“የመንግሥት አካሄድ ወደለየለት አምባገነንነት እንዳያመራን እና ከዴሞክራሲ የበለጠ እንዳያርቀንም ያስፈራል።”

“የመንግሥት አካሄድ ወደለየለት አምባገነንነት እንዳያመራን እና ከዴሞክራሲ የበለጠ እንዳያርቀንም ያስፈራል።”

ኢስሃቅ እሸቱ

ከአርቲስት እና ታጋይ ሃጫሉ ሁንዴሳ በግፍ መገደል በኋላ አገራችን ያለችበት ሁኔታ እጅግ ያሳስባል። ውጥረቱ እጅግ ያስፈራል። በዚህ መካከል በተፈጠረው ቁጣ እና ቀውስ እየሞቱ እና እየተገደሉ ያሉ ንጹሃን ሞት ከምንም በላይ ልብ ይሰብራል።

እንዲህ ዓይነት ሕዝባዊ ቁጣ ሲቀሰቀስ መንግሥት የሚወስደው የማረጋጋት እርምጃ እጅግ ብልሃት የተሞላበት እና ነገሮችን የሚያበርድ መሆን ነበረበት። እየሆነ ያለው ግን ያ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን። መንግሥት እጅግ ተጽእኖ ፈጣሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ሰብስቦ ማሰሩ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ኃላፊዎችም የኦሮሞ ፖለቲከኞችን መፈንቅለ‐መንግሥት በሚመስል ክስ መወንጀላቸው የተፈጠረውን ቀውስ ሊያባብስ እንጂ ሊፈታ እንደማይችል ግልጽ ነው። ከሐጫሉ አቀባበር ጋር የተፈጠረውን ችግር መንግሥት ያሥተናገደበት መንገድም ግራ የሚያጋባ ነው። መንግሥት ይህንን መንገድ መምረጡ እኔንም እንደበርካታዎች ሁሉ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ከትቶኛል።

እኒህ እርምጃዎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከሜዳው መገለላቸውን ለሚፈልጉ የቀኝ ክንፍ አክራሪዎች ደስታ እና ጊዜያዊ እፎይታ ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል። የአገር ሠላምን ሊያሰፍኑ ግን አይችሉም። «ጠላቴ ተመታልኝ» ዓይነት ስሜት ከጊዜያዊ እፎይታ ባለፈ ለአገር ሠላም መፍትሄ አይሆንም። በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እየተፈጠረ ያለው የመጠቃት ስሜት ከቀድሞውም ውጥረት የበለጠ እና የከፋ እንደሆነ ነው እየታየ ያለው። እኔ በበኩሌ ይህ ስሜት በለውጥ ጅማሬ ላይ ያለችውን አገር ወደከፋ ቀውስ እና ግጭት የሚከት ሆኖ ይታየኛል። የመንግሥት አካሄድ ወደለየለት አምባገነንነት እንዳያመራን እና ከዴሞክራሲ የበለጠ እንዳያርቀንም ያስፈራል። እስካሁን በጠ/ሚ ዐብይ ላይ ተጥሎ የቆየው የሪፎርም ተስፋ እንዳይጨልም ክፉኛ ያሳስበኛል።

ያም ሆነ ይህ የአገር ሠላም ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። በግርግር በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ ብሄር ነክ ጥቃት እንዳይደርስ መጠበቅም ሆነ ጥቃት ያደረሱ ሰዎችን ለሕግ ማቅረብ የመንግሥት ኃላፊነትም ግዴታም ነው። ዜጎች ምንጊዜም ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። በዚህ ምንም ጥርጥር የለም። ነገር ግን አስፈሪ ሕዝባዊ ቁጣ በተፈጠረበት ሁኔታ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ሰብስቦ ማሰር፣ «ለጊዜያዊ ማረጋጊያ ነው» መባል እንዳይቻል እንኳ መፈንቅለ‐መንግሥት በሚመስሉ ክሶችን በሚዲያ ማቅረብ ውጥረቱን ያበርዳል ብዬ አላምንም። በእነዚህ እርምጃዎች የተደሰቱ ሰዎችም ውጥረቱን እንደማያበርደው ያውቃሉ። «ጠላታችን ይመታልን እንጂ ሠላም ሌላ ጊዜ ይደርሳል» ዓይነት አመለካከት ይዟቸው ነው። ይህ ለአገር ሠላም በፍጹም አይጠቅምም።

መንግሥት ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ የተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እና ለዜጎች ጥበቃ ከማድረግ ጎን ለጎን አካሄዱን ቀይሮ ሌሎች የመፍትሄ አማራጮችን መመልከት፣ አስፈሪው ውጥረት በዘላቂነት የሚፈታበትን መንገድ ማሰብ፣ በሕዝብ ብርቅዬ ልጅ ሐጫሉ ድንገተኛ እና ምስጢራዊ አገዳደል የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የኦሮሞ ሕዝብን እና አመራሩን እንደአንድ ባለድርሻ አካል አድርጎ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። እኔ የሚታየኝ ይሄ ነው!

አላህ አገራችንን ከገባችበት አስፈሪ ቀውስ ያወጣልን ዘንድ እለምናለሁ!

Share this post

One thought on ““የመንግሥት አካሄድ ወደለየለት አምባገነንነት እንዳያመራን እና ከዴሞክራሲ የበለጠ እንዳያርቀንም ያስፈራል።”

  1. I don’t understand. You want the government to keep peace and security but you don’t want it to detain those who instigate and initiate these insecurities. Jawar had created a defacto gov’t and wasn’t listening to any form of dialogue unless it’s something he wanted to hear. How do we know if he loses in the election he would accept the results and doesn’t call on his supporters to riot? We haven’t heard any consolatory message from him about these killings rather his plan was to dismantle menelik’s monument and bury hacchalu there against the wishes of his family. Does that sound like a sane person ? The same goes for Eskinder Nega who is mobilizing the youth on the other side of the spectrum. I think the Ethiopian government has been patient beyond limits. The time for dialogue has already passed and even if you want to negotiate , you should only do that with people who would listen to reason.

Comments are closed.