“ማርገዜን ከነገርኩት ቀን ጀምሮ ደብዛዉ ጠፋ።እውነት ለመናገር አንድ የእንግሊዝ ወታደር እንዲህ ያደርጋል ብዬ አላሰብኩም ነበር» ትላለች ካሮሊን ዋምቡይ ሙሩኪ፣ የ33 ዓመቷ ኬንያዊት።በኬንያ ናንዩኪ ከተማ ከእንግሊዝ ሀገር ከመጣ ወታደር ጋር ተዋውቃ ግኑኙነታቸው እስከ አንሶላ መጋፈፍ እንደደረሰ ትገልጻለች።
ከናይሮቢ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝው ናንዩኪ የብሪታንያ ጦር የማሰልጠኛ ክፍል ኬንያ (British Army Training Unit Kenya — BATUK) መቀመጫ ናት።በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የእንግሊዝ ወታደሮች እየመጡ ይሰለጥኑበታል።
ቋሚ ሥራ የሌላት ካሮሊን ልጇ ሰባት አመት እንደሆነው እና ለማሳደግ እየተቸገረች እንደሆነ ትናገራለች።”ልጄ ስለ አባቱ ማንነት ደጋግሞ ይጠይቀኛል።የትምህርት ክፍያውን መክፈል ስላልቻልኩ የተወሰነ ጊዜ ከትምህርት ቤት ማስወጣት ነበረብኝ» ትላለች።«አንድ የምፈልገው ነገር ቢኖር ይህ ሰው ልጁን በማሳደግ እንዲረዳኝ ነው፤ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እፈልጋለሁ» ትላለች።
የኬንያ ፓርላማ በህዳር 2025 ባቀረበው ሪፖርት፣ የእንግሊዝ ወታደሮች በአካባቢው ከሜኖሩ ኬንያውያን ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት እንደሚፈፅሙ እና በርከት ያሉ ልጆች እንደተወለዱ ገልጿል።ወታደሮቹ በተለይ ከሳምቡሩ እና ከማሳይ ማህበረሰቦች የመጡ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈጸሙ ማስረጃ ማግኘቱን ሪፖርቱ ገልፆል።እነዚህ ወታደሮች ወደ እንግሊዝ ከተመለሱ በኋላ፣ብቻቸውን የቀሩ እናቶች ማህበራዊ መገለልና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ሪፖርቱ ያብራራል።
የእንግሊዝ ወታደሮች በናንዮኪ የሚሠለጥኑት በብሪታንያ እና በኬንያ መንግስታት መካከል በ1964 በተደረገ ውል መሠረት ነው።ይሄ የጦር ማሠልጠኛ በናይሮቢ እና በለንደን መካከል ዲፕሎማስያዊ ውጥረትን እያሰፈነ ነው።የእንግሊዝ ወታደሮች ጾታዊ ትንኮሳ በመፈፀም፣ እና በአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች እየተከሰሱ ነው።የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴር በጥቅምት 2025 ባወጣው መግለጫ፣ ከኬንያውያን እናቶች እና ከብሪታንያ ወታደራዊ አባላት የተወለዱ ልጆች መኖራቸውን እንደሚያውቅ ገልፁፆል።”አባታቸውን ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ካሉ ለመተባበር ዝግጁ ነን” ብሏል።
በ2024 መጨረሻ ላይ ከኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የተውጣጡ ባለሙያዎች ቡድን የፎረንሲክ ጄኔቲክስ ምርመራ በማድረግ፤ በናንዩኪ በብሪታንያ ጦር ሰራዊት ውስጥ ያገለገሉ ከነበሩ ሰዎች የዲኤንኤ ናሙና እና የግል ታሪኮችን ሰበሰቡ።ቡድኑ የፎረንሲክ ጄኔቲክስ ባለሙያ የሆኑትን ፕሮፌሰር ዴኒዝ ሲንደርኮምብ-ኮርትን እና የቤተሰብ ጉዳይ ጠበቃ ጀምስ ኔቶ ያካትታል። አባቶቻቸውን በማግኘት ልጆቹ ቀለብ እንዲያገኙ እና ዜግነት እንዲሰጣቸው ለማድረግ። በዚህም ወደ ሃያ አራት የሚሆኑ አባቶች ተለይተው ጉዳዬ ወደ ፍርድ ቤት ተልኳል።