ዜማን አጥንተው በአሥራ ስድስት ዓመታቸው ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በ1918 ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በስዊድን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት በኋላም በራስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ቀጥሎም በጎጃም ዳንግላና ደብረማርቆስ በአስተማሪነት አገልግለዋል።በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር፤ የጎጃም እንደራሴ ከነበሩት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለስላሴ ስር በመሆን ትግራይ ሰለክለካ (በሽሬ እና በአክሱም መካከል) ግንባር ዘመቱ።ሰለክለካ ላይ በተደረገ ጦርነት የራስ እምሩ ጦር ድል ሳይቀናው ቀረ። የጣሊያን ጦር ወደ ደቡብ አቅጣጫ እየገፋ ሲሄድ የኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግስት መቀመጫ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሆን ተወሰነ። በጦርነቱ ለመሸነፍ ምክንያቱ የመሣሪያ እጥረት ነው ተብሎ በመታመኑ ሀዲስ፤ እንግሊዝኛና አረብኛ መናገር ስለሚችሉ በተመረጡት በአቶ ዩሐንስ አብዱ በሚመሩ 50 ወታደሮች እና በቅሎዎች ታጅበው ወደ ሱዳን በመሄድ ስንቅ፣ መድኃኒትና ትጥቅ እንዲያመጡ ተላኩ። በሱዳን የነበራቸውን ቆይታ ትዝታ በተባለ መጽሃፋቸው የተረኩትን ትረካ እዚህ ላይ ቀንጨበን አቅርብነዋል።

ዘሪሁንና እኔ ሱዳን የቆዩንበት ጊዜ፥ ከግንቦት 1928 መጀመሪያ እስከ ነሀሴ 1928 መጨረሻ ግድም፥ አራት ወራት ያክል ነበር። ካራቱ ወራት ሁለቱን ወራት ያክል ገዳሪፍ፥ የቀረውን ካርቱም ነበር። ካራቱ ወራት ሁለቱን ወራት ያክል ገዳሪፍ፥ የቀረውን ካርቱም ነበር የቆዬን።ገዳሪፍ አቶ ዘውዴ በሰጡን ቤት ካስራ አምስት እስከ ሃያ ቀናት ያክል ከቆዬን በኋላ፥ ምንም እንኩዋ እሳቸው አፋቸውን አውጥተው ባይናገሩ እኛ ከያዝነው ሌላ እንግዳ የሚቀበሉበት ቤት ያልነበራቸው መሆኑን በማየት፥ እዚያው ባጠገባቸው አንድ ትንሽቤት ተከራይተን ወጣን።ግን ከግቢያቸው ብንወጣም ገዳሪፍን እስከለቀቅንበት ቀን ድረስ፥ ያቶ ዘውዴ ርዳታ አልተለየንም። እንኩዋንስ ጠይቀናቸው፥ ሳንጠይቃቸው እሳቸው አውቀው የሚያደርጉልን ርዳታ ብዙ ነበር ።

ካቶ ዘውዴ ሌላ፥ ገዳሪፍ በነበርንበት ጊዜ አይነተኛ ረዳታችን አቶ ሚካኤል በኪት ነበሩ። በተለይ ፥ እኔ ሬዲዮ ስላልነበረኝ፥ ስለኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ሁኔታም ሆነ፥ በጠቅላላው ስለ አለም ሁኔታ የማውቀው ካቶ ሚካኤል በኪት ጋር በመነጋገር ነበር። መቸም ፅህፈት ቤታቸውን በቀን አንድ ጊዜ ሳልረግጠው ውዬ አላውቅ! ታዲያ፥ በሄድሁ ቁጥር፥ በደስታ ተቀብለው ቡና እየጋበዙ በየጊዜው ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ውስጥ የያዙዋቸውን ክፍሎች፥ እንዲሁም ለአለም ማህበር አባል ከሆኑት መንግስታት እነማን ኢትዮጵያን ደግፈው በኢጣሊያ ላይ ቅጣት እንዲጣልባት አሳብ እንዳቀረቡና እነማን ቅጣቱን እንደተቃወሙ ነግረውኝ ፥ ተስፋ እንዳልቆርጥ አበረታተውኝ እሄዳለሁ ። ጃንሆይ ቤተሰባቸውንና ብዙ መኩዋንንታቸውን ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳቸውን ከዚያም ወደ እንግሊዝ አገር የሚሄዱ መሆናቸውን መጀመሪያ የሰማሁ ካቶ ሚካኤል ነበር ።

አቶ ሚካኤል በኪት፥ ምንም እንኩዋ ሱዳን ተወልደው አድገው እዚያ በክብር የኖሩ ቢሆኑ፥ የኢትዮጵያ ነፃነት መጥፋት በጉያዋ አቅፋ የናትነት ፍቅርዋን እየመገበች እንዳሳደገቻቸው ኢትዮጵያውያን አገርወዳዶች ሁሉ ነበር ያሳመማቸው። ሙሶሊኒ የጦር ሰራዊቱ አዲስ አበባ የገባበትን ቀን አስታውቆ ፡ ከዚያ ቀን ጀምራ ኢትዮጵያ ነፃ አገር መሆዋ ቀርቶ የጣሊያን ቅኝ ግዛት እንደሆነች ማስታወቁን ሰምተው የነገሩኝ እለት፤ ከኔ ጋር ያለቀሱትን መሪር ልቅሶ አልረሳምው፤ አብሮኝ ይኖራል ።

ኢትዮጵያ የጣሊያን ቅኝ ግዛት መሆንዋን ሙሶሊኒ ባዋጅ ካስታወቀ በሁዋላ፤ የኢትዮጵያ የክብርዋና የነፃነትዋ ምልክቶች የሆኑት ነገሮች ሁሉ ተዋረዱ ፤ወደቁ። በገዳሪፍ ግዛት መስሪያ ቤት ያስቀመጥሁት የኢትዮጵያ ብርም ከነፃነትዋ ምልክቶች አንዱ ስለነበረ፤ከኢትዮጵያ ነፃነት ጋር አብሮ ወደቀ ፤ ዋጋ አጣ ! ሳስቀምጠው ከሱዳንአንድ ላንድ የነበረው ፤ ባንድ ጊዜ በግማሽ ወረደ። እዚያ ላይም አልቆመ፤ በዬቀኑ እየወረደ ፥እየወረደ ሄዶ በመጨረሻ ፈላጊ አጣ።የሚፈልጉት አንዳንድ ነጋዴዎች ቢኖሩ ፤ ለመገበያያ ገንዘብነቱ ሳይሆን ፥ ተነጥሮ ጥሩውን ብር ለጌጣጌጥ መስሪያነቱ ብቻ ሆነ። ያን ጊዜ ወደ ሱዳን የተላክሁበት አላማ ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ታዬኝና አዘኔ ከኔ አልፎ አቶ ሚካኤልንና አቶ ዘውዴን አስጨንቆዋቸው ፤ እኔን ለመርዳት ያላሰቡትና ያልሞከሩት ነገር አልነበረም።

አንድ ቀን፤ አቶ ዘውዴን ጭምር አቶ ሚካኤል በኪት ጠርተውን አፅህፈት ቤታቸው ገብተን እንደ ተቀመጥን፤ «የሱን የወንድማችንን ችግር የሚያቃልል መስሎ የታዬኝን አሳብ እንድገልፅልዎና እንድንመካከርበት ነው ፥ ዛሬ እርስዎ ጭምር እንዲመጡ ያስቸገርሁዎ» አሉዋቸው ‘ «የሱን የወንድማችንን» ሲሉ ወደኔ እያመለከቱ። «ምንጊዜም ቢሆን ወደስዎ መምጣት በስራዎ ጣልቃ ገብቸ እንዳላስቸግርዎ እሰጋለሁ እንጂ ለኔስ ደስታ ነው ። ይልቁንም የሱ ችግር የሚቃለልበት መንገድ ከተገኘ እንኩዋንስ እርስዎ ዘንድ ሩቅ አገር ብሄድ አይከብደኝም» አሉ አቶ ዘውዴ ።

“እንደያውሚቁት እዚህ እኛ ዘንድ ያስቀመጠው ገንዘብ ዋጋ ስላጣ፥ እንደታሰበው ኢትዮጵያ ውስጥ ከጠላት ጋር ለሚዋጉት ወታደሮች ልብስና መድሀኒት ገዝቶ ሊወስድላቸው ላይችል ነው ማለት ነው። ታዲያ፥ እዚያ (ኢትዮጵያ) ያሉት ኢትዮጵያውያን ለጋራ አገራችን ነፃነት ህይወታቸውን ሲሰጡ ፥ እኛ እዚህ ያለነው ኢትዮጵያውያን ለመድሀኒትና ለልብስ የሚሆናቸው ገንዘብ እንደያቅማቸው አዋጥተን መስጠት ይበዛብናል?  ለኔ እንደሚመስለኝ፥ ገዳሪፍ የምንኖረው ኢትዮጵያውያን ብዙ ስለሆን፥ ሴት ወንዱ ልጅ አዋቂው እንደያቅሙ ቢያዋጣ ይህን ዋጋ ያጣ ገንዘብ፥ ይህን እንዶ ጠፋ የሚቆጠር ሰላሳ ሺህ ብር ሰብስቦ መተካት ይቻላል ።ስለዚህ ፥ ይህን አሳብ መሰንበቻውን ብቻየን ሳሰላስል ከሰነበትሁ በሁዋላ ነው፥ ከሰዎቹ ጋር ፥ ከኔ የተሻለ ግንኙነት ያለዎ በመሆንዎ ፤ ከርስዎ ጋር እንድንመካከርበት የፈለግሁ።”

«ማለፊያ አሳብ አስበዋል ። ፈቃደኞች ስንት እንደሚሆኑ አናውቅም እንጂ ሁሉም ፈቃደኞች ከሆኑማ ብዙ ገንዘብ መሰብሰብ ይቻላል። አቅም የሚያንሳቸው ስለሚኖሩ ፡ እነሱን ብንተዋቸው እንኩዋ ፥ ከሚችሉት ሰላሳ ሺህ የሱዳን ብር መሰብሰብ ባይቻልም፡የኢትዮጵያን ብር ለጌጣጌጥ ስራ ገዝተው ለሚነግዱ አትራፊ ነጋዴዎች ባወጣው ዋጋ ሸጦ ፡ የሚጐድለውን የሚያሙዋላ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚቻል ይመስለኛል። ለማናቸውም፥ የሁለታችሁም ፈቃድ ቢሆን ስለ ብሩ ሽያጭ ካንዳንድ ነጋዴዎች፥ ስለመዋጮው ካንዳንድ ተደማጭነት ካላቸው ያገራችን ሰዎች ጋር ተነጋግሬ፥ አሳባቸውን ካወቅሁ በሁዋላ እንደገና እንነጋገርበት» አሉ አቶ ዘውዴ ።

«ማለፊያ ነው ። ብቻ ስለ ብሩ ሽያጭ  ካንድ ብቻ ሳይሆን በርከት ካሉ ነጋዴዎች ጋር ቀስ ብለው ውስጥ ለውስጥ ተነጋግረው እያንዳንዳቸው ያቀረቡትን ዋጋ ካወቁ በሁዋላ ፥ የስምምነት ቃልዎን ከመስጠትዎ በፊት እዚህ እንደገና ብንነጋገርበት ይሻላል። ይህን ያልሁበት ምክንያት ፥ እኔም የማውቃቸው አንዳንድ ነጋዴዎች ስላሉ፡ መጠየቄ አይቀርምና ለሁለታችን የቀረቡትን ዋጋዎች አመዛዝነን መምረጥ እንድንችል ነው» ብለው አቶ ሚካኤል አሰናበቱን። ያነለታ ጠፍቶ የነበረው የመልእክቴ አላማ እንደፊቱ ጠርቶና ጎልቶ ባይሆንም፥ ደብዘዝ ብሎ በሩቅ ታዬኝና ደስ እያለኝ ወደ ቤቴ ተመለስሁ።

አቶ ዘውዴ ፡ ላቶ ሚካኤልና ለኔ እንደ ነገሩን ከብር ነጋዴዎችና ስለ መዋጮው ከኢትዮጵያውያን ጋር በመነጋገር ላይ እንዳሉ፥ አንድ ቀን ፥ አቶ ሚካኤል ፅህፈት ቤት ስደርስ አዲስ ወሬ ቆዬኝ።

«ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛታቸው መሆንዋን ካስታወቁ በሁዋላ፥ መገበያያው ገንዘብ ፥ በኢትዮጵያ ብር ፋንታ የጣሊያን ሊሬ እንዲሆን አውጀው፥ አሁን ብሩን ከኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፥ በወሰንዋ ባሉት አገሮች የሚገኘውንም በውድ ዋጋ እገዙ መሰብሰብ ስለ ጀመሩ፥ ለጊዜው የኢትዮጵያ ብር ዋጋ ከፍ እያለ መሄዱን ሰማሁ ። ስለዚህ፥ ከሱዳን ብር ጋር አንድ ላንድ በሚለወጥበት ደረጃ ከደረሰ ፣ ‘ይዋል ይደር’ ሳትል ቶሎ ብትሸጠው ይሻላል ። ይህን የምልበት ምክንያት ጣሊያኖች መሰብሰቡን ሲያቆሙ የብር ዋጋ ተመልሶ መውደቁ የማይቀር መሆኑን ስለማውቅ ነው» አሉኝ አቶ ሚካኤል። እኔም ሳላመነታ ባሳባቸው ተስማማሁ።

እውነትም በጥቂት ቀናት ውስጥ፥ አቶ ሚካኤል እንደነገሩኝ፥ መተማን የያዙት ጣሊያኖች የኢትዮጵያን ብር እየፈለጉ በውድ ዋጋ መግዛታቸው ገዳሪፍ በሰፊው ስለተወራ፥ ቀደም ብለው አቶ ዘውዴ ያነጋገሩዋቸው የብር ነጋዴዎች አንዱን የኢትዮጵያ ብር አንድ የሱዳን ብር ካንድ መሀለቅ (ፒያስትር) ሂሳብ ገዙት። አስር መሀለቅ (ፒያስትር) አንድ የሱዳን ብር ስለሆነ ሰላሳው ሺህ የኢትዮጵያ
ብር ሰላሳ ሶስት ሺህ የሱዳን ብር ሆነ ማለት ነው። ስለዚህ ያን ሰላሳ ሶስት ሺህ የሱዳን ብር ባንክ አግብቼ «ኧሁ !» አልሁ ፤ አረፍሁ !

አቶ ዘውዴ ፣ ስለ መዋጮው ከኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጉት ንግግር ደስ የሚያሰኝና የተረጋገጠ ተስፋ ማግኘታቸውን ላቶ ሚካኤልና ለኔ ነግረውን ነበር ። ገዳሪፍ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ሁሉ፥ የቀን ሙያተኞች እንኩዋ፥ ያንዳንድ ቀን የሙያቸውን ለማዋጣት ቃል ገብተው ነበር ። በተለይ ሴቶች ፥ ወርቃቸውንና ሌላ ጌጣቸውን እዬሸጡ ለማዋጣት ያስታወቁት ገንዘብ ሲታይ፥ መዋጮው ከታሰበው በላይ የሚገመት ነበር ። ነገር ግን፥ ያልታሰበ አጋጣሚ ደርሶ ፥ የኢትዮጵያ ብር ከቀድሞ ዋጋው እንኩዋ ፤ ከፍ ብሎ ስለተሸጠ፥ አቶ ዘውዴ ለሁሉም ምስጋናችንን ገልፀው መዋጮው የማያስፈልግ መሆኑን እንዲያስታውቁልን አደረግን ።

ራስ እምሩ ጎሬ መድረሳቸውን ፣ አቶ ሚካኤል በኪት እዚያ በነበረው የቆንስላቸው መስሪያ ቤት በኩል አውቀው ነግረውኝ ነበር ።
ነገር ግን ፥ ምንም እንኩዋ ፣ አቶ ዮሀንስ ደርሶባቸው ከተገናኙ ፣ እኔ ገዳሪፍ መሆኔን ሳይነግራቸው እንደማይቀር የታወቀ ሲሆን ፣ እስከዚያ ድረስ ከራስ የደረሰኝ መልእክት አልነበረም ። በመሀከሉ የግል ገንዘቤ እያለቀ ስለሄደ ፥ ዘሪሁንና እኔ እንዴት አድርገን መኖር እንደምንችል በጣም ያሳስበኝ ጀመር ። ወደ ሱዳን እንድንሄድ ስንታዘዝ ፣ የስድስት ወር ደመወዜን ፣ ከሶስት መቶ ብር በላይ ተቀብዬ ነበር ከራስ የተሰናበትሁ ። እንዲሁም ሁለቱን በቅሎዎችን ገላባት ሸጨ ፣ ከሞላ ጎደል ያኑ ያክል የሱዳን ብር አግኝቻለሁ ።

Share this post