ዮዲት እምሩ- የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አምባሳደር

ዮዲት እምሩ- የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አምባሳደር

ከማዕረጉ በዛብህ

ልሳነ ህዝብ መጽሔት ቅፅ 1 ቁጥር 3 ጥቅምት 1996

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማቲክ ታሪክ የተጀመረው በአጼ ምኒልክ ዘመን ቢሆንም የተጻፈ አይመስለኝም።የሀገራችንን ልዩ ልዩ ተቋማትና እንቅስቃሴዎች ታሪክ በመጻፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንከርስት ብዕር ይህንን መስክም ዳስሶት እንደሆነ አላውቅም ። እስከአሁን ካልተዳሰሰ ግን ሊፈተሽ የሚገባ አንድ የጥናት መስክ ይመስለኛል።

የዚህ የሙያ ዘርፍ ታሪክ ቢጻፍ የልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ቤተሰብ ሚና ጎላ ብሎ የሚታይ ይመስላል። ራስ እምሩ ራሳቸው በድኅረ ኢጣሊያ ፋሽስት ወረራ በተቋቋመው የኃይለሥላሴ መንግስት ፣ መጀመሪያ በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሹመው ነበር። ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው አጉረምርመውና አዝነው ስለነበር ሹመቱ በሥራ ላይ ሳይውል ቀረ ይባላል። ቀጥሎ በዩናይትድ ስቴትስ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሹመው በዋሽንግተን አገልግለዋል። ሦስተኛው የአምባሳደር ሹመታቸው በህንድ ነበር።እዚያም አገልግለዋል። ልጅ ያባቱን ተግባር ይከተላል እንዲሉ ፣ ከስምንት ልጆች ብቸኛው ወንድ የሆኑት ልጃቸው ልጅ ሚካኤል እምሩ በጄኔቫ (ስዊትዘርላንድ) በተባበሩት መንግስታት ቢሮ የኢትዮጵያ ዋና መልዕክተኛ (Head of Mission) በመሆን ሰርተዋል።

የዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የራስ እምሩም ሆኑ የልጅ ሚካኤል አምባሳደር መሆን አይደለም። በእርግጥ አባትየውም ሆኑ ልጅየው ከውጭ ቋንቋ ዕውቀት እና ባህል ጋር በመለማመዳቸውና በተለይ ልጅ ሚካኤል አንድ የታወቀ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ በመሆናቸው በግዜው ከነበሩት ባለስልጣናት ለአምባሳደርነት ሥራ መመጠናቸው አያከራከርም። ጉዳዩን ያነሳሁበት ሌላ ምክንያት አለኝ።ስለትሁትዋ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ፣ ሴት አምባሳደር ፣ ስለ አምባሳደር ዮዲት እምሩ የህይወትና የስራ ልምድ አጭር ጽሁፍ ለማቅረብ ነው። የቀድሞዋ አምባሳደር ዮዲት እምሩ ከናይጄሪያ ኤምባሲ ፊት ለፊት በሚገኘው ከአባታቸው ርስት በሠሩት ቤት የሚኖሩ ሲሆን “ዓለምን የረሱ ዓለምም የረሣቸው” ይመስላሉ። የልዑል ራስ እምሩ ልጆችና የልጅ ልጆች በሚኖሩበት በዚያ የቤተሰብ ምኩራብ፣ አምባሳደርዋ ከወንድማቸው ከልጅ ሚካኤል እምሩ ቤት መቶ ሜትር በማይሞላ ርቀት በተሠራ በተንጣለለ ግቢ ውስጥ ይኖራሉ።

ይህ ጸሐፊ ድምፃቸው ስለማይሰማው ስለመጀመሪያዋ የሴት አምባሳደር ለመጻፍ አሰበና ስልክ ደውሎ አገኛቸው።”ስለ እርስዎ ለመጻፍ እንፈልጋለንና ቀጠሮ ቢሰጡኝ መጥቼ ላነጋግርዎሮት” አላቸው።እጅግ በሚያስደንቅ ትህትና “ስለኔ ምን የሚጻፍ አለ?”ብለው ተከራከሩት።የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያዊት ሴት አምባሳደር መሆንዎ ራሱ ታሪካዊ ምክንያት አለው ስለ እርስዎ ለመጻፍ ሲል ጸሐፊው ደጋግሞ በመጠየቅ ስላስቸገራቸው ብቻ ጥያቄውን ተቀበሉት። ቤተሰቡ የትሁት ኢትዮጵያዊ ባህል ቅሪት መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አይፈጅም።አምባሳደርዋ ጋዜጠኛው እና ፎቶግራፍ አንሺውን ታደሰ ተስፋዬን ውጭ ድረስ መጥተው እንደተቀበሏቸው ሲጨርሱም በዛው መልኩ ነበር የሸኟቸው።

ዮዲት እምሩ ሐረር ይወለዱ እንጂ ትምህርታቸውን “ሀ” ብለው የጀመሩት ኢየሩሳሌም ውስጥ ሳን ጆዜፍ በተባለ የካቶሊክ ሚስዮን ትምህርት ቤት ነበር። ልዑል ራስ እምሩ የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ገዢ በነበሩበት ጊዜ ሕፃን ዮዲት ስመጥሩው ዕውቅ ደራሲ አቶ ሐዲስ አለማየሁ ያስተምሩአቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ከኢየሩሳሌም በኋላ ዮዲት እምሩና አንዷ እህታቸው ካይሮ በሚገኝ የአሜሪካን ኮሌጅ ለሁለት ዓመት ያህል ተምረዋል። አባቶቻቸው በአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ወደ ዋሽንግተን ሲሄዱ ትምህርታቸውን በዚያ እንደቀጠሉና አስተማሪም ተቀጥሮላቸው እቤት ያስተምሯቸው እንደ ነበር ይናገራሉ። ከዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሁለተኛ ፀሐፊነት ደረጃ ተቀጠሩ። የተመደቡበት የሥራ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚመለከት (Multilateral diplomacy) ስለነበር በዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ላይ እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል። ለብዙ ዓመታት በዚያ ክፍል ከሰሩ በኋላ አንድ ቀን ተጠርተው አንደኛ ፀሐፊና አማካሪ የሚሉትን ማዕረጎች ዘለው የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴት አምባሳደር ሆነው ተሾሙ።ወቅቱ የጃንሆይ መንግስት የመሸበት፣ ባጠቃላይ የነገስታት አገዛዝም በኢትዮጵያ የሚያከትምበት ጊዜ ዋዜማ ነበር። አምባሳደር ዮዲት ተቀማጭነታቸው በስዊዲን ሆኖ የመላው የስካንዲኔቪያ አገሮች ( ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድንና ኖርዌይ) አምባሳደር ነበሩ።

በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ብዙ ዓመታት ያገለገሉት ዲፕሎማት የሁለትዮሽ አገሮች ዲፕሎማሲ ሥራ እምብዛም አይጥማቸውም። “አምባሳደር መሆን ሹመቱ የተከበረ ነው ።ሥራ ግን የለውም ። ዋነኛው ሥራ በኮክቴሉ መገኘቱ ነው።” ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላም፣ ለተወሰነ ጊዜ በዚያው ሹመትና አገር ሲሰሩ ቆይተዋል። በኋላ ተጠሩና ወደ አገራቸው ተመለሱ። በሥራ ላይ ብዙም ሳይቆዩ ጡረታ ገቡ ።ከሙያ ብቃት ይልቅ የፖለቲካዊ ታማኝነት ለሹመት ማብቃት የጀመረው በደርግ ጊዜ እንደነበር አንጋፋዋ ዲፕሎማት በማዘን ያስታውሳሉ።

የኢትዮጵያን የዲፕሎማቲክ ታሪክ መለስ ብለው ሲቃኙ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የሀገራችን የዲፕሎማሲ ሙያ እያደገ እንደመጣ አንጋፋዋ አምባሳደር ይናገራሉ። የአፍሪካና የአረቡ ዓለም ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ያደንቁ እንደነበር የሚናገሩት አምባሳደር ዮዲት “የኛ ዲፕሎማቶች ትልቁ ጥንካሬቸው ብዙ አለመለፍላቸው ነው። ሲያስፈልግ ብቻ ነው የሚናገሩት።የሌሎቹ አፍሪካና የአረብ ዲፕሎማቶች ብዙ መናገር ይወዳሉ። በዚያው ልክ ብዙ ስህተት ሲሰሩ ማየት ቀላል ነው። የኛዎቹ ግን ዝግ ብለው አስበው ነው የሚናገሩት።ዝምታ ራሱ አንዳንድ ጊዜ አለማወቅችንንም ስለሚሸፍንልን እንደ ሌሎቹ አንጋለጥም።”የሚለውን ሃሳብ አንጋፋዋ አምባሳደር ያሰምሩበታል።

ወደ ዲፕሎማሲ እንዴት እንደገቡ ሲያስረዱ እንደ ጠንካራ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ያስተዳደጋቸውን አስተዋጽኦ ነው። በራስ እምሩ ቤተሰብ ሕፃናት ያድጉ የነበሩት በፍፁም ነፃነትና እኩልነት ነበር።በምግብ ጊዜም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ሁሉ ልጆች ከወላጆቻቸው እኩል ይናገራሉ።ይከራከራሉም።ሌላው ምክንያት ደግሞ ለውጭ ትምህርትና ባህል ከሕፃንነታቸው ጀምሮ መጋለጣቸው ነው።ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የልጆቻቸውን ባሕርይ የቀረፀው የልዑል ራስ እምሩ የሕይወት ፍልስፍና እንደሆነ አምባሳደር ዮዲት በኩራት ያስታውሳሉ።

ራስ እምሩ የፋሺስት ኢጣልያን ወረራ ተከትሎ ብዙ ችግሮች ደርሶባቸዋል። በኢጣልያን አገር በሶስት የተለያዩ ቦታዎች ታስረዋል። ክፉውንም ደጉንም በማየታቸውና “ጌትነቱንም ድህነቱንም” የቀመሱና የተገነዘቡ በመሆናቸው የሀብት ጉዳይ አያስጨንቃቸውም ነበር።ራሳቸው ብዙ መሬት ባይኖራቸውም የእናታችንን መሬት ከእርሳቸው ጋር ለዘመቱና ወላጆቻቸው ለሞቱባቸው ልጆች ይሰጡ ነበር።ታዲያ እናታችን “እርስዎኮ እያነሱ ለሰው የሚሰጡት መሬት የልጆቼን ርስት ነው። ለምን እንዲህ ያደርጋሉ?” ሲሉዋቸው ራስ እምሩም “ልጆቻችን ተምረው በራሳቸው ሥራ ነው መኩራትና መኖር ያለባቸው እንጂ በእኛ ርስት አይደለም” ይሉ ነበር ይላሉ አምባሳደርዋ።

አንጋፋዋ ዲፕሎማት በአሁኑ ጊዜ ምን እየሠሩ ነው? መልሳቸው አጭር ነበር። “አነባለሁ። ዘመድ እጠይቃለሁ።”መጽሐፍ ሊጽፉ ይሞክሩና ትንሽ ከሄዱ በኋላ ከራሳቸው ጋር ይሟገታሉ።”አንዳንድ ላስታውሳቸው የማልፈልጋቸው ነገሮች ሲመጡብኝ መጻፍን እተወዋለሁ። ከተጻፈ ሙሉ በሙሉ እውነቱ መፃፍ አለበት።ግማሽ እውነት መፃፍ የለበትም”።ይላሉ በሚያስገርም ትህትና።

ባገር ውስጥና ከውጭ የሚያደንቋቸውን መሪዎች ሲገልፁ፣ ለአፄ ቴዎድሮስ ከፍተኛ አክብሮት እንዳላቸው ይናገራሉ። “አፄ ቴዎድሮስ ኃያሉን የእንግሊዝ መንግስት “እምቢየው አሻፈረኝ” በማለት የተቋቋሙ ንጉሠ ነገስት ነበሩ። ታገሉ፣ አልሆን ሲል ራሳቸውን ገደሉ። እጃቸውን ባለመስጠታቸው ድሉ የርሳቸውና ያገሪትዋ ሆነ። ጀግና ናቸው። ላገራቸው ትልቅ ፍቅርና ክብር የነበራቸው ይመስለኛል።” ይላሉ አምባሳደር ዮዲት።

ከአፍሪካ መሪዎች መካከል ደግሞ ክዋሜ ንክሩማህንና ሴኩቱሬን በጣም ያደንቁል። “እነኚህ መሪዎች ለአፍሪካ ትልቅ ራዕይ የነበራቸው ሰዎች ናቸው። የታገሉት ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ጥቅም፣ ዕድገትና ፍፁም ነፃነት ነበር። ሌሎቹ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ መሪዎች ግን ጥቁር ፈረንሳዮች ስለሚሆኑብኝ እነሱን መገንዘብና ማድነቅ ይቸግረኛል።” ይላሉ ዮዲት እምሩ።

Share this post

Post Comment