የአሜሪካ አዲሱ የስደተኞች ሕግ እና አንደምታው

የአሜሪካ አዲሱ የስደተኞች ሕግ እና አንደምታው

በዚህ ሳምንት የትራምፕ አስተዳደር ያፀደቀው አንድ ህግ የስደተኛ ጠበቆችን እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እጅጒን ያስደነገጠ ነው። አስተዳደሩ የአሜሪካን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያለውን አሠራር የባሰ አክብዶታል። “በጣም ልዩ በሆኑ” ሁኔታዎች ብቻ ካልሆነ በቀር ግሪን ካርድ ለማግኘት የሚያመለክቱ ስደተኞች አገሪቱን ለቅቀው በመውጣት አገራቸው ከሚገኝ ኤምባሲ ወይም ቆንጽላ ጥያቄ ማቅረብ እንዳለባቸው የሚደነግግ።

እንደ ኤንፒአር ዘገባ፣ ይህ አዲስ ህግ በአገሪቱ ላለፋት አምሳ አመታት ሲተገበር የነበረውን የአሜሪካ ቪዛ ያላቸው ሰዎች በአገሪቱ እያሉ መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንዲያመለክቱ የሚያስችላቸውን አሠራር የሚቀለብስ ነው። እስካሁን ባለው አሠራር አጭር ጊዜ ለመቆየት የሚያስችል ቪዛ የተሰጠው ሰው፣ በተለያየ ምክንያት አገሪቱ ውስጥ መቆየት ከፈለገ እዛው እንዳለ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መጠየቅ ይችላል።ለምሳሌ ትምህርቱን ለመከታተል መጥቶ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በሓላ ሥራ ያገኘ ሰው እንዲሁም ለአጭር ጊዜ መጥቶ ትዳር የመሠረተ።የአሜሪካ የዜግነት እና ስደተኞች አገልግሎት ቃል አቀባይ ዛክ ካህለር “ከዚህ በኋላ አሜሪካ ወስጥ በጊዜያዊነት የሚኖሩ እና የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው፤ ከመጠን ያለፈ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልሆኑ በስተቀር” ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ለዚህ ለውጥ መነሻ ምክንያት አድርጐ ያቀረበው ህጉ መጀመርያውኑ ወደወጣለት አላማ መዋል አለበት በሚል ነው።በሌላ አነጋገር፣ ጊዜያዊ ቪዛ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት መረማመጃ መሆን የለበትም የሚል ነው።ተማሪዎች፣ ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ ያላቸው ወይም ቱሪስቶች አሜሪካ የሚመጡት ለተወሰነ ጊዜ እና አላማ ነው። ቆይታቸው “የመኖሪያ ፈቃድ ፍለጋ የመጀመሪያ ደረጃ” ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል። አዲሱ ፖሊሲ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ነው ተብሏል።እንደ ሲቢኤስ ዜና ዘገባ ከሆነ በየአመቱ ወደ 600,000 የሚደርሱ ሰዎች እዚያው አሜሪካ ውስጥ ሆነው ግሪን ካርድ ይጠይቃሉ።ከእነዚህም ውስጥ ተማሪዎች፣ H-1B ቪዛ ያላቸው መሐንዲሶች፣ ተመራማሪዎች፣ የውጭ አገር ሰራተኞች (expatriates)፣ የአሜሪካ ዜግነት ካለው ሰው ጋር በትዳር የተቆራኙ ወይም ስደተኞች ይገኙበታል።

ይህ አዲስ የወጣው ፖሊሲ የስደተኞችን ጥያቄ የሚመለከቱ ባለሙያዎችን አስደንግጧል። ዘ ሲያትል ታይምስ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው አንድ ጠበቃ፣ በትራምፕ አስተዳደር በህጋዊ የኢሚግሬሽን ላይ ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል “ምናልባትም በጣም ትልቁ” እንደሆነ ይናገራሉ፣ ይህም “የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያመለከቱ ቤተሰቦችን የሚነጣጥል ነው” ብለዋል።

አዲሱ ህግ ግልጽ በሆነ መልኩ ያላብራራቸው ነገሮች አሉ። የትኞቹን ዓይነት ቪዛዎች ነው የሚመለከተው? አሁን ላይ የመኖሪያ ፈቃድ ጠይቀው እየተጠባበቁ ያሉ ስደተኞች የሚስተናገዱት እንዴት ነው? አመልካቾች ከዩናይትድ ስቴትስ ወጥተው ለምን ያህል ጊዜ መቆየት አለባቸው? እነዚህ ጥያቄዎች ግልጽ መልሶችን አለማግኘታቸው ለሕግ ባለሙያዎች ራስ ምታትን ፈጥሯል። እንደ ዋሽንግተን ፖስት ገለፃ፣ ይህ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ህጋዊ ስደትን ለመግታት የወሰደው አዲስ እርምጃ ነው።ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የመኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) ትሰጣለች፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሰነዳቸው ይሁንታ እስከሚያገኝ እየተጠባበቁ ያሉ ስደተኞች የሚገኙት እዚያው አሜሪካ ነው።

የህጉ ተቃዋሚዎች አንዱ የሚያቀርቡት መከራከርያ ነጥብ ህጉ በግለሰቦች ላይ የሚፈጥረውን ምስቅልቅል ሁኔታ ነው። ወርልድ ሪሊፍ የተባለ ድርጅት በርካታ ቤተሰቦችን ‘አስተዳደራዊ ወጥመድ’ ውስጥ እንደሚጥላቸው ጠቅሷል። በቪዛ ገደቦች ወይም በግጭት ውስጥ ባሉ አገሮች፣ አመልካቾች ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት በውጭ አገራት ሊቆዩ ይችላሉ።እንደ አፍጋኒስታን ላሉ የአሜሪካ ቆንስላ አገልግሎቶች በተዘጉባቸው ሀገራት፣ ለዜጎች ሁኔታው የበለጠ ይወሳሰብባቸዋል።

ዴሞክራቶች ይህ ህግን ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድን ለመገደብ የሚደረግ አለአግባብ የሆነ እንቅስቃሴ ነው በማለት አውግዘውታል።በፕሬዚዳንት ባይደን ዘመን የአሜሪካ ዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት ዳይሬክተር ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ዶግ ራንድ “ዓላማው ግልጽ ነው፡ ግሪን ካርድን የሚያገኙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ፣ ምክንያቱም ዜግነት ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ስለሆነ ነው” ብለዋል። “ይህ አዲስ ፖሊሲ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጋዊ ስደተኞች፣ ከአሜሪካን ዜጎች ጋር በትዳር የተጣመሩትን ጨምሮ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ በመውጣት ግሪን ካርዳቸውን ለማግኘት ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውን እና ስራቸውን ለሳምንታት ከዚያም አልፎ ለወራት ለቀው እንዲወጡ ያስገድዳቸዋል” ሲሉ የዲሞክራቲክ ኮንግረስ አባል ቹይ ጋርሲያ በኤክስ ገጽ ላይ ፅፈዋል።

Share this post

Post Comment