ወግ አጥባቂው አክቲቪስት ቻርሊ ከርክ ከተገደለ ከጥቂት ቀናት በሗላ፥ ዶናልድ ትራምፕ፥ አንቲፋ የተባለውን የግራ ዘመም፥ እንቅስቃሴ፥ በአሸባሪነት ፈረጁት።ፕሮፌሰር ማርክ ብሬይ የጥቃት ኢላማ የሆኑት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር። በሩትጌዝ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑትና በስፔን ታሪክ ላይ ብዙ መጽሃፎችን የፃፉት ይህ ምሁር Antifa: The Anti-Fascist Handbook የሚል መጽሐፍ በ2017 አሳትመዋል። “በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ የነጭ የበላይነትን ሰባኪዎችና አክራሪዎች የሚፈፅሙት ጥቃት እየጨመረ ቢሆንም ብዙዎች ፋሺዝም ላይመለስ ከስሟል ብለው ያምናሉ” ይላሉ መግቢያው ላይ ባሰፈሩት ፅሑፋ። መፅሐፉ ከተፃፈ ከአስር አመት በኃላ ደራሲውና መፅሐፋቸው የትራምፕ አስተዳደር በትር አርፎባቸዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው። ፋሺስት መባላቸው ያበሳጫቸውና በትራምፕ መመረጥ የልብ ልብ ያገኙት፥ የነጭን የበላይነት አቀንቃኞች፥ በማህበራዊ ሚዲያና በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን፥ ስድቦችና ዘለፋዎችን ሲያወርዱባቸው ነው የከረሙት፤ የዚህ መፅሐፍ ደራሲ ላይ። እንደ ሐዋርያ አድርገው ያዩት በነበረው ቻርሊ ከርክ ግድያ በመናደድ እና ጥፋቱን ያለ ምንም ማስረጃ በግራ ዘመም ቡድን ላይ ለማላከክ የጏጉ የትራምፕ ደጋፊዎች፥ ትኩረታቸውን እነዚህ ምሁራን ላይ አነጣጠሩ። በቻርሊ ከርክ የተቋቋመው የፖለቲካ ተቋም ተርኒንግ ፖይንት (Turning Point USA) አባላት የሆኑ የተወሰኑ ተማሪዎች ብሬይ “ዶ/ር አንቲፋ” የሚል ቅጽል ስም በመስጠት ከማስተማር ሥራቸው እንዲባረሩ አቤቱታ (ፔትሽን) ማሠባሰብ ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ፥ ምሁሩ፥ ከተለያየ አቅጣጫ የሞት ዛቻ ፤ ይደርሳቸው ጀመር። በዚህም ምክንያት፥ በአካል ማስተማር አቁመው ኦንላይን ትምህርት ለመስጠት ተገደዱ ።ይባስ ብሎ፤ የቤት አድራሻቸው እና የቤተሰባቸው የግል መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተሠራጨ።
አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱት ብሬይ በስፔን እየኖሩ በኦንላይን ላይ ለማስተማር አስበዋል። ወደ ስፔን ለመጓዝ በሞከሩበት ጊዜ በአየር መንገዱ ተከልክለው መጉላላታቸውን ተናግረው ነበር።፣ በኋላ ላይ ግን ተፈቅዶላቸው እዚያው ሩትጌዝ ዩኒቨርሲቲ መምህር ከሆኑት ባለቤታቸው እና ሁለት ልጆች ጋር በመሆን ለመውጣት ችለዋል።
“ስራዬ ማስተማር ነው። ከአንቲፋ ቡድን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም።ምንም አይነት ተሳትፎም አድርጌ አላውቅም። ጥናት እና ምርምር ካደረኩባቸው ርዕሶች በመነሳት እኔም የእንቅስቃሴው አካል እንደሆንኩኝ አድርጐ ለመሣል የሚደረግ ጥረት አለ። ነገርግን ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰሩ አክለዋል።