በቅኔ ትገዛቸዋለህ ጸጋዬ እና ግራ የኢትዮጵያ ታሪክ ግምገማሐተታ፣

በቅኔ ትገዛቸዋለህ  ጸጋዬ እና ግራ የኢትዮጵያ ታሪክ  ግምገማሐተታ፣

(የመጨረሻው ክፍል)

በክፍል አንድ፣ ስለ “ጁጁ ተረት”፦ መረጃ በሌለው ትርክት ራስን መደለል፣ “ጋላ”ን በ “ጋ*” ከመተካት እሳቤ ጋር ይቀራረባል ብለን ነበር። “[ጁጁ] አረመኔያዊነትን የሚያንጸባርቅ ፍጹም ባዕድ የሆነና ኢትዮጵያዊነትንና ክርስትናን የማይወክል በደም መስዋእት በሚያምኑ ኋላ ቀር የሆኑ ሰዎች እምነት ላይ የተመሠረተ ትረካ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ባህል ይወክላል ተብሎ ሊመረጥ እንዴት ቻለ? … ይህች አገር እኮ የንግሥተ ሳባ አገር ነች!” (ገጽ 201-202)። የሚገርመው፣ ይኸ ዓይነት አስተሳሰብ ዘመናዊ ትምህርት ተስፋፍቶም እንኳ፣ በጋራ ሸንተረሩ ተከልሎ የኖረ ሕዝብ፣ በቲቪ በሞባይል ባውራ ጎዳና ባውሮፕላን ከውጭው ዓለም ጋር ተገናኝቶም ሥፍራ አለመልቀቁ ነው።

በጸገመ አእምሮ፣ ታሪክ እንደ ጎርፍ ነው፦ እያዳቀለ እያፋፋ እያዳፋ እያራገፈ የሚጓዝ ነው፦ “የሰው የአራዊት የአእዋፍ፣ ውስብስብ ነገረ ጉንዳን | ሲነሳ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያዚባ ሚዛን| በማይመጠን ታላቅ ኃይል፣ በተፈጥሮ ግዙፍ ሥልጣን | ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል | ልደቱ እድሜና ሞቱ፣ አለማቋረጥ ይጓዚል…።” በሌላ አነጋገር፣ ለብቻው የሚጓዝ የለም። የጸገመ አባት የኦርቶዶክሱን ከኦሮሞው ጋር አዳቅለው መጓዝ አልከበዳቸውም። ለኦርቶዶክሱም፣ ከተገኘው ባህል ነጥቆ መጓዝ የኖረ ልማድ ነው። ሰው በተባለ ዘንድ፣ ባህል፣ ቋንቋ በተባለ ዘንድ አንዱ ባንዱ ላይ ማየል፣ መዳቀል የተለመደ ነው። አምልኮ፣ ባእድ ይሁን ቤተኛ፣ ዘር የለውም። የጸገመ የልጅ ልጅ “ምኒልክ” መባሉ አይደንቅም (ገጽ 251)። ለጸገመ፣ እንደ “ኤ አይ” ውልድ፣ ምኒልክን ከታሪክ ፍቆ ማውጣት ክህደት ይሆንበታል።

የጥንት የኃይማኖት መዛግብት ሊቅ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በሌላ ሥፍራ፣ “ኢትዮጵያዊነት አማራ ኦርቶዶክስ ነው” ብለውን ነበር። እንደ እርሳቸው አባባል፣ ሌላው ሁሉ በእንግድነት መጥቶ ቤተኛ መሆን የከጀለው ነው። አገላለጻቸው በአግላይነቱ ብዘዎችን ቢያስቆጣም፣ ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ማለት አይደለም። አማራ እና ኦርቶዶክስ በሌሉበት ኢትዮጵያ የምንላትን በዚህ ዝናዋ በዙህ ቁመናዋ ልናውቃት አንችልምና። ሦስት እውነቶች ግን ከዙህ ጋር አንድነት መታየት ይኖርባቸዋል፦ ያልፈለሰ ያልተደባለቀ፣
ከተገኘበት የበቀለ “ንጹሕ” ሕዝብ አንድም በምድር ላይ የለም። ኦርቶዶክስ ክርስትናን ከአይሁድ ቢዛንቲን ግሪክ መሠረቱ ነቅሎ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ በርኖስ ማልበስ ቀላል አይሆንም። ከ “አማራ ኦርቶዶክስ” ውጭ ያለ ወገናችንም በሌለበት ኢትዮጵያ የምናውቃትን ኢትዮጵያ አትሆንም!

ጠ/ሚ ዐቢይ ለፖለቲካቸው ሲሉ በማይረግብ አንደበታቸው፣ ከእነ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ከካውንስል ወንጌላዉያን እና ካዲሳባ ነቢያት ጋር፣ አንዴ “(አክሱማዊት) ጽዮናዊት ኢትዮጵያ” ወይም እንደ ናታንያሁ እስራኤሏ “ቃለ የተገባላት ቅድስት አገር”፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “የአፍሪካ ቊንጮነትን” የታሪክ ቅርሷና ኅልውናዋ አድርገው ስለውናል። ይኸ በመረጃ ያልተገራ አስተሳሰብ፣ ስለ ራሳችን እና ስለ እርስበርስ እውነቱን እንዳንነጋገር የዕውርነት ኮርቻውን ጭኖብን እንዲጋልበን ፈቅደንለታል። ኃይለሥላሴንማ ከኤጄርሳ ጎሮ አንሥቶ “ሰሎሞናዊ” ዙፋን ላይ አስቀምጧቸዋል። የተለማመድናቸው ትርክቶች በእውነት ብርሃን እንዳይገለጡ መስጋት፣ መከላከል፣ ጭለማና ድንቊርናን መምረጥ ይሆንብናል። እውነትንም ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል ብሏል።

ብዘሓኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ የትርክት ቀመር ውስጥ አለመደመሩ አሁን ለምንገኝበት ነውጥ ዋነኛ ምክንያት ነው። የክርስቶስ ወንጌል በሰዎች ልብ፣ ማኅበርና ሥልጣኔ ላይ በጎና ስር ነቀል ለውጥ ማምጣቱ የታሪክ ሐቅ ነው። ያንኑ ወንጌል በእግዙአብሔር አምሳል የተፈጠረን ሰው ለማጎሳቆል ሲጠቀም ግን እስከ ዚሬ የዘለቀ (ድንፋታችንን) እውነታን የካደ አስተሳሰባችንን ያጎላዋል። ክርስትናን በመቀበል ከአፍሪካ ከአውሮጳ አገራት ሁሉ ቀድመናል የምንል፣ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገና በህገ አራዊት እንደሚመሩት መምሰላችን፣ ማተብ እና ምንሽር አንድነት የምንይዝ፣ ሥጋ ወደሙን በወሰድንበት አንደበት እርስ በርስ ለምንራገም፣ የኔ ዘር ካንተ ዘር ይበልጣል ለምንባባል ውርደትና ጒስቊልና እንጂ አንዳች ክብር እንዳላተረፈልን እያየን ነው።

ጸገመ ከአማራ እናቱ እና ከኦሮሞ አባቱ፣ በአምቦ ቦዳ ቦረን አንኮበር ባህላዊ ልማድ አድጎ፣ በባእድ የተፈጥሮ አምልኮ ኅብር ተሳፍሮ፣ ከግብጽ እስከ ሴኔጋል እስከ መስጴጦምያ እስከ ህንድ አሜሪካ አውሮጳ መዝለቁ፣ የሰውን ልጅ ትሥሥር በማጉላቱ፣ ለጸገመ በአፍሪካ ፌስቲቫል መሳተፍ እና ከባለቅኔዎች ፈላስፎች አፍሪካዉያን ከእነ ሴንጎር ጋር ለመወዳጀቱ ምክንያት ሆኗል። ለቦዳ እሬቻ ከወሎ ግሸን ማርያም ኩሽ ግብጽ እና ዎሎፍ ፉላኒ ጋር ተመሳሳይነት ማግኘት፣ ለጸገመ የጥበብ ሕይወት ዋነኛ በር
ከፋች ሆኖ እንመለከታለን። ከላይ እንዳመለከትኩት፣ ባእድ አምልኮ ዘር የለውም። የጸገመ አካሄድ አግባብነት የለውም በተባለበት ሰዓት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባህል አክብሮ በማስተባበሩ፣ ለአገሩ ኲራትን አትርፏል። የአፍሪካን አህጉራዊ ልሳን የቀረጸው ጸገመ እንደ ሆነ አንርሳ!

የጸገመ ሁለት ቀዳሚ ሥራዎች የታተሙት በእንግሊዝኛ ነው (“ኦዳ ኦክ ኦረክል” በፈረንጆች 1965 እና “ኮሊዥን ኦፍ ዖልታርስ” በፈረንጆች 1977)። የኋለኛው መጽሐፉ፣ ጸገመ በዋነኛነት በአገርኛ ቋንቋ ለመጻፍ ፊቱን ያዞረበት ወሳኝ ዓመት ነው። ከላይ የጠቀስኩት ደቡብ አፍሪካዊው ፕሮፌሰር ካቨና፣ በቅኝ ገዥዎች ልሳን ላለመጻፍ ወስነው ከነበሩት፣ ብዘዎች መሃላቸውን ሲያፈርሱ፣ ጸገመ ብቻ በቃሉ እንደ ረጋ አስፍሯል። የሚገርመው፣ እውቁ የኬንያ ደራሲ እና ጸሐፌ ተውኔት ንጉጊ ዋቲዮንጎ (በፈረንጆች ከ
1938 እስከ 2025 የኖረ) ለአንድ ዓመት በኬንያ መንግሥት ታስሮ ከተፈታ በኋላ፣ ዳግም በቅኝ ገዥ ቋንቋ በእንግሊዝኛ ላይጽፍ የባህሉን እና የአእምሮውን ነፃነት ያወጀው በ1977 ነበር። በጸገመ ውሳኔ ላይ የ ንጉጊ (ወይም በ ንጉጊ ላይ የ ጸገመን) ተጽእኖ ለጊዜው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

ጸገመ እና አብዮታዊ ምሑራን

ጸገመ በየትኛውም መሥፈርት ምሑር መምህር ተራኪ እና ፈላስፋ ነው። በግለ ሰቦች ላይ፣ በአማርኛችን ላይ እና በትውልዶች ላይ ተጽእኖው ለዙህ ጒልህ ማስረጃ ነው፦ በቅኔ እና በመድረክ ሥራዎች ከተሠማሩት አያልነህ ሙላትን፣ ፍቅሬ ቶሎሳን፣ ከበደች ተክለአብን፣ አዳም ረታን፣ በእውቀቱ ስዩምን፣ ነቢይ መኮንንን፣ አበባው መላኩን፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆን፣ አበበ ባልቻን፣ ወዘተ፣ መጥቀስ ይቻላል።

በ1966 ዓም የተቀጣጠለው ሶሻሊስት አብዮት በ17 ዓመት ውስጥ የአገራችንን ፊውዳል ገጽታ (ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ መልክዐ ምድር፣ ኃይማኖት እና እርስ በርስ ግንኙነቶችን) ሙሉ በሙሉ ለበጎ ባይሆንም፣ ጨርሶ ቀያይሮታል። ለዙህ በዋነኛነት የምሑራን ድርሻ አለበት። ጸገመን ከእነዙህ ምሑራን ጋር ማስተያየት ይኖርብናል። ጸገመ እና የኢትዮጵያ ግራ-ዘመም “አብዮታዊ” ምሑራን የሚለዩት በሦስት መንገድ ነው፦ አንደኛ፣ ስለ ሕዝብ እና ስለ ኃይማኖታዊ ባህል ባላቸው መረዳት። ለምሳሌ፣ አብዮታውያኑ ከአውሮጳ ወርሰው፦ ኃይማኖት ከዘመናዊነት/ከሳይንስ፣ ከዘመናዊ ትምህርት፣ ከፖለቲካ መነጠል አለበት ይላሉ። በርዕዮተ ዓለማዊ ክትባት፣ በእስራትና በባሩድ ሕዝቡን ከኃይማኖት ነፃ ማውጣትን ተቀዳሚ ያደርጋሉ። ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሲቻኮሉ፣ አስተማማኝ ምትክ ሳያገኙለት፣ ማኅበረሰብ ለዘመናት የተያያዘበትን የሞራል መሠረት ንደው ባለመተማመን (በመደብ ጦርነት) ላይ አውዳሚ ግንኙነቶችን ለማነጽ ሞከሩ። እግዚአብሔርን ያለመፍራት ፋሽን በ “አብዮታዊ ኃይማኖት” ተቀይሮ ብሔራዊ ኪሳራ አድርሶ አየን። ጸገመ በአንፃሩ፣ በቅኔዎቹ እና በመድረክ ሥራዎቹ፦ ሕዝቡ በሚረዳው ቋንቋ እና ምስል ራሱን እንዲያይበት ከሕይወቱ ንጥረ ህዋስ የተሠራ መስተዋት እፊቱ ማቅረብ ይሻላል ሲለን ኖሯል። ሥልጣን የሚፈልቀው ከጠመንጃ አፈሙዝ ነው ሲሉት (ዛሬ ድረስ)፤ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ሲሉት (ያው ወዳጅ ተመልሶ ነገ ጠላት ሊሆን!)፦ እኔንስ “ጥበብ ይናፍቀኛል፥ ተቻችሎ የሚኖር ሕዝብ ያስቀናኛል፥ ድንቍርና ያስፈራኛል፥ ጦርነት ያስጠላኛል” ይላቸዋል!

ሦስተኛ፣ ግራ-ዘመሞቹን አብዮተኛ ምሑራን “አንድ ብቸኛ መንገድ” እንጂ እንደ ጸገመ አስታራቂ መንገድ አያውቃቸውም። በእነርሱ ዐይን፣ ቅራኔዎች የሚፈትቱት በፍልምያ ብቻ ነው፤ አንደኛው አንጃ የበላይነቱን ሲይዝ ነው። ወይ ሶሻሊስት ማርክሲስት ወይም ሽብር ነው። የህወሓት አመራር ወይም የማያቋርጥ ጦርነት ነው። ብልጽግና ካሠመረው “መደመር” ውጭ እኲል ተቀምጦ መመካከር አይፈቀድም። ባጭሩ፣ ያለእኔ ለኢትዮጵያ የሚያውቅላት የለም ነው! ርዕዮተ ዓለማዊነት እንጂ አንዳቸውንም ሰብዓዊ ሕዝባዊነት አያውቃቸውም! ሁላቸውም ግራ-ዘመም መሆናቸው የሚጠቊመን የሥልጣን ጥመኝነታቸውን፣ ለሕዝብ ርኅራኄ-ቢስነታቸውን ነው! ከኃይሌ ፊዳ ከብርሃነመስቀል ረዳ አንድ ምረጥ ይሉናል! ፊዳንና ረዳን መወዳጀት፣ አንድነት መያዝስ አይቻልም?

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ (እና በጣም ጥቂቶች ሌሎች)፦ ይቻላል ሲሉ የሰማቸው አላገኙም (ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ–የሕይወት ጉዞ እና ትዝታዬ፣2007 ዓም ይመልከቱ)። ያኔ ጥያቄ ያነሱ፣ ያለምስክር “አብዮታዊ እርምጃ” ተወስዶባቸዋል፤ በዚህም ፊዳንም ረዳንም አጣን እንጂ አንዳቸውን እንኳ ማትረፍ አልቻልንም። ለረጅሙ ጒዞ የሚያዘልቀን ሽብሩ የጠቆሙን ዓይነት ወዳጅነት ነው።የድንክ መሪዎች ሥራ፣ ከኪሳራ ወደ ባሰ ኪሳራ ነው። ዛሬም ከሸኔ ከብልጽግና፣ ከፋኖ ከብልጽግና፣ ከፋኖ ከሸኔ እያልን ነው።ከታሪክ የማንማር ሆነን እንጂ መልሱ አንድ ነው፦ ከሁለቱም ወገን በጋራ የሚበጀንን መርጠን እስካልያዝን፣ ሁለቱንም ማጣት ይሆንብናል!

ምሑራኑ ለሕዝብ ያላቸውን የአክብሮት ዓይነት በአመለካከታቸው አስመስክረዋል። አብዮታዉያኑ “ዴሞክራቶች” ባመዛኙ ሕዝቡን በቃል ባይሆን በተግባር፣ አንተ አታውቅም እኛ እናውቅልሃለን የሚሉ ዓይነቶች ናቸው። እንደ ተገኙበት ዘመን፣ በሶሻሊስት አብዮት ወይም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም በመደመር ብልጽግና ሥልጣናቸውን አበጃጅተዋል። ጸገመ በአንጻሩ፣ ሕዝቡ ከዘመናት እምነቱ ልምዱ እና አብሮነቱ መማማር ይችላል ባይ ነው። እርግጥ ነው፣ በዚህ አመለካከቱ ጸገመ ብቸኛ አይደለም፤ መንግሥቱ ለማ፤ ሰሎሞን ዴሬሳ፤ መስፍን ወ/ማርያም፣ ገ/ክርስቶስ ደስታ፣ ወዘተ፣ በሕዝቡ ኃይማኖት እና ባህል ላይ ሥር ነቀል ለውጥ የማምጣቱን ፋይዳ የተቀበሉ አይመስሉም።

ጸገመ እና ምሑራኑ ደግሞ የሚጋሩት አላቸው፦ አምልኮ እግዚአብሔር እና ባህላዊ አምልኮ የተዛመዱ እንጂ የጎላ ልዩነት እንደሌላቸው ያስባሉ። ከሕዝቡ ጋር የኃይማኖቱ ሥርዓት ተካፋይ ሲሆኑ ግን አልታዩም። እንደ አውሮጳዉያኑ አቻዎቻቸው፣ ንቃተ ኅሊናው ከፍ ሲል ሕዝቡ ኃይማኖቱን ወደ ጎን ያደርገዋል ብለው ያምናሉ! በዓለም ዘሪያ ያሉትን ጨምሮ፣ እየጨመረ የመጣው ኃይማኖታዊ እይታ የሚያስረዳን ግን ተቃራኒውን ነው፦ ንቃተ ኅሊናቸው የወረደው የሕዝቡ ሳይሆን የምሑራኑ ሆኖ እናገኛለን! ፋሲል፣ የጸገመ ኃይማኖት ምን እንደ ሆነ ጠይቆት ምን መልስ ሰጥቶት ይሆን?

ከላይ እንደ ጠቀስኩት፣ ጸገመ በእናቱ አማራ ኦርቶዶክስ ነው፤ አድባራትና ጬሌን አንድነት ያስተያያቸዋል። በአባቱ ሜጫ ኦሮሞ ሆኖ፣ ገዳ ሥርዓት፣ ኢሬቻ፣ ዋቄፈና እና አቴቴ አምልኮን ይገነዘባል (ገጽ 59፤207- )። እነዙህ ሲወራረሱ የመጡ ማኅበራዊ እሴቶችና፣ ኗሪው የለት ተለት ኑሮውን ለማሸነፊያ የተገለገለባቸው፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን የሚያጠናክሩ የባህል ኃይላት እንደ ሆኑ ይረዳል። ጊዜ ያለፈበትን የቤተ መንግሥተኛ አባ ሀብተማርያምን አድርባይነት ይቃኛል። አባቱን አቶ ገብረ መድኅንን ተከትሎ የአድርባዮችን ያልተገባ ሥልጣንና ግብዝነት ያወግዛል (ገጽ 219)።

አብዮታዊ ምሑራኑ (ሁላቸውም ግራ ዘመም) ማኅበረ ሰባዊ ህመሞችን የመረመሩበት መሣሪያ እና መነሻ አሳባቸው መለያየቱ፣ ለተመሳሳይ በሽታ መጠኑ የተለያየ መድኃኒት እንዲያዝዙ አስገድዷቸዋል። ውጤቱ፣ የማይፈውስ ጠባሳው ያልሻረ የሚመረቅዝ ማኅበራዊ ነውጥ ሆኖ እንመለከታለን። ይህም የአገሬውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ያልተያያዘ፣ የሕዝብን ስሜት የተጫነ፣ ከባህር ማዶ የተለቀመ መድኃኒት በመሆኑ ነው። ከመቶ ዓመት በላይ የተገለገልንበት የከፍተኛ (ዘመናዊ) ትምህርት ፖሊሲ ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል፦ ከ1900 ዓም እስከ 1927 ዓም ከፈረንሳይ የተቀዳ ነው። እስከ 1933 ዓም ድረስ ከጣልያን። እስከ 1943 ዓም ከእንግሊዝ። እስከ 1965/66 ዓም ከአሜሪካ። እስከ 1983 ዓም ከሶሻሊስት አገሮች። አንደኛው የጀማሪ አብዮተኛ አንጃ ከታንዚንያ አፍሪካ ሲል፣ ቀጥሎ፣ ያንኑ በአገር በቀሉ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲተካው፤ ከዙያ የሶቭየቶችን፤ የቻይናዎችን የምሥራቅ ጀርመኖችን
የቪዬትናሞችን የአልቤኒያዎችን። እነ መለስ ዜናዊ በ 1983 ዓም ተራ ሲደርሳቸው፣ ባልተጠና፣ በቂ በጀትና የሠለጠነ የሰው ኃይል በሌለበት (በተለይ በአናሳ ወገኖች አካባቢ)፣ በጎሳ ፖለቲካቸው ታውረው፣ ሁሉን በየቋንቋው ሲበታትኑት አየን (በቂ ዝግጅት አለመደረጉን እንጂ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መደረጉ ተገቢ አይደለም ለማለት አይደለም)። ባጭሩ፣ የፖሊሲ ቀረፃው ባእድነት እና አለመያያዝ፣ የሕዝቡ ድህነት እና ፊደል አለመቊጠር ተደማምሮ በኪሳራ ላይ ኪሳራ አስከትሎ እንመለከታለን። በዚህ ላይ ቤተ ክህነት በዘመናዊ ትምህርት ላይ ያስነሳችውን ተቃውሞ ስንጨምር፣ ያለፍንበት እና የምንገኝበት ዝብርቅርቅ ምክንያቱ ጒልህ ይሆንልናል። በሌላ አነጋገር፣ አብዮታውያኑ በገዛ አገራቸው እንጠቅመዋለን ባሉት ሕዝብ ላይ ከባእዳን (ከጣልያን ፋሺስቶች፣ ወዘተ) ባልተናነሰ ጉዳት አድርሰው እንመለከታለን።

የጸገመ ሥራዎች ፍትኅ እና ሰብዓዊነትን ማማከላቸውና ከሕዝቡ አብራክ መገኘታቸው ሁለት ቊምነገር ያስጨብጠናል። ከሕዝብ አብራክ መገኘታቸው፣ ጸገመ የእንግሊዛዊውን የሼክስፒርን ማክቤዝ (1961 ዓም) እና ኦቴሎ (1956 ዓም) ወደ አማርኛ መልሶአቸው የተመለከቱ፦ “ሼክስፒር አማርኛ ሲናገር ዋለ” እንዳላሉ ሁሉ (ተገላቢጦሽ ዛሬ፣ አማርኛውን በእንግሊዝኛ የሚያስቡና የሚጽፉ ተበራክተው እያየን ነው)። ሁለተኛው፣ ምናልባት ዋነኛው ቊምነገር፦ አዝጋሚ ባህላዊ የለውጥ ባቡር፣ ፈጥኖ ብዙ ተሳፋሪ ባጭሩ ካራገፈ ከሥር ነቀሉ በተሻለ ፍጥነት እና ርቀት ወደ ታቀደው ያደርሳል የሚል ነው!

የጸገመ አእምሮ ያደገበትን አካባቢ መልክዓ ምድር እና ውስብስብ ልማድ፣ ቋንቋ እና አምልኮ ከጮጮ ወተት ጋር ተ-ግቶ እንዳደገ አያጠያይቅም። በዙህ አኳኋኑ ከየትኛውም የአገራችን ማኅበረ ሰብ ጋር ብዘ ልዩነት የለውም። ቅይጥነትን ሁሉም ይጋራዋል። የምንጋራቸውን መሠረታዊ እውነቶች መዘንጋታችን ብዘ አክሥሮናል፤ እያከሠረንም ነው።

በታሪካችን ተረጋግቶ መኖርን የሚያናጉ ፀቦች ዝርፊዎች ድርቆች ድህነቶች ህገ ወጥነቶች መፈናቀሎች ድንቊርናዎች አንዱ ባንዱ ላይ መሠልጠኖች ጠፍተው አያውቁም። ጸገመን የሚለየው፣ የልጅነት አእምሮው ለእውቀት ካለው ጥማት የተነሳ ከእድሜው በላይ እንዲጥር እና እንዲያስብ፣ ደቃቅ አሳቦችን፣ ተፈጥሮ አፈራርቃ ከደገሰቻቸው ጋር እያስተያየ ማውጠንጠንን፣ ማስታመምን፣ ምሥጢሯን እንድታጋራው እየተማፀነ ማደጉ ነው (ገጽ 4፣ 5፣ 240)። “ቢራቢሮ ከአበባው ላይ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ፣ ከቄጤማው ከለምለሙ፥ ሰምረሽ አቅፈሽ መመሠሉ … | አዴ አዳዬ እመ-ምኔቴ፣ የትውልድ መስታየቴ፣ የዘመን ቅርሴ መክሊቴ፣ የዕድሜ አንቀልባ ሞግዚቴ …”

ጸገመ የልጅነት አድማሱ እየሠፋ በሄደ መጠን፣ ሕይወት ውስብስብ ብቻ ሳትሆን፣ የሚጋራቸውን ሰብዓዊነቶች ከዘራፊ መታደግ ሕይወት እና ንብረት እንደሚያስከፍል ወደ መረዳት ደርሶ ነበር። አውዳሚ ኃይላትን ለመቃወም፣ ልዩነቶችን ማጥበብ እና ማስታረቅን ቀዳሚ ተልእኮው አድርጎት እንመለከታለን። በኦሮሞ አማራ ሳይወሰን፣ ጥቊር ኲሻዊ አፍሪቃዊነትን ከሥርዓተ እምነቱ እና ከቋንቋ ድምፀቱ ጋር አስተሳስሮ የማንነቱ መታወቂያ፣ የቅድመ ሥልጣኔ ቅድመ ፍጥረት መሠረት አድርጎት እንመለከታለን።

ኖርዌጅያኑ ራይዱልፍ ሞልቬር፣ የ “ብላክ ላየንስ” መጽሐፍ ደራሲ እና የኢትዮጵያ ተኮር ጥናቶች ተመራማሪ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እና ሌሎች፣ ከጸገመ ቅኔ ድርደራ እና ተውኔት “ሙያው” ወጣ ያሉ “ታሪክ ነክ” ምርምሮቹ ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ተደምጠዋል። እርግጥ ነው፣ የጸገመ የእውቀት ግብይት ስልቱ ግር ይላል። “ወል ቤት፣ ዋል፣ ወል፣ ውል፣ ወል-ኦ፣ ወል-አጋ፣ ወል-ቂጤ፣ ወል-ኢሶ፣ ወል-ወል፣ ወል-አይታ፣ ወል-መራ፣ ወል-ኢንጪቲ፣ ወል-ድያ፦ እነዚህ ኅብር አንድነት አመልካች ናቸው” ይለናል (ሲዲ)። የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስበርስ፣ አልፎ ከግብፅ ከጥቊር ሕዝቦች ጋር ያስተሳስራል። በዙህም ኢትዮጵያን የሰው ልጅ መገኛ፣ የሥልጣኔ መነሻ ያደርጋታል። ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት ምንጭ፣ “እጅግ ጥንታዊ የግብፅ ኲሽ ሐይሮግሊፊክ ቃል” ናቸው ይለናል። የጸገመን ድምዳሜ ሙሉ ለሙሉ መቀበል ቢያዳግተኝም፣ የሚገርመው፣ ጸገመ ይህን አሳብ ሲያንሸራሽር የኖረው ድንቅነሽ (ሉሲ)
በ1966 ዓም ከአፋር ምድረበዳ ራቊቷን ብቅ ከማለቷ አስቀድሞ መሆኑ ነው!

ጸገመ እነዙህን እውነቶች ያለሳይንስ እርዳታ እንዴት አወቃቸው? ይኸ በጸገመ ብቻ ሳይወሰን፣ ከሱሜር እስከ ግሪክ እስከ አዜቴክ እስከ 16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ሳይንሳዊ አብዮት ድረስ የዘለቀ ጥያቄ ነው። ጥንታውያን የተገነዘቡት፣ ዘመናዉያን ግን በተለይ አውሮጳዉያኑ፣ ሳይንስ ያልመረቀው እውቀት ከብልሹ ኃይማኖተኛ መላ ምት አይሻልም፤ እንግዲህ የጨቅላነት ዘመን አበቃ፤ ምራቅ ለዋጠ ላደገ ለሰው ልጅ የኃይማኖት ጡጦ አያሻውም፤ ማኅበረሰብ ወደ ሥልጣኔ ብርሃን እንዳይገሠግሥ ካገተው ሳይላቀቅ እውቀቱ የተሟላ አይሆንም ሲሉን ኖረዋል። ከበጎ ምኞታቸው በተቃራኒ፣ “አደገ፣ ምራቅ ዋጠ” የተባለው ሰው እንደ አራዊት ከአንድ እልቂት ወደ ሌላ ወደ ጥፋቱ ሲመላለስ ታይቷል።

ዛሬ በተቃራኒው የኃይማኖት ጉዳይ ተበራክቶ ምድርን አጣብቧት እንመለከታለን! በዚህም፣ ሰው፣ አማልክት ቢቀሩ፣ ራሱን እና የራሱን ጥላ እንደሚያመልክ፣ ሳይንስን እንደሚያመልክ፣ ከአምልኮ መላቀቅ እንደማይሆንለት አስመስክሯል። ጸገመ ይህን ምሥጢር ቀድሞ እንደ ተገነዘበው ያስታውቃል። ጠቢቡ ጸገመ፣ በስፌት እህል እንደምታበጥር ባለሙያ ሴት፣ ባህሎችን ከያሉበት አዳቅሎ፣ መድረክ ላይ አንጋግቶ እፍ ይልባቸዋል፤ ሕያዋን ይሆናሉ!

ሳይንስ ዛሬ፣ የሰውን አእምሮ፣ የሕይወት ምሥጢራትን በሙላት መገንዘብ እንደማይችል አስረድቷል። በሌላ አነጋገር፣ በትዝብት ወይም በምክንያታዊነት ላይ ብቻ ሳይደገፍ ለእውቀት ፍንጭ ማግኘት ተችሏል። በፈረንጆች የ1981 ኖቤል ተሸላሚው የስነ አእምሮ ስነ ልቡና ሊቅ ሮጀር ስፐሪ (እና ከ ስፐሪ ኋላ የመጡትን ጨምሮ) እንዳመለከተን፣ የሰው አንጎል፣ ግራ/ቀኝ ክፍል ተነጣጥሎ ሳይሆን አንድነት ነው። ግራው ክፍል ባመዛኙ ወደ ምክንያታዊ ሳይንሱ ወደ ቋንቋ፣ ቀኙ ወደ ኪነ ጥበቡ ወደ ምናባዊነት እንደሚያዘነብሉ አረጋግጧል። ከቀኙ የአንጎል ክፍል ወደ ግራው መሸጋገር እንደሚቻል ታውቋል።

በኪነ ጥበባት የተሠማሩ ሁሉ እንደሚያውቁት፣ የፈጠራ ሥራዎችን አካሄድ እና የመገለጦችን ዘይቤ በውል ማወቅ ከቶውን አለመቻሉን ነው። የልቡና ብልጭታዎች ሁሌ እርግጠኝነትን አይላበሱም፤በልምድ ልውውጦች አይዳብሩም ማለት ግን አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ የጸገመን ግኝቶች እና “መላ ምቶች” ከማጣጣላችን በፊት ትርጉም ሰጭነታቸውን፣ የተሠወሩ፣ ግን ቅርባችን ያሉ እውነታዎችን ለማገናዘብ እንደሚያስችሉ መቀበል ይኖርብናል።

ጸገመ እውን “ምሥጢረኛ ባለቅኔ” ነው?
ጸገመ ጽሑፉ በቀላሉ አይገባም ብለናል፤ ወይም ሲባል ሰምተናል። ሚካኤል ሺፈራው “ምሥጢረኛው ባለቅኔ” ሲለው፣ ጠ-ጠር ማለቱን ለማሳወቅ እና ሥራዎቹን ማጣጣም ጥረት እንደሚጠይቁ፣ የተደራረቡ አሳቦች እንደ ተካተቱባቸው ለመግለጽ ይመስለኛል። እርግጥ ነው፣ የጸገመ “ኤክስፔሪሜንታል” ቴአትር መድረክ፣ እንደ ተለምዶው መግቢያ-ሐተታ-መደምደሚያ ትርክቶች ራስና ጭራውን መለየት ቀላል አይሆንም፤ መድረኩ “ሕዝባዊ” ነውና በአውራ መንገድ ላይ እና በታዳሚው መሓል ሳይቀር ሊከሠት ይችላል። ትርክት የለውም ማለት ግን አይደለም። የዚህኛው ዘይቤ ዒላማ ተመልካቹን ማሳተፉ፣ ማወያየቱ፣ መጠየቁ እና በራሱ ወደ ድምዳሜ እንዲደርስ ማደፋፈሩ ላይ ነው። ይህን ማሳካት ሙዚቃን (ነርሲስ ናልባንዲያን) ምስሎችን (ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ታደሰ መስፍን) እና ጭፈራ/ዳንስን ያካትታል። ብሔራዊ ቴአትር ፊት ለፊት ቅድም ያየነው ስም የለሹ ጩሎ፣ ከየሰው እግር ሥር የሚንደፋደፈው ሊስትሮ፤ እውስጥ ሲ-ገ-ባ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር መድረክ ላይ ታዳሚውን ቊልቊል እያየ ያናግረዋል። ነገር ተገልብጦ፣ እኛም ሳንወድ ልናደምጠው እንገደዳለን!

ሚካኤል ለረጅም ዓመታት የጸገመን ቅኔዎች ካብላሉ እና ውበታቸውን አጣጥመው ካደነቁ መሓል አንዱ ነው። ከራሱ እና ከአገራዊ ማንነት ጋር አዛምዶ የጸገመን ቅኔዎች እና ተውኔቶችን ለመረዳት የተለየ ጥረት አድርጓል። ሆኖም፣ ጸገመን እና ሥራዎቹን ለመተንተን ወደ “ሳይኮቴራፒ” “ሲምቦሊዝም” “ሜታፎሪካል” ቋንቋ ሲዛመት (“ቨልጋራይዜሽን ኦፍ ስፒሪት”፣ ወዘተ፣ ገጽ 106) ያልተጠበቁ እክሎች ገጥመውታል፦ ይህም፣ ከሙያዊ ክህሎት አንጻር እና ከአውሮጳው የተዋሳቸው ስልቶች እሳቤዎች
ለተርታው ዜጋ በአግባቡ ያለመተርጎማቸው ጉዳይ ነው።

የ“ደራሲያን እና ፖለቲከኛ ምሑራን” በእንግሊዝኛ እያሰቡ በአማርኛ መጻፍ መናገር፣ አንባቢውን በገዛ አገሩ ባእድ ሲያደርግ ኖሯል። ሕዝቡ “ምሑራኑ” የሚሉትን ሳይረዳ፣ በመጤ ልምዳቸው ተማርኮ ወደ ባሰ አለመግባባት ውስጥ ገብቷል። የዘመኑን ታዋቂ ደራሲያንን የሚያደንቁ ብዘዎች፣ የደራሲውን ቅይጥ አጻጻፍ በቅጡ ሳይረዱ አብሮ ለመታየት ወድደው የሚያደንቁ ናቸው። ሚካኤል ምናልባት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢያስተምር፣ ስነ ጽሑፍ እና ቴአትር የሚያጠኑ (በተለይ የጸገመን ሥራዎች) የበለጠ ይጠቀማሉ። ሦስተኛ፣ ሚካኤል ከጸገመ ሥራዎች ጋር ረጅም ዘመን ከመቆየቱ ይመስላል፣ የጸገመ አሻራ በአጻጻፉ ላይ ይታያል። ከታች የተመለከተውን “የምሥጢረኛው ባለቅኔ”ን መግቢያ (ገጽ 3-6፤ ገጽ 3፣ አንቀጽ 2) ከጸገመ “እሳት ወይ አበባ” መግቢያ (ገጽ 7-14) ጋር እናስተያይ፦

“አንድ ምእመን የሃይማኖቱን ድንጋጌ ከማተቱ ይልቅ በቀጥታ እግዚአብሔርን በእምነት ማገልገሉ እንደሚበልጥበት ሁሉ፤ ባለቅኔም የሥነ-ግጥሞችን የአደራደር ሥርዓትና ድንጋጌ (ፎርም) ከማተቱ ይልቅ ቅኔውን ተቀኝቶ ደርሶ ፍሬ ሃሳቡን (ኮንቴንት) ማበርከቱ ይበልጥበታል ቢያሰኝም፣ የግል አስተያየቱን ፈለግ ከጽሑፉ አነፃፅሮ በቅርብ መመልከቱ ደሞ የብዕሩን ዝንባሌ ፈር ሊያሳይ ይችላል ይባላልና፤ …” (ጸገመ)

“ይሁን እንጂ የአንዲት ውብ አበባን ወይንም የአንዲት ውብ ቆንጆን ውበት አይቶ ይኽንን ዓይነት ውበት በምናይበት ጊዜ የሚፈጠርብንን መልካም ስሜት ሳይሰማው ከውበት ጋር ገጽ ለገጽ ተፋጦ ቆሞ ሳለ የማይንቀሳቀስ ታዳሚ በቱርጁማን ውበትና እውነት ተተንትነውለት ከተኛበት ይቀሰቀሳል ማለት ቢያስቸግርም …” (ሚካኤል)

በ1960ዎቹ፦ አሳምነው ገብረወልድ እና ታደሰ ሙሉነህ፣ ጸገመን፣ አፃፃፍህ ይጠጥራል ትባላለህ አቅልለህ መጻፍ ትችል አልነበር? ብለው፣ ከጻፈው ጽሑፍ ላይ ነቅሰው አንብበውለታል (Timeless Muzika + ክፍል 2)። ጸገመ ግን አቅልሎ አለመጻፉን አልተቀበለውም። ቋንቋ ከማኅበረ ሰቡ ጋር አብሮ የሚያድግ፣ እድገቱን የሚያንፀባርቅ እንጂ በነበረው የሚቀር አይደለም ብሏል። እድገቱን በማሳካት፣ ከሕዝቡ የወሰደውን መልሶ በማቅረብ ድርሻውን እየተወጣ እንደ ሆነ አስረድቷል።

እንደ ብዘዎች እኔም፣ ጸገመ ውስብስብ ነው፣ በቀላሉ አይገባም ስል ኖሬአለሁ። ኋላ ግን የተገነዘብኩት፣ ወደ ጸገመ ግብዣ ለመታደም፣ ትእግስት፣ ንቊ ተሳትፎ እና በራስ ማሰብን መጠየቊን ነው። አንድ ነገር ግልጽ ነው፦ ሌሎች እንዲያስቡለት ራሱን ለሸጠ፣ የቴክኖሎጂ ግርግር ትእግስት ለነሳው ትውልድ፣ የጸገመ ሥራዎች ከምንጊዜውም ይልቅ ባህሉን እና ራሱን አውቆ እንዲከባበር የማድረግ ጥበብ በውስጣቸው አካትተዋል። “ሀ ሁ”ን “እናት ዓለም ጠኑ”ን 2፣ 3፣ 4፣ 5 ጊዜ ተመላልሰው
የተመለከቱ ነበሩ! ለእነዚህ ትርፋቸው፣ ከላይ እንደ ጠቀስኩት፣ በኅብረ ቀለማት በዳንስ በሙዚቃ በነጎድጓዳዊ መብረቃዊ ሐረጎች መጥለቅለቅ ብቻ ሳይሆን፣ በአእምሮአቸው እንዲያስቡ፣ በልማድ የተቀበሉትን በአዲስ መልክ እንዲጠይቁ መደረጋቸው ነው! የቴአትር ቤት ደንበኛ ዞሮ ዞሮ (ባዲሳባም በክፍለ ሃገርም) ከተሜው ነው፤ በዘመናዊነት ላይ የተንጠላጠለ ከተሜ፣ በማንነቱ ያልተደላደለ በጥራዝ ነጠቅነት የተፈናቀለ፦

የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም | የኔ ክንድ ተልም አይተልምም
የኔ ጣት አረም አይነቅልም | በፊደል መፈደል በቀር፥ ጉልጓሎ እኮ አይጐለጉልም
ለስልሻለሁ፥ ሠልጥኛለሁ፥ ሰይጥኛለሁ አልሆንሽም፥
አቴቴ ዱብራ ቦረና | መቸም ሁሉን ቻይ ነሽና
አጥንቴ ከአጥንትሽ ማዕድ፥ ቢመነጭም ተቀምሞ | ከ “ሀ” እና ከ “አሐዱ” በፊት አስቀድሞ
ዚሬ በዓይንሽና በዓይኔ መሀል፥ አጉል ስልጣኔ ቆሞ | ሰየጠንኩና አልሆንሽ አልኩ፥ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ፥ …

ሁለት እውነታዎች የጸገመን ቅኔ ለማጣጣም ረድተውኛል። አንደኛው፣ ቅኔውን (እንደ ጥሩ ኢትዮጵያዊ) ከሥጋ ክፍል ከሳላይሰጥ ጋር ማመሳሰሌ ነው፦ ሳላይሰጥ አያያዘን ላወቀበት ብዘ ይቸራል። እርግጥ ትንሽ ጥረት ትንሽ ትግል ይጠይቃል። ሁለተኛው፣ የጸገመን ቅኔ ይበልጥ ለመረዳት ኦሮምኛ ማወቅ መጥቀሙን ነው። ይህን የተገነዘብኩት ከአማርኛ ወደ እንግሊዜኛ የተተረጎሙ ጥቂት ግጥሞቹን ኢንተርኔት ላይ አንብቤ የተዘለሉ እና ያልተስተካከሉ ሐረጎች እና የአሳብ ክፍተቶችን በመታዘቤ ነው። ቅኔዎቹን
በእንግሊዚኛ እንድተረጉም ካነሳሱኝ ምክንያቶች ቀዳሚው ለእንግሊዚኛ ተናጋሪው ዓለም ማስተዋወቅ ቢሆንም፣ ክፍተቶቹን ለማሟላት ጭምር ነው (የተረጎምኳቸውን ኢትዮፕያ ኦብዘርቨር ዶት ኮም እና በእንግሊዜኛ “Blue Nile Poems” መጽሐፍ ላይ ይመልከቱ)።

የጸገመ የቅኔ ኃይል ምንጩ፣ ፋሲል ይትባረክም በትክክል እንደ ታዘበው፣ “በቃላት ሸማኔነቱ” ነው። ጸገመ በስነ ልቡናው ሆነ በአእምሮው ለኦሮምኛ ለግእዝ እና ለአማርኛ ድንበር የለውም። ጸገመን ለመረዳት የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር፣ ሕዝብ እና ባህል፣ ላይ ላዩን ወይም ለይስሙላ ሳይሆን፣ በጥንቃቄ ከጥቃቅኑ እስከ ግዙፉ አያይዝ መረዳትን ግድ ይላል። ለምሳሌ፣ ጸገመ በሲዲ በድምጽ በተቀዳው ላይ “አዋሽ”ን ከማንበቡ አስቀድሞ የግጥሙን አካሄድ ሲያብራራ ቆይቶ፣ “ሲሞላና ሲቆጣ ግን አዋሽ ልክ እንደ ኢትዮጵያዉያን ሕዝብ ባህርይ ሁሉ አያድርስ ነው” ይለናል (ከ46ኛ ደቂቃ ጀምሮ)። ይኸ ድምዳሜ እንዳመጣ የተነገረ ሳይሆን፣ እቦታው በመገኘት፣ አካባቢውን ከአካባቢው ጋር ከመሠረቱ በማስተያየት፣ አፈ ታሪኮችን ጭምር በማገናዘብ ነው። አዋሽ፣ ድንበር ሳይሻገር በምድረበዳ አሸዋ ውስጥ ተቀብሮ መቅረቱን፣ እንደ አገር ወዳድነት ወይስ እንደ ራስ ወዳድነት እንተርጒመው? “አያድርስ ነው” ያለው የትኛውን ባህሪአችንን ይሆን?

ኢትዮጵያን እንደ አገር እና እንደ ሕዝብ ለመረዳት “እሳት ወይ አበባ”ን በተናጠል እና በቡድን ከዳር ዳር ደጋግሞ ማጥናት ይገባል። ኢትዮጵያ የአሳብ እንጂ የቋንቋ ድኃ አይደለችም! ህወሓት እና የመደመር ብልጽግና፣ እንደ ቀደሟቸው መንግሥታት፣ የጸገመን ሥራዎች ማንሠራራት በዐይነ ቊራኛ የሚመለከቱትና የሚከላከሉት ለምን ይሆን?

ፋሲል፣ እስከ 1966 ዓም ድረስ ያለውን የጸገመን የሕይወት ታሪክ እንዳቀናበረ አስታውቆናል። ቀጭን ትእዛዝ እንደምሰጥ አይምሰልብኝና፦ ከ1966 ዓም በኋላ ለ “ክፍል ሁለት” ሥራዎቹ፤ የዘር ፖለቲካን፣ የስደቱን ዘመን፣ የፖለቲካ ተሳትፎዎቹን/ጽሑፎቹን ባፋጣኝ ማሰባሰብ ይገባል። ደበበ እሸቱ፣ ኃይማኖት ዓለሙ፣ አባተ መኲሪያ፣ ወዘተ፣ ማለፋቸው ብዘ ጠቃሚ መረጃዎችን እያሳጣን እንደ ሆነ መገመት አያዳግተንም። ወጣቱ ትውልድ ቅርሱን ካለማወቅ የተነሳ ብዙ እያጎደለ ነው። ጊዜ ቆሞ አይጠብቅም። የጸገመን የተበታተኑ ሥራዎች ቶሎ በጥንቃቄ (ቢቻል በባለሙያ ጥምረት) ማሰባሰብ እና ለሕዝብ ማድረስ
ይገባል። ቴአትሮቹን ለሕዝብ ማቅረብ። ክፍል 2 “አበባ ወይ እሳት” ን፤ “እሳት ወይ አበባ” ን ማሳተም፣ ወዘተ፣ (እየተደረገ ሊሆን ይችላል)።

ስደተኛው ባለቅኔ
የጸገመን አገር ወዳድነት፦ እርሱ ንውዮርክ፣ ባለቅኔ ወዳጁ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ስዊድን፣ አገር ቤት ገብተው ጒሽ ጠላ ትፍትፍ እያሉ መጠጣት እና ማውራት አምሮታቸውን በስልክ ሲጨዋወቱ መስማት በከፊል ይገልጸው ይሆናል (“ገሞራው”፣ በ 2007 ዓም በ72 ዓመቱ አረፈ። አዲስ አድማስ)። ሁለቱም የሚወዷትን ምድራቸውን በዐይነ ሥጋ ሳያዩ መቅረታቸው፣ እራሳችን በራሳችን ላይ ያመጣነው፣ ዛሬ ድረስ ያልረገበ የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት ነው። ትንሽ ተስፋ የሚሆነን፣ የሁለቱ ሬሳ ለምድራቸው
በመብቃቱ ነው። ምኞታቸው ያልያዘላቸው ሌሎቹ ግዞተኞች ሰሎሞን ዴሬሳ እና ገብረ ክርስቶስ ደስታ ምን ሲሉ እንደ ነበረ መገመት አያዳግትም። ነፃ ብዕራቸው፣ ሥልጣን ላይ ያሉትን ስላሠጋቸው፣ የእውቀት ብልጭታ በማያዘልቅ ሥልጣን ተዳፍኖ እንመለከታለን። ምርጫው ዛሬም ከሁለት አንድ ነው፦ድምፅ አጥፍቶ፣ ገዥውን አወድሶ እድሜና ኑሮ ማራዘም፤ ወይም ለጥሪ ታማኝ ሆኖ ዋጋ መክፈል? የግዞተኞቹ የተስፋ ቅኔ የሚነግረን ነገር አለው፦
አስተምሪኝ ቢራቢሮ፣ ሰው ለመባል አለኝታዬ፣
ቀድሞ የት ነው መነሻዬ፣ ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ?…
ዕድልሽ የዋዛም አደል | ክፉ ፈተና ነው መምሰል…
በርቺ እንግዲህ ቢራቢሮ፣ ክረምት ላንቺ ብቻ አለፈ መስሎ አላድር ያለውማ፣ በጐርፍ ዘቅጦ ጐረፈ… [ጸገመ]

………………………………………………………….

የተሳሰረው ቤተሰብ የጠበቀውም አንድነት | እንዳልነበር ተነጣጥሎ የትየለሌ ቢራራቅም …
በጠበበው ምድርና በተደፋው ሰማይ ማዶ | ዐይነ-ሕሊና አሻግሮ ሐቅን ከሒደት አዋህዶ ተስፋ ብቻ ይሻገራል ጥቊሩን ሕዋ ቀዳዶ [ከበደች ተክለአብ፤ 1980 ዓም፣ ከሶማልያ የስደት እስር ቤት]

……………………………………………………………..

ኢትዮጵያን ሞሽሬ ሳልቀበል | ረገፈ ያቆጠቆጠ ቅጠል
በለዘ ፍራፍሬ ሳይበስል | ዛገ ልሳኔ አፎት አጣ ሾተል ተለይቼ ልቀር | ተለይቼ ልቀር … [ሰሎሞን ዴሬሳ]

…………………………………………………………………..

ባያውቁት ነው እንጂ – የእኔን ቋሚ ንግርት | በተወለድኩበት ነው – የምቀበርበት
ሌላ ቦታ ሳይሆን – በትውልዴ መሬት
አስቀድሞም ቢሆን – ዕትብቴ ተቀብሯል | ቀሪውም አካሌ – በርግጥ በክብር ያርፋል
ሲንከራተት ኖሮ አካሌ – የትም ምድር | በስተመጨረሻ – የሚያርፍበት አፈር ከተወለድኩበት ነው – በክብር የሚቀበር … [ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው)]

…………………………………………………………………………

አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት | ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት።
ለምለም ነው አገሬ፣ | ውበት ነው አገሬ፣ | ገነት ነው አገሬ።
ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ | እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ።
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ | አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ።
አለብኝ ቀጠሮ | ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ። [ገብረክርስቶስ ደስታ]

እነዙህ ባለቅኔዎችና አቻዎቻቸው ባዳበሩት የባህል መሠረት ላይ ከማነጽ ውጭ አማራጭ የለንም፤ እንደ ፖለቲካው ሁሉ፣ ያለፈውን አፍርሶ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” “አብዮታዊ ክልላዊ ዲሞክራሲ” “ጽዮናዊ መደመር” ግርግር መፍጠር ከኪሳራ ወደ ኪሳራ መንከራተት ነው። ከዙህ አኳያ፣ በጸገመ ሥራዎች ላይ የቋንቋ እና የመረጃ ጥራት የጎደላቸውን የድኅረ ምረቃ ጥናቶችን መመልከት እጅጉን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ አግኝቻለሁ!

እንደ ሕዝብ እንደ አገር ሁሉ ነገራችን በእቅድ ሳይሆን በእድል ባጋጣሚ ሆኗል
በሌላ ሥፍራ፣ ከገብረ ክርስቶስ ደስታ ሥራዎች ጋር እንዴት በድንገት እንደ ተዋወቅሁ ገልጬ ነበር (Lissan Magazine 2010)፦ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ፣ የትምህርት ቤታችን ርእሠ መምህር ቢጫ ወረቀት ላይ የተፃፈ ጽሑፍ ሲያድሉ እኔና ጓደኞቼ ድንገት ደረስን፤ መምህሩ ስንንጋጋባቸው፣ ያውላችሁ ብለው ወረቀቱን አየሩ ላይ በተኑት። በግብግቡ ተገፍቼ ከዳር የወጣሁ፣ ቆሜ ካለሁበት ንፋሱ ሽው አድርጎት እቅፌ ላይ አኖረልኝ። ቢጫው በራሪ “መንገድ ስጡኝ ሠፊ” ይላል (ርእሱ፣ “የጠፈር ባይተዋር”ም ተሰኝቶ አይቻለሁ)፦

ግማሽ ቀልድ አላውቅም! | ሞት እንደሁ ልሙት በሴኮንድ መቶኛ
እንቅልፍ እንደ ሬሣ ዘላለም ልተኛ።| መንገድ ስጡኝ ሠፊ …

ሁሉ በእድል፣ በድንገት ነው። የህግ የበላይነት የናቀ ነው። በጉልበትም ነው። አንዳንዴም በስእለት።በደጅ ጥናት። በሎተሪ። በጉቦ። ተቋማትን ቆመ ቀር ያደረገ ነው። ወይም ባዲሳባ ይሳካልሃል ትንቢት ነው። በድግምት። በድፍን ብልጽግና። በሌላ አነጋገር፣ እጅ አጣምሮ የመንግሥት እጅ ማየትን (የፖለቲካ መሪዎች የሚወዱት የሚያበረታቱት፤ መብት መጠየቅ ያሳስራል!)። ጸገመ፦ “ያለፈ ጥረታችንን፣ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ፤ ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ” ይለናል። የአገር እና
የሕዝብ አስተዳደርን ህጋዊ ሰላማዊ ቀጣይነት አሁን ከነገሠው ገዥ ፓርቲ አያያዝ ጋር ስናስተያይ፣ ካለፈው የተለየ ለውጥ የሚኖር አይመስልም። መሪዎቻችንን፣ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም እስከ መለስ ዜናዊ እስከ ዐቢይ አሕመድ አንዳቸውንም ለመሪነት ያሰባቸው የለም። አመጣጣቸውና አገዛዛቸው እንደ ፍፃሜአቸው ድንገት ነው፤ አካሄዳቸው ሕዝብ በታኝ ግብታዊ ነው፤ በጭለማ በምሥጢር ነው።የትምህርት ዘርፍ ዛሬም ከመጣው ጋር እየዋዠቀ ነው።

ትምህርት ቤት ገብቼ ተምሬ ሥራ ይዤ ቤት ሠርቼ ትዳር መሥርቼ ልጅ ወልጄ አስተምሬ ድሬ ተጡሬ ካስፈለገ ውጭ አገር ሄጄ ተመልሼ ከአብሮ አደጎቼ ጋር ሽምግልናዬን አጣጥሜ፣ ስሞት ዘመድ ወጥቶ በምድሬ እቀበራለሁ፤ መካነ መቃብሬን ማንም ባለሃብት ባለሥልጣን አይደፍረውም ማለት ለብዘሓን ከቶውንም የማይጨበጥ ተስፋ፣ የጅል ወሬ መስሏል።

በህመምና በአምልኮ ዓይነት የታጀበ የጸገመ የሕይወት ታሪክና የጥበብ ሥራ በዚህ ረገድ ስለ ራሳችን እና ስለ አገራችን ትልቅ ቊምነገር አዝሏል። እስኪመቻች መጠበቅ፣ ማመኻኘት፣ ተስፋ መቊረጥ እንደማያሻ፤ አስቀድሞ ጥሪን ጠንቅቆ ማወቅ። ለጥሪ መገዛት። አለማመንታት። ደፍሮ መጠየቅ።መስዋእት ለመክፈል መፍቀድ። ደፋር እና ጭስ መውጫ አያጣማ! ይኸ የጸገመ ሕይወት ነው። በፕሮፌሰሮች መስፍን ወልደማርያም እና ባህሩ ዘውዴም ያየነው ነው (የ“ኅብር ሕይወቴ”ን ግምገማሐተታ ኢትዮፕያንቸርችዶት ኦርግ ላይ ይመልከቱ)።

የድንገተኛ ነውጥ ድግግሞሾችን ለመከላከል፣ ልምድ እና እውቀት የሌላቸው፣ ለመምራት ያልበቁ፣ ያልተገባቸው፣ እየተነሡ ያልተብላላ ፖሊሲ መሞከሪያ መሳረርያ እንዳያደርጉን ምን ቅድመ ዝግጅት እናድርግ? ለዚህ ጥያቄ ባስቸኳይ መልስ ማግኘት ይኖርብናል። ይህን ለመመለስ የሚበቊ፣ ከትጥቅ ትግል ይልቅ በልብ ስፋት፣ በአስተሳሰብ ጥልቀት፣ ከአጭር የሥልጣን ሱስ እና ሥሥት ተላቅቀው የረጅሙን ውጤት የሚያስቀድሙ ቅን ምሑራን በምድራችን ይፈጠሩ ይሆን?

የጸገመ የቅኔና የተውኔት እምቅ ኃይል እንዳይባክን መጣር ያለብን ጊዜ ላይ ደርሰናል! ሚካኤል ሺፈራው በትክክል እንዳስቀመጠው፦ “(የጸገመ) ሥራዎቹ ወደ መድረክ ደግመው ቢቀርቡና ቢታዩ ዘመን የሚያልፍባቸው አይደሉም … እኛም ሆንን ተከታዩ ትውልድ ላይ ላዩን እያየን ከመደናቆር ይልቅ ጠልቆ ለማስተዋል ከምንገደድበት ምዕራፍ ላይ ነን” (ገጽ 337)። አሜን ወአሜን እንበል።

ምጥቀት”፣ በሁለተኛው ኅትመት የተሻለ አርትዖት ሊደረግለት ይገባል። ግድፈቶች በከፊል እነሆ፦
 ገጽ 13፣ 22፤ የአውሮጳ አቆጣጠር መስከረም/ጥቅምት 2011 በኢትዮጵያው ይተካ።
 ምዕራፍ አንድ እና ሁለት ውስጥ የሠፈረው የምኒልክ ዘመን (በግምትም ቢሆን) ይጠቀስ። “ምጥቀት” የጸገመ ታሪክ
ይሁን እንጂ ባንድ ገጽታው የአገራችን (ሕዝብ) ታሪክ ጭምር ነው!
 ገጽ 45፣ አንቀጽ 3፣ መስመር 5፦ ደሞ = ደግሞ (ደሞም ደግሞም፤ በሁሉም መልኩ ወጥ ይሁን ነው)
 ገጽ 47፤ አንቀጽ 2፣ መስመር 2፦ ስላሳሰባችው = ስላሳሰባቸው
 ገጽ 88፣ አንቀጽ 4፣ መስመር 4፦ አጃቢዎቸቸው = አጃቢዎቻቸው
 ገጽ 89፣ አንቀጽ 1፣ መስመር 8፦ በሹክሹታ = በሹክሹክታ
 ገጽ 159፤ አንቀጽ 1፣ መስመር 1፦ ጸገመ ከለንደን የተመለሰበት ዓመት ይጠቀስ።
 ገጽ 170፣ አንቀጽ 2፣ መስመር 3፦ “ወደ ገጠር ቤትህ ተመልሰህ አርሰህ ብላ” (“የከርሞ ሰው” በ1959 ዓም ቀኃሥ ቴአትር ከመታየቱ በፊት (ገጽ 316 ሠንጠረዥ) በብሔራዊ ቤተ መንግሥት አዳራሽ ታይቶ ነበር። የ “መሬት ላራሹ” መፈክር ጅማሬ ይኸ ይሆን?
 ገጽ 179፤ አንቀጽ 2፦ ከበደ ሚካኤል እና ባላምበራስ ማኅተመ ሥላሴ የቀኃሥ ሽልማት የተቀበሉት ዓም?
 187 ኦዳ ኦክን ወደ አማርኛ የመለሰው ማነው?
 ገጽ 191፣ አንቀጽ 3፦ ኦዳ ኦክ ኦረክል መቸ እና የት አፍሪካ እና አውሮጳ አገር ታይቷል?
 ገጽ 192፣ ከፎቶው ግርጌ፦ ዶክተር ፊሊፕ ካፕላን እና ፍራንሲስ ካፕላ ወይስ ካፕላን?
 ገጽ 198፣ ጸገመ ከሴንጎር ጋር ፎቶ ዓመተ ምሕረቱ መቸ ነው?
 አብረን ዝም እንበል ገጽ 198 መስመር 2፣ አፍታ እፍታ ተብሏል፤ ገጽ 200፣ መስመር 5 አፍታ። በ1999ኙ ኅትመት
ላይ ብዘ ግድፈት አለበት። የመጀመሪያውን ኅትመት 1986 ተብሏል (1966 ነው)፣ ወዘተ
 ገጽ 247፤ ስለ ዳያሊሥሥ በረጅም አንቀጽ መ዗ገብ ለምን አስፈለገ?
 ገጽ 257፤ የእሳት ወይ አበባ መጀመሪያ እትም የታተመው በ1966 እንጂ በ1965 ዓም አይደለም (ከመጽሐፉ የውስጥ
ሽፋን ይታያል)። ገጽ 175፣ አንቀጽ 3፣ መስመር 7 [1965 የተባለበት ምክንያቱ፣ ሁለተኛው እትም በፈረንጆች 1973 መባሉ፣ እና ከ 1973 ላይ 8 ስለ ተቀነሰ ነው። “First printed in 1973 by Berhanena Selam Printing Press, Addis Ababa, Ethiopia”
 ገጽ 317፤ ቆሼ ሲጋራ = ኮሾ ሲጋራ?
 የጸገመ የመጀመሪያ ቅጅ ሥራዎች በጥንቃቄ ከያሉበት በባለሙያዎች ተሰባስበው ሊያዙ ይገባል።

Share this post

5 thoughts on “በቅኔ ትገዛቸዋለህ ጸጋዬ እና ግራ የኢትዮጵያ ታሪክ ግምገማሐተታ፣

  1. ፀጋየ ገብረመድህን ሥልጣን ላይ ከነበረው መንግስት ጋር ሳይነካካ፤ በአቋሙ እና ባመነበት ፀንቶ እንደኖረ አድርጐ ማቅረብ ደጋፊዎቹን ሊያስደስት ይችላል። እውነታው ግን ሌላ ነው። ፀጋየ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከደርግ ሰዎች ጋር ቅርርብ ነበረው። ደርግን በማሣመን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲቋቋም አደረገ። የራሱ የቅርብ ሰዎች የነበሩት እና በኃላ ላይ የእርሱን ትያትር በማዘጋጀት በስፋት የተሳተፉት አባተ መኩሪያ፣ ሃይማኖት አለሙ፣ ጌታቸው አብዲ እና ሳህሉ አሰፋ ቁልፍ ቦታ እንዲይዙ አድርጐአቸዋል።በአብዮቱ ዘመን ያዘጋጃቸው ትያትሮች ሀሁ በስድስት ወር፤እናት ዓለም ጠኑ፤መልእክተ ወዛደር፤አቡጊዳ ቀዊሶ ከደርግ ዲስኩር ጋር እጅጉን የሚዛመዱ ነበሩ። እዚህ ላይ አንድ ነገር መጥቀስ ያስፈልጋል። በደርግ የመጀመሪያዎቹ አመታት ተስፋየ ገሠሠ የሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ወቅት ተይዘው ታሰሩ። የተሰጠው ሞክንያት ቴአትር ቤቱን ለማሣደስ አላስፈላጊ ወጪ አድርገዋል በሚል ነው። ተስፋየን ከሥራ ኀላፊነታቸው እንዲነሡ እና እንዲታሠሩ ፀጋየ ገብረመድህን ሚና እንደነበራቸው በወቅቱ የሚታወቅ ነገር ነበር። ይህ በስፋት የሚታወቅ ቢሆንም ከፀጋየ ቲፎዞ ብዛት አንፃር የሚነገር አልነበረም።ስለ ጉዳዩ ደፍራ የፃፈቸው አንዲት እንግሊዛዊት ነች። እንዲህ ትላለች፦ “It is hard to imagine that Tsegaye did not have some role to play in the sacking. He was certainly able to extend his patronage to ensure that his protégées, Sahalu Assefa and Getachew Abdi, were brought in to replace Tesfaye at the Hager Fikir Theatre.”A History of East African Theatre, Professor Jane Plastow. የአዲስ አበባን ማዘጋጃ የቲያትርና ባህል አዳራሽ እንዲያስተዳድሩ ኀላፊነት የተሰጣቸው አባተ መኩሪያ አብዮታዊ የተባለውን መልእክተ ወዛደር አዘጋዡ።ትያትሩ ለደርግ የተበረከተ ገፀበረከት ነበር።አባተ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ ቲያትር ቤቱን ሲመራ የሚሣየው የፀጋየን ትያትር ብቻ ነበር። በ70ዎቹ ፀጋየ እና አጋፋሪዋቹ ብዙዎቹ ትያትር ቤቶችን ተቆጣጥረዋው ነበር። “Many of my informants in the late 1980s agreed that a small cabal, led by Tsegaye Gebre-Medhin, had massive control of the theatres and their output. Even when new young directors were employed by the theatres they might get minimial opportunity to practice their craft” ትላለች ጄን ፕላስቶው። ፀጋየ በደርግ ዘመን ሁሉ፥ አንድ ሳምንት ከመታሠሩ ውጭ እና ጋሞ የተባለው ትያትሩ ከመታገዱ ውጭ የደረሰበት ነገር የለም።ወጣቶች ኢሃፓ ተብለው ሲጨፈጨፉ እርሱ የሚፈራ፣ የሚከበር ባለሥልጣን ነበር።

  2. በነገራችን ላይ ጸጋዬ ከኢሃዲግ ጋርም ለመሞዳሞድ ሞክሮ ነበር። ኢሃዲግ ሲገባ ለወጣት አዘጋጆች ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ትያትር ማሣየት ያለባችሁ አሁን ነው ይላቸው ነበር። ከዚያም በደርግ ውድቀት ዋዜማ ላይ የፃፈውን የመጨረሻ ቴአትሩ ”ሀሁ ወይም ፐፑ” ለአዲሶቹ ገዥዎች እንዲስማማ የብሔር ብሔረሰቦችን የመሣሠሉ ሃሳቦች ጨምሮባቸው በ1984 በዓለሙ ገብረአብ አዘጋጅነት በብሔራዊ ቴአትር እንዲቀርብ ጥያቄ አቀረበ፡፡ጥያቄውን የተመለከቱት አዲስ የተሾሙት የብሔራዊ ቴአትር አስተዳደር ማንያዘዋል እንደሻው ቴአትሩ ‹በኮሚቴ መገምገም አለበት›› የሚል ውሣኔ አስተላለፉ፡፡ጸጋዬ ደግሞ ‹‹ቴአትሬ እዚህ አይገመገምም። ፑሽኪንን ማን ነው የሚገመግመው!››በማለት መለሠ።ከዚያም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ከነበሩት ታምራት ላይኔ ጋር ስሞታ አቀረቡ። እንዲሁም ጉዳዩን ወደ ባህል ሚኒስቴር በመውሰድ የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና ባለሙያዎች በተገኙበት ቴአትሩን አሳይቶ የይለፍ ፈቃድ ለማግኘት ቻለ፥ በወቅቱ ኢሃዲግጐች ‹በረሃ ሆነን ያንተን ቴአትር እናጠና ነበር› ብለውኛል እያለ ያሞካሻቸው ነበር። ያ ፍቅር ግን ብዙ አልቀጠለም።

  3. ውድ ወንድሜ ከበደ፣

    ስለ አስተያየትህ አመሰግናለሁ። ክፍል አንድ፣ አንቀጽ 6 ላይ ያነሳኋቸውን ጥያቄዎች ልጠቊምህ? ትኲረቴ በዋነኛነት በጸጋዬ ሥራዎች ላይ ነው። “ፀጋየ ገብረመድህን ሥልጣን ላይ ከነበረው መንግስት ጋር ሳይነካካ፤ በአቋሙ እና ባመነበት ፀንቶ እንደኖረ አድርጐ ለማቅረብ” ያልከው ጨርሶ አሳቤ ውስጥ አልነበረም። “ጸገመ የሚፈልገውን ያውቃል፤ አጋጣሚዎችንም ይጠቀምባቸዋል፤ ካስፈለገ መስዋእት ይከፍልባቸዋል” ብያለሁ (ክፍል 1፣ የመጨረሻው አንቀጽ)። ጸጋዬ በደርግ ታስሮ ነበር። በአንፃሩ፣ የአንደኛችን “መሞዳሞድ” የሌላኛችን ብልኃት ቢሆንስ?

    እንግሊዛዊቷ ፕሮፌሰር ጄን ፕላስታው ስለ ጸጋዬ የጻፈችው በእርግጠኝነት አይደለም፤ እንክዋን ከውጭ መጥታ፣ የደርግ ነገር ለአገሬውም ግራ ያጋባ ነበር። “It is hard to imagine that Tsegaye did not have some role to play in the sacking. He was certainly able to extend his patronage to ensure that his protégées…” በተረፈ፣ መረጃዋን ከየት እንዳገኘች መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል።

    ጸጋዬ ለውጭ አገር ፈረንጆች የሚያሳየውን “ማነህና ነው የምትጠይቀኝ” ዓይነት ግትርነት፣ ፕሮፌሰር ሞልቬር በ ብላክ ላየንስ መጽሐፉ ዘግቧል (የዌንዲ ቤልቸርን ቃለ መጠይቅ ማየት ይጠቅማል)። በደርግ ዘመን ባለሥልጣን የሆነ ሁሉ የደርግ ደጋፊ እንደ ሆነ መታሰብ የለበትም። ያረጀውን ሥርዓት አስወግዶ በሕዝባዊ አመራር ለመተካት፣ በመሠረተ ፍልስፍናው ተስማምቶ አፈጻጸሙ ላይ ግን አለመስማማት አለ፤ አንዳንዱም፣ ከውጭ ይልቅ ከውስጥ ሆኖ ምናልባት ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይል የነበረ ነው። ህወሓት አዲሳባ የገባ ሰሞን እውነተኛ ቀለሙን ቶሎ አላስታወቀም ነበር፤ በአማራ ኦሮሞ ትግሬ መከፋፈልን (የእያንዳንዱን ጎሳ ኢትዮጵያዊነት፣ የኢትዮጵያን አንድነት በተመለከተ) ግን የጸጋዬ አቋም አጠያያቂ ሆኖ አያውቅም። ለማንኛውም፣ ጥሩ ነጥብ አንስተሃል፤ የማላውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ሌሎች ደግሞ አሳባቸውን ይስጡበት። ሰላም ሁን። ምትኩ

  4. እኔ ያየሁት፥ እርሶም ሆኑ ፋሲል ስለ ፀጋየ የፃፉት እውነት፣ እውነት አለመሽተቱ ነው።የተጋነነ አድናቆት፣ የተለጠጠ ማሞካሸት ይበዛዋል።የተሳለው ፀጋየ ያልሆነውን ያልነበረውን ነው።በሥራዎቹ ላይ መወያያት፣ ቲያቲሮቹን፣ ግጥሞቹን መገምገም ጥሩም ነው፤ ይገባልም።ግን የእርሱ ዝና ጥግ በደረሰበት ሰዐት፥ ኪነጥበብ ለነበረው ወታደራዊ አስተዳደር አገልጋይ ነው የነበረችው።በፀሐፍት እና በካድሬዎች መካከል የነበረው ልዩነት የደበዘዘ ነው።አብዮቱ ዋዜማ ላይ ፀጋየ የፃፈው “እናት አለም ጠኑ” በጀርመናዊው የትያትር ፀሐፊ ላይ ተመርኩዞ ነው ቢባልም፥ አላማው ግን የሃይለስላሴን መንግስትን ማውገዝ ነበር።አፄው፥በላይ ዘለቀን በጭካኔ እንዴት እንደገደሉት ለማሣየት።ቲያትሩ ሲጀምር የሚያሣየው፥ የንጉሱ 80ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ የንጉሡን መወገድ የሚያሣይ በሬዲዮ የተላለፈ የደርግ መግለጫ፣ ታንኮች ሲርመሠመሡ በስክሪኑ ላይ በማሣየት ነው። እናት አለም ጠኑ ኢትዮጵያን በድህነት አረንቋ እንደኖረች ያሳያል።ምክንያቱም በበላይ ዘለቀ በመረገሟ።አገሪቷ ቆራጥ ልጆች እንዳኗራት። ደርግ ስልጣን ላይ ሲመጣ ያ እርግማን ተሻረ።ሲራክ ታደሰ ንጉሡን ሆኖ ተጫወተ።የምረቃው ቀን ተጋባዥ ማን ነበር? መንግስቱ ኃይለማርያም! https://www.facebook.com/photo/?fbid=4258692997695952&set=pcb.4258693101029275

    1. አባባልህ ይገባኛል። ከእኔ ባልተናነሰ/በተሻለ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዳሰብክበት ግልጽ ነው። እኔ የገመገምኩት ፋሲል የፃፈውን መጽሐፍ ከጸጋዬ ሥራዎች አኳያ መሆኑን አትዘንጋ። እንዳንተው ብዙ ጥያቄዎችን አንስቻለሁ። መወያየታችን ለመማማር ይጠቅመናል። በተረፈ፣ ፋሲልንም ጸጋዬንም በዐይነ ሥጋ አላውቃቸውም። ሲቻልህ፣ “እውነት እውነት አይሸትም፣ ተጋንኗል፣ የተለጠጠ ማሞካሸት ይበዛዋል” ላልከው አንድ ሁለት ምሳሌ እንደ አማራጭ ብትጠቅስ የበለጠ እንማማራለን። “በሥራዎቹ ላይ መወያያት፣ ቲያቲሮቹን፣ ግጥሞቹን መገምገም ጥሩም ነው፤ ይገባልም” ማለትህ ትክክል ነው።

Comments are closed.