ኢትዮጵያዊነትና ጀርመናዊነት

ኢትዮጵያዊነትና ጀርመናዊነት

ከኢትዮጵያዊት እናቷና ከጀርመናዊ አባቷ የተወለደች ትዕግስት ሰላም ያደገችው በተለያዩ ሀገራት ማለትም በናይጄሪያ፣ በአርጀንቲናና በዋነኝነት በጀርመን ነው፡፡ One Drop: Shifting the Lens on Race (አንዲት ጠብታ፣ ዘርን በተለየ ምልከታ) የሚል ርእስ ባለው መጽሐፍ ውስጥ ጽሑፎች ካበረከቱት አንዷ ናት፡፡ መጽሐፉ የዘር ክፍፍሎችን ውስብስብነትና ሰዎች ጥቁርነትን በህይወትና በተሞክሮአቸው የሚኖሩባቸውን የተለያዩ መንገዶች ይመረምራል፡፡

ዘርሽ ምንድን ነው ብባል መልሴ ጥቁር ሲሆን፣ በባህል ረገድ ራሴን የምቆጥረው እንደ ኢትዮጵያዊትና ጀርመናዊት/ አሜሪካዊት ነው፡፡ የፖለቲካዊ ዐውድ ካላጣቀሰ በቀር ፣ ራሴን ጥቁር አድርጌ አላቀርብም፤ ለምን ቢባል ትርጉሙ ራሱ ምን እንደሆነ ስለማይገባኝ፡፡ ለመሆኑ የጥቁር ባህል ምንድን ነው? አፍሪካዊ ባህል ነው ወይስ ካሪቢያዊ? ለኔ ባህል ሲባል በበእቅጭ የታወቀ ነገር ሲሆን፣ እኔ ደግሞ ባለ ብዙ ባህል ነኝ፡፡ ስለዚህም ራሴን ጥቁር አድርጌ ሳቀርብ ፖለቲካዊ መልዕክት እያስተላለፍኩ ነው፤ እንዲሁ ባህላዊ ዝቅተኛነት ለማመልከት እየሞከርኩ አይደለም፡፡

አባቴ የተወለደው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በ1945 ሲሆን በፓስፖርቱና በልደት ሰርተፊኬቱ ላይ የስዋስቲካ (የናዚ) አርማ አሁንም አለ፡፡ እናቴ የጣሊያን ጊዜና የአጼ ኃይለሥላሴ ዘመንን አይታለች፡፡ አባቴ በጀርመናዊነቱ፣ እናቴም በኢትዮጵያዊነቷ በጣም ይኮራሉ፡፡ ማንነትን በተመለከተ ለራሳቸው ከፍ ያለ ግምት ይሰጣሉ፡፡ ይሁንና ዘርን አስመልክቶ ዘራፍ የሚሉ ዓይነት አልነበሩም፡፡ ሌላውን ሰው ሁሉ ቂል አድርገው ነበር የሚቆጥሩት፡፡ እናቴ በዚህ ረገድ ዋዛ የማታውቅ በመሆኗ ይህ ለእኔ ጥሩ አርአያ ሆኖኛል፡፡ ምግብ ቤት ውስጥ መቀመጫ ማግኘት ሳትችል ስትቀር፣ አንድ ነገር ትናገራለች ወይም ለምግቡ ሳትከፍል ትወጣለች፡፡ አባቴ ወደ ምርጫ ጣቢያ ይዞኝ የሄደው በአስራ አንድ አመቴ ነበር፡፡ በየቀኑ ዓለም ዓቀፍ ዜና ቁጭ ብዬ የማዳመጥ ግዴታ ተጥሎብኝ ነው ያደግኩት፡፡ በመሆኑም እኔና ወንድሜ ከፖለቲካው ዓለም ጋር የተዋወቅነው ገና በለጋነታችን ነበር፡፡ ናይጄሪያ ሁለት ዓመት፣ አርጀንቲና ሶስት ዓመት ፣ ጀርመን አስር ዓመት በአሁን ወቅት በአሜሪካ በመካከል ሄድ መጣ እያልኩ ለአስር ዓመት መኖሬም ለተለያዩ ተሞክሮዎች እንድጋለጥ አድርጎኛል፡፡

ወደ ጀርመን ስንሄድ አምስት ዓመቴ ነበር፡፡ የአባቴ ቤተሰቦች “እንዲህ ነውና፣ መቼም ሚስቴ ይህቺ ናት፣ እዚህ ላኖራት ነው እያልከን አይደለም” ነበር ያሉት፡፡ ሴት አያቴና አክስቴ ነገሩ ሁለት ዓመት አልዋጥ ብሏቸው ሲተናነቃቸው ቆይቶ ነበር ምን ይደረግ ብለው የተቀበሉት፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ማየት በእጅጉ የሚያም ነበር፡፡ ይሁንና ለአባቴ ያለኝን ፍቅርና አክብሮት የላቀ እንዲሆን አድርጎኛል፡፡ ለእኛ ሲል ቤተሰቡን ለመሰዋት ወደኋላ የሚል አልነበረም፡፡

በጎረቤት ልጆች “እናትሽ ግን ምን ሆና ነው ጥቁር የሆነችው?” እየተባልኩ ነው ያደግኩት፡፡ “እኔም እኔ እንጃ፤ ጥቁር ናት እንዴ?” ለእኔ ኢትዮጵያዊ እንደሆነች ነው የሚገባኝ” ብዬ እመልሳለሁ፡፡ አንዳንዶቹ በጨዋታቸው ሊያሳትፉኝ አይፈቅዱም ነበር፡፡ ይሁንና በምን ምክንያት እንደነበር አላስተዋልኩም ነበር፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰው እንደ ብርቅ ይመለከተኝ ነበርና በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ነበርኩ፡፡ ጸጉሬም ረዥም ትልልቅ ሆኖ አምር ነበር፡፡ በ12 እና በ13 ዓመቴ አንዳንድ ነገሮች ግልጽ እየሆኑልኝ መጡ፡፡ አፍላ ወጣትነት ዓለምን መረዳት የሚጀመርበት በመሆኑ ፖለቲካዊ ንቃት ማዳበር ጀመርሁ፡፡ በ16 ዓመቴ ፣ ለእናቴ እንዲህ አልኳት፣ “የሆነ ቦታ መሄድ አለብኝ፡፡ አለኝታ እንዲሰማኝ የሚያደርግ ስፍራ እፈልጋለሁ፡፡ እኔን የሚመስሉ ወይም እንደእኔ ዓይነት ሰዎች እሻለሁ ይህም ብቻ ሳይሆን ምርጫዬ አርቲስት መሆን ነበርና ጀርመን አገር ብዙ ዕድሎች እንደማላገኝ አውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ አገር መለወጥ እንደሚያስፈልገኝ ተሰማኝ፡፡ ይህ ለእናቴ ቀላል ነገር አልነበረም፤ ሆኖም ሁኔታዬን በመረዳቷ በጄ አለችኝ ፡፡ ስለዚህ ክልስ ለሆነ ሰው የናት ጥቁር መሆን ምን ያህል መታደል እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ፡፡ ጀርመን ውስጥ ከነጭ እናቶች ተወልደው ጥቁር አባታቸው አብረዋቸው የሌሉ ልጆችን ስለደረሱባቸው አሰቃቂ ነገሮች ሰምቻለሁ፡፡ ጥቁር ከመሆን ጋር አንዳችም ዝምድና የላቸውም፡፡ እንደ ሁለተኛ ዜጎች እየተቆጠሩና በጥቁር ቆዳቸው ምክንያት ለከፋ ዘረኝነት የተጋለጡ ሲሆኑ አለኝታ የሚሆናቸው ሰው የለም፡፡ ለእኔ እናቴ አይዞሽ ባይ ሆና ከአጠገቤ አንዳለች ነበር የሚሰማኝ፡፡

በተጨማሪም እስከዚያች ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያዊና ጀርመናዊት ስለመሆኔ አንዳችም ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ ከዚያ መኖሪያዬን በአሜሪካ ደቡብ ሳክራሜንቶ ሳደርግ ሰው ሁሉ እንደጥቁር ነበር የሚያየኝ፡፡ እናም ራሴን በዚህ መልኩ መቀበል ነበረብኝ፡፡ ድንገት እንደዚህ ያለው ሁኔታ ውስጥ ስትገኙ ራሳችሁን ከአካባቢው ጋር ታላምዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ነገሩ የምርጫ ጉዳይ አልነበረም፤ ምርጫው የተወሰነልኝ በጥቁሮችም በነጮችም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ይቅርና ጀርመን እንኳን የት እንደምትገኝ የሚያውቁ አልነበሩም፡፡ “ምን ጀርመን ነው ያልሽው? ጥቁሮች እዚያ አሉ?” ብለው ይጠይቁኝ ነበር፡፡

ኒውዮርክ የገጠመኝ ለየት ያለ ነገር ነበር፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከላቲን ፣ ከእስራኤል ወይም ከደቡብ አውሮፓ እንደመጣሁ አድርገው ነበር የሚቆጥሩኝ፡፡ ብዙ ግምቶችም ይሰነዝሩ ነበር፣ ኢትዮጵያዊና ጀርመናዊት ብሎ የሚያስበኝ ግን አንድም አልነበረም፡፡ ለነገሩ ይህን ማን ሊገምት ይችላል? አንዳንድ ጥቁሮች የጥቁር ክልስ እንደሆንኩ ያውቁ ነበር፡፡ ሁሉ ጥቁሮች ግን እንደዚህ አይረዱኝም ነበር፡፡ ሌሎች ግምት እንኳን ለመሰንዘር ያቅታቸው ነበር፡፡ ስለዚህም የየት አገር ሰው ነሽ? የሚል ጥያቄ ዘወትር ነበር የሚገጥመኝ ፡፡ ምናልባት የንግግሬ ዘዬ ፣ ወይም አኳኋኔ ይሆናል እንደዚህ የሚያስጠይቃቸው፡፡ የጸጉሬ አሠራር፣ አለባበሴ፣ አብሮኝ ያለው ሰው፣ ያለሁበት ከተማ እነዚህ ነገሮች ይሆናሉ፡፡ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ነገሮች ይገምታሉ፡፡ አንዳንዶች “አይ ጥቁር አይደለችም” የሚሉኝ ከዘሬ ውጭ ከሆኑ ወንዶች ጋር ሲያዩኝ ነው፡፡ ከአንድ ነጭ ይሁዲ ጋር ያዩኝ፣ ክልስነቴን የሚያውቁ አንዳንዶች “አሃ፣ እንዲያ ነው የሚወድላት?” ዓይነት ነገር ይሉ ነበር፡፡ ይህን የታዘቡ ጥቁር ወንዶች ክህደት እንደፈጸምኩና ከጠላት ጋር እንደተኛሁ ዓይነት ይቆጥሩኛል፡፡ ግን ይህ ሰው አባቴን ነበር የሚመስለው፡፡ አባቴን ደግሞ አጥብቄ እወደው ነበርና ለእኔ ክህደትነቱ አልታየኝም እንደ አባቴ ዓይነት ሰው ካልሆነ ብዬ ወይም በበታችነት ስሜት ተጠቅቼ አይደለም፡፡ ሰውን ለይቶ ማየት አልታየኝም፡፡ ለምን በራሴ ላይ ገደብ እጥላለሁ?

እውነቱን ለመናገር፣ የበለጠ ነጻነትና ምቾት የሚሰማኝ ከአፍሪካዊ አሜሪካዊ አካባቢ ይልቅ ነጭ ባለበት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ስለፖለቲካዊ ስፍራዎች ስንናገር፡፡ አለልክ ጥቁርነትን የሚያቀነቅኑ ሰዎች፣ ስልጣንን ተጋፋጭ ዓይነት ጥቁሮች በጠብ መልክ ነው የሚያዩኝ፡፡ ጥቁር ሴቶች በተሰበሰቡበት ክፍል ድንገት ዘው ብል ነገሬም አይሉኝም፡፡ ከመካከላቸው እህት ብሎ የሚቀበለኝ የለም፡፡ ቀለሜ ወደንጣት ስለሚያደላ፣ እንደጥሩር ሊቆጥሩኝ አይፈቅዱም፡፡ ንጣት የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ይህ ከቶም አይካድም፡፡ ለምሳሌ በንጣቴ ምክንያት ሥራ ማግኘት ችያለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ይህ ነገር አስሬ እየተነገረኝ የኛ ወገን አይደለሽም መባል አለብኝ ማለት አይደለም፡፡ ያልተበረዘ ዘር በራሱ ልዩ ጥቅም በመሆኑ የራሳቸውን ልዩ መብት ያለመረዳት ዓይነት ነው፡፡ ይህን ነገር ልታገስ አልችልም፡፡ እናንተስ ማናችሁና የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ሴቶች ይህን ነገር የበለጠ እርስ በእርስ ቢወያዩበት ደስ ይለኝ ነበር፤ የነጣ መልክ ያላቸው ሴቶች በግልጽ ሲናገሩ ግን ለመናደድ መብት እንደሌለን ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ጥቁሮቹም ስለራስሽ ራስሽ እወቂ ካሉና ነጮችም ይህንኑ ሲደግሙ ታዲያ ለማን አቤት እንበል? ይህም ያም መለየትና መነጠል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያማል፡፡ በሌላ በኩል ሰው እንደምርጫው የመወገን መብት እንዳለው አምናለሁ፡፡ ይህ በራሱ ልዩ መብትና ነጻነት ነው፡፡ የርስ በእርሳችንን ተሞክሮ መቀበል እንጂ የሌላን ሰው መብት መጣስ የለብንም፡፡ አንዱ ሰው ጋናዊ ተብዬ መጠራት እመርጣለሁ ካለ ይህ ምርጫው ነው፡፡ አፍሪካዊ መባል ይሻለኛል ካለም መብቱ ነው፡፡ ይህ ማለት የዚያ ሰው እንጂ የእኔ ፈንታ አይደለም፡፡ እኔ አንተን አይደለሁም፡፡ ላንተ ትርጉም የሚሰጥህ ይህ ከሆነ ይህ የአንተ እውነት ነው፤ በአንተ ጉዳይ ፍርድ መሰንዘር የእኔ ድርሻ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ግን ስለመወገን ስንናገር ቁጥሮችን ማየት አለብን፡፡ እኔ ክልስ በመሆኔ ወደ ሌላው ወይም ወደ ክልሶቹ መሄድ እችላለሁ፡፡ ይሁንና መወሰን ሲኖርብኝ መምረጥ ግድ ይሆናል፡፡ ምርጫውም የሚወሰነው ሰዎች እኛን በሚያዩበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ነገር ይለወጣል ብዬ አላስብም፡፡ ይሁንና የኋላ ኋላ እንደሰዎች አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ላይ በመቆም ከጥቁር ከነጭና ከሌላ ቀለም ባሻገር መመልከትና በቤተሰቦቻችን በጓደኞቻችን፣ በግንኙነቶቻችን መካከል በጥቁር ማህበረሰብ መካከል ስለፍርሃቶቻችን ያልተሸፋፈነ ውይይት ማድረግ እንችላለን ብዬ ተስፋ አድጋለሁ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ግን ሁለቱም ወገኖች ፈውስ እንደሚያስፈልጋቸው አምናለሁ፡፡ ዋናው ጉዳይ ፍርሃትን ማሸነፍ መቻል ነው፡፡ ዘርን ወይም የትኛውም ዓይነት የማህበረሰብ በሽታ በተመለከጸ አንኳሩ ጉዳይ ይህ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ የፍቅር ተቃራኒ ፍርሃት ነው፤ በዚህ ማህረሰብ የጎደለውም ዋናው ነገር ይህ ነው፡፡

Share this post

One thought on “ኢትዮጵያዊነትና ጀርመናዊነት

  1. ግሩም አባባል ነው።
    “ዋናው ጉዳይ ፍርሃትን ማሸነፍ መቻል ነው፡፡ ዘርን ወይም የትኛውም ዓይነት የማህበረሰብ በሽታ በተመለከተ አንኳሩ ጉዳይ ይህ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ የፍቅር ተቃራኒ ፍርሃት ነው፤ በዚህ ማህረሰብ የጎደለውም ዋናው ነገር ይህ ነው፡፡”

    ጸጋዬ ገብረመድኅንን ደግመን እንስማው?

    ፍቅርን ፈራን መቀራረብ ፈራን
    እንዳልተዛመድን እንዳልተዋለድን
    ፈርተን መዋደድን ጉርብትናን ናድን
    እኛነትን ትተን እኔነትን ለመድን
    “ፈራን”
    ፍቅርን ፈራን ጥላቻን ሰራን ብቸኝነት ጠራን
    በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር ሰራን

Comments are closed.