ሮብ ዕለት ነው ጆሃንስበርግ የገቡት።ስማቸው ፋጢማ ሄንድሪክስ፣ማንድላ ማንዴላ፣ረአዝ ሙላ፣ካሪ ሼልቨር፣ዛህራ ሱማራ፣ዙኪስዎ ዋነር ይባላሉ። እነዚህ የደቡብ አፍሪካ የመብት ተሟጋቾች፥ከተለያዩ ሀገራት ተወጣጥተው፥ በመርከብ በመሣፈር ወደ ጋዛ ሠርጥ ካመሩት መካከል ናቸው። በጋዛ ነዋሪዎች ላይ የተጣለው ዕገዳ እንዲነሳ ለመጠየቅ እና እንዲሁም፥ የምግብ እርዳታን ለማድረስ። በእስራኤል ጦር፥ ወደ ሀገሪቱ የውሃ ግዛት ከመድረሳቸው በፊት፥ ተይዘው ለበርካታ ቀናት ታስረዋል።ሰኞ ለት እስኪፈቱ ድረስ።
ልክ ከአውሮፕላን እንደወረዱ፥ ስድስቱ ግለሰቦች ያደረጉት ነገር፥ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ነው።ማንድላ፣ የማንዴላ ልጅ ልጅ፥ እንደሚለው የእስራኤል ጦር በተለይ እነሱ ላይ ያተኮረባቸው፥ የሀገራቸው መንግስት በዓለም አቀፍ የፍትህ ችሎት ያቀረበውን ክስ ምክንያት በማድረግ ነው፡፡እንደሚታወሰው፥ ከሁለት አመት በፊት እስራኤል ከሐማስ ጋራ በምታደርገው ጦርነት የዘር ማጥፋት ፈፅማለች በሚል ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የፍትህ ችሎት ክስ ከፍታለች፡፡
ማንድላ ማንዴላ፣ ሲናገር እስራኤልና የአፓርታይድን ስርዐት በማያያዝ ነው። የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ እንደሆኑ አድርጐ።በ1970ዎቹ በደቡብ አፍሪካ፥ የአፓርታይድ ስርዐት ላይ ይደረግ በነበረው ትግል፥ ተዋናይ የነበሩት ታጋዮች የፍልስጤም ሕዝብ ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና፥ እነርሱ ላይ ይደርስባቸው ከነበረው ጋር አዛምደው ያዩት ነበር።በዚህ ላይ፥ የእስራኤል መንግስት፥ በነጮች የበላይነት ይመራ ከነበረው የደቡብ አፍሪካ አስተዳደር ጋር ለመወዳጀት ይጥር ነበር። ከደቡብ አፍሪካ ፀረ አፓርታይድ መሪዎች መካከል የነበሩት ዴዝሞንድ ቱቱ ከፍልስጤም መሪዎች ጋር ግንኙነት የጀመሩት በ1966 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነበር። የመጀመሪያው ኢንቲፋዳ እንደ እእኤ1989 ሲካሄድና የነጮቹ የደቡብ አፍሪካ አስተዳደር ከመውደቁ አንድ አመት በፊት፥ ዴዝሞንድ ቱቱ ወደ ዌስት ባንክ አምርተው ነበር። በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ፥ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የሚደረገውን ወከባ ና አፍጦ አግጦ የሚታየውን መድልዎ፥ ኮንነዋል።በ2012 ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በዌስት ባንክ እየተፈፀመ ያለው ግፍ፥ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዐት ከተፈፀመው የከፋ መሆኑን አስምረውበታል። ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ቀደም ብሎ፥ በ1997 ከያሲር አራፋት የተላኩ ተወካዪችን፥ ማንዴላ ፕሪቶሪያ ላይ ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል። በወቅቱም ፥ “የፍልስጤም ህዝብ ነፃ ካልሆነ ነፃነታችን የተሟላ እንደማይሆን ጠንቅቀን እናውቃለን።” የሚል ንግግር አሰምተዋል። እ.ኤ.አ. በ 1999 ማንዴላ መካከለኛው ምስራቅን ሲጎበኙ እስራኤልን እና የፍልስጤም ግዛቶችን ጎብኝተዋል። ጋዛ በደረሱበት ወቅት ‘ከአገሬ ሰዎች መካከል እንዳለሁ ይሰማኛል’ ብለዋል።
የፍልስጤማውያን የዛሬ ሁኔታና የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድን ዘመን የሚያመሳስለው ብዙ ሁኔታ አለ ትላለች ሶፊ ዱሎክ የተባለች በቱሉዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር፤ መሬታቸውን የተነጠቁበት ሁኔታ፣ የሁለቱም ሀገሮች የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ቅርስ መሆናቸው፣ ሌላውን በማፈናቀል ነጮችን ማስፈር ፣ የተጨቆኑት ሕዝቦችን ዝቅተኛ አድርጐ ማቅረብ በሁለቱም ሀገሮች ላይ የተስተዋለ ነገር ነው። “በእስራኤል እና በፍልስጥኤማውያን ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጥቃት እና ጦርነት በምዕራባዊም ሆነ በምስራቅ አገሮች መካከል በተመሳሳይ ሁኔታ አይታይም። ለአንዱ ወገን፥ ናዚዝም የተወው ቁስል ፥ በሌላ በኩል ቅኝ ግዛት እና ኢምፔሪያሊዝም የፈጠረው መዘዝ”ይላል ማቴው ሬይ የታሪክ ባለሙያ።
ኢትዮጵያውያን ስለ ፍትህ ያለን አመለካከት የወረደ መሆኑን ከደቡብ አፍሪካውያኑ ድርጊት መረዳት ይቻላል። እስራኤል ናዚ ጀርመኖች ከ80 ዐመት በፊት የፈጸሙባትን ጭፍጨፋ በጠራራ ጸሐይ በአሜሪካ ድጋፍ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ ፈጽማለች። ሰብአዊ መብት ተሙዋጋቾችን በማሰር ጋዜጠኞችና እርዳታ አቅራቢዎችን በመግደል። ህጻናትን ብቻ ከ 25ሺህ በላይ ጨፍጭፋለች። 80 በመቶ ጋዛ ሰው እንዳይኖርባት አድርጋ አውድማለች። ማንም አይጠይቀኝም ነው። እግዚአብሔርም እንኳ። ኢትዮጵያውያን ልብ የለንም ላልኩት፣ ቴዲ አፍሮ ተከፍሎት ሊያዝናና የተጉዋዘው ወደ እስራኤል ነው። ዶር ፍቅሬም። ተጽእኖ ፈጣሪዎች ካልተጠነቀቁ በስተቀር ሳያስቡበት ወይም ገንዘብ ኣሳስቱዋቸው ታሪክ ስማቸውን ያጎድፋሉ። ደቡብ አፍሪካዎቹ መስዋእት ከፍለው አላማቸውን ከግብ አድርሰው መመለሳቸው ደስ ይላል።