ከአራት ወራት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል በአንድ ላይ ተጣምረው ኢራንን መደብደብ ሲጀምሩ፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር ቤንያሚን ኔታንያሁ ምኞቴ ሠመረልኝ በሚል አይነት ፈንጥዘው ነበር።ዛሬ ግን ያ ሁሉ ተቀይሮ፤ እስራኤል ብቻዋን እንደቀረች እየተሰማት ነው ይለናል በቅርቡ ፖለቲኮ ላይ ታትሞ የወጣው ፅሑፋ። የአሜሪካው ምክትል ፕሬዘዳንት ጄዲ ቫንስ ባለፈው ሳምንት ባደረጒት ንግግር እስራኤል ብዙ ወዳጅ የላትም፤ እና አንድ የቀረች ባለውለታዋን ማስቀየም የለባትም ብለዋል።
ለመሆኑ በአሜሪካ እና በእስራኤል መካከል የተፈጠረው ጊዜያዊ መቃቃር ነው ወይስ ግንኙነታቸው ወደ ቀድሞ ላይመለስ ሻክሯል? በባይደን ዘመን የዋይት ኃውስ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት ጄክ ሱሌቫን፤ የተፈጠረው ነገር ተራ ጥል አይደለም ይላሉ። “መታወስ ያለበት ነገር እስራኤል፤ በርካታ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች፤ ኢራን ላይ ጦርነት እንዲከፍቱ ግፊት ስታደርግ ነበር።የኦባማን እጅን በመጠምዘዝ አገራቸው ኢራንን እንድትወጋ ለማሳመን ሞክረዋል፤ ባይደንንም እንደዛው፤ ትራምፕንም በመጀመሪያው የስልጣን ዘመኑ፤ እንደዚያው ሞክረው ነበር በሁለተኛው ላይ ግን ተሳካላቸው።ግን ጦርነቱ ከተጀመረ በኃላ አሜሪካ እና እስራኤል ሊያስፈፅሙ ያሰቡት አላማ የተለያየ ሆነ፤ እስራኤሎች የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት በአለም ኢኮኖሚ ላይ ያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ እምብዛም የሚያሳስባቸው አልሆነም።ትራምፕ ግን የግድ የአሜሪካ ኢኮኖሚ እንዳይዋዥቅ ሲሉ ጦርነቱን ማስቆም ነበረባቸው።” ይላሉ።
አንድ እስራኤላዊ የፖለቲካ አማካሪ እንደተናገረው፣ እስራኤል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ፣ ይዘውት የመጡት «ቅድሚያ ለአሜሪካ» የሚለው የውጭ ፖሊሲያቸው እስራኤልን የማይጨምር መስሏቸው ነበር።እስራኤል በሁሉም መስክ ከአሜሪካ ጋር የተያያዘች ነች በሚል እሳቤ። አሁን ግን ያ እሳቤ ሕልም እንደነበር እስራኤሎች እየተከሰተላቸው ነው። “ይህ ሁኔታ በፍጹም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ አልነበረም።አሜሪካ ከምታራምደው የውጭ ፖሊሲዋ በተለየ መልኩ እኛን ትንከባከበናለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ነበር።” ብለዋል አማካሪው። በሁለቱ ወገኖች መካከል ንፋስ እንደገባ በግልጽ ይታያል።በ2025 የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወደ ዋሽንግተን አምስት ጊዜ ተመላልሰዋል።በዚህ ዓመት በየካቲት አንድ ጊዜ መጥተዋል፣ ነገር ግን ከዚህ በሗላ ለዋይት ሀውስ ጉብኝት ሌላ የተያዘላቸው ቀጠሮ የለም፤ እንዲሁም የስልክ ልዉዉጦችም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል በማለት አንድ ዉስጥ አዋቂ ለፖለቲኮ ተናግረዋል።
ስለ ጒዳዩ የተጠየቊት የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ግን ምንም የተቀየረ ነገር የለም በማለት ለመከራከር ይሞካራሉ።
“የፕሬዚዳንቱና የምክትል ፕሬዚዳንቱ አቋም አንድ አይነት ነው፤ እስራኤል ሁልጊዜም የዩናይትድ ስቴትስ ታላቅ አጋር ነች፣ እንዲሁም ከፕሬዚዳንት ትራምፕ በላይ የእስራኤል ታማኝ ወዳጅና የሰላም ተሟጋች የሆነ ሌላ ማንም የለም” ሲሉ የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ ተናግረዋል። “የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች በ38 አጭር ቀናት ውስጥም የኢራንን አገዛዝ ወታደራዊ አቅሞች በእጅጉ ባዳከመው በ‘ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ’ ወቅት እጅግ የላቀ አጋሮቻችን ነበሩ።”
ለመሆኑ ጄዲ ቫንስ እስራኤል ወዳጅ ሀገሯን ማስቀየም የለባትም ያሉበትስ ምክንያት ምንድነው? አሜሪካ ከኢራን ጋር ድርድር ማድረጏ ሲሰማ፤ በርካታ የእስራኤል ባለሥልጣናት እና የመገናኛ ብዙሃናት፤ ያመናት አሜሪካ ከዳችን ሲሉ አማረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን የሚደግፍው ቀኝ ዘመም የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ Channel 14, ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ላይ የትችት መአት እያወረዱ ነው። ይኖን ማጋል፣ የተባለው የእኩለ ሌሊት ቶክሾው አዘጋጅ፣ ቫንስን በዕብራይስጥ “ልክስክስ” ወይም “የወረደ ሰው” ብሎ ሰድቦታል፣ እንዲሁም ስቲቭ ዊትኮፍንና ጃሬድ ኩሽነርን “የእስራኤል ወንድሞቻቸውን እየሸጡ ያሉ” በማለት ከሷቸዋል። የኔታንያሁ ዕጣ ፈንታ በኦክቶበር ምርጫ የሚወሰን ሲሆን ከዋይት ሀውስ አገኛለሁ ብለው አስበውት የነበረው ድጋፍ አየር ላይ ተንኖ የጠፋ ይመስላል።