እስራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ እንደገና ጥቃትን ለመጀመር ከፍተኛ ዝግጅቶችን እያካሄዱ እንደሆነ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ። አዲሱ ጥቃት ከዚህ በፊት ከተፈፀሙት ሁሉ የጠነከረ ሊሆን እንደሚችል ሁለት ባለስልጣኖችን በመጥቀስ ጋዜጣው ዘግቧል።ጋዜጣው የጠቀሳቸው የአሜሪካ ኃላፊዎች እንደሚሉት፣ በኢራን ላይ እንደገና ሊደረጉ ከታሰቡት የተቀናጁ ጥቃቶች መካከል ከባድ የቦምብ ጥቃቶችን በወታደራዊና መሠረተ ልማት ኢላማዎች ላይ ማካሄድ፣ በሰሜናዊ ባሕረ ሰላጤ በኻርግ ደሴት የሚገኘውን እና ኢራን ነዳጅ ለውጭ ገበያ የምትልክበት ቁልፍ መተላለፊያን መቆጣጠር፣ እና ከምድር በታች የሚገኙ የኒውክሌር ኃይል ማበልጸጊያ ቁሳቁስ ለማውጣት ኮማንዶዎችን ወደ ወደ ቦታው መላክን ያካትታሉ።
ከኢራን የበለጸገውን ዩራኒየም ማውጣት ከባድና አስቸጋሪ መሆኑን የዘገበው ጋዜጣው በሂደቱ ብዙ ሰዎች ሊጎዱ የሚችሉበት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል አስታውቋል።ኦፕሬሽኑን ለማካሄድ የደህንነት ቀጠና ለመፍጠር እንዲሁም ከኢራን የምድር ጦር ኃይሎች ጋር ሊዋጉ የሚችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የምድር ጦር ኃይሎች እንደሚያስፈልግ ጋዜጣው ጠቅሷል።
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ማክሰኞ ለሕግ አውጭዎች እንደተናገሩት፣ አሜሪካ “አስፈላጊ ከሆነ በበለጠ ጥንካሬ እና ከፍ ባለ ኃይል ኢራንን ትመታለች” በማለት ተናግረዋል።
ካለፈው ወር ጀምሮ በአሜሪካና በኢራን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የሰላም ውይይቶቹን ለማካሄድ ያስችላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል። ፓኪስታን በሁለቱ አገራት መካከል አሸማጋይ ሆና ለማቀራረብ ብትሞክርም፤ አገራቱ ጦርነቱን ለማስቆም የቀረቡትን ሀሳቦች ውድቅ አድርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓርብ ለፎክስ ኒውዝ እንደተናገሩት፣ ኢራን ከዚህ በፊት ተስማምታው የነበሩ በርካታ ስምምነቶችን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነችም። “ስምምነት ባደረግን ጊዜ፣ በሚቀጥለው ቀን ‘ምንም የምናውቀው ነገር’ በማለት ይክዳሉ” ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
ትራምፕ አርብ ዕለት በቻይና የሁለት ቀን ጉብኝታቸው ካጠናቀቁ በኋላ፤ ቴህራን ለ20 ዓመታት የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ብትገታ እንደሚቀበሉ ያሳወቁ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ማቆም አለባት ከሚለው አቋማቸው ለውጥ ማድረጋቸውን አሳይቷል። ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንቱ ኢራን መሣሪያ ማምረት በሚያስችላት ደረጃ ዩራኒየም ማበልፀጓን ሙሉ በሙሉ እንድታቆም እና የኒውክሌር መሣሪያ ፈጽሞ እንዳታመርት ሲጠይቁ ነበር።