የአሜሪካ አዲሱ የስደተኞች ሕግ

የአሜሪካ አዲሱ የስደተኞች ሕግ

በዚህ ሳምንት የትራምፕ አስተዳደር ያፀደቀው አንድ ህግ የስደተኛ ጠበቆችን እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እጅጒን ያስደነገጠ ነው። አስተዳደሩ የአሜሪካን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያለውን አሠራር የባሰ አክብዶታል። “በጣም ልዩ በሆኑ” ሁኔታዎች ብቻ ካልሆነ በቀር ግሪን ካርድ ለማግኘት የሚያመለክቱ ስደተኞች አገሪቱን ለቅቀው በመውጣት አገራቸው ከሚገኝ ኤምባሲ ወይም ቆንጽላ ጥያቄ ማቅረብ እንዳለባቸው የሚደነግግ።

እንደ ኤንፒአር ዘገባ፣ ይህ አዲስ ህግ በአገሪቱ ላለፋት አምሳ አመታት ሲተገበር የነበረውን የአሜሪካ ቪዛ ያላቸው ሰዎች በአገሪቱ እያሉ መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንዲያመለክቱ የሚያስችላቸውን አሠራር የሚቀለብስ ነው። እስካሁን ባለው አሠራር አጭር ጊዜ ለመቆየት የሚያስችል ቪዛ የተሰጠው ሰው፣ በተለያየ ምክንያት አገሪቱ ውስጥ መቆየት ከፈለገ እዛው እንዳለ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መጠየቅ ይችላል።ለምሳሌ ትምህርቱን ለመከታተል መጥቶ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በሓላ ሥራ ያገኘ ሰው እንዲሁም ለአጭር ጊዜ መጥቶ ትዳር የመሠረተ።የአሜሪካ የዜግነት እና ስደተኞች አገልግሎት ቃል አቀባይ ዛክ ካህለር “ከዚህ በኋላ አሜሪካ ወስጥ በጊዜያዊነት የሚኖሩ እና የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው፤ ከመጠን ያለፈ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልሆኑ በስተቀር” ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ለዚህ ለውጥ መነሻ ምክንያት አድርጐ ያቀረበው ህጉ መጀመርያውኑ ወደወጣለት አላማ መዋል አለበት በሚል ነው።በሌላ አነጋገር፣ ጊዜያዊ ቪዛ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት መረማመጃ መሆን የለበትም የሚል ነው።ተማሪዎች፣ ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ ያላቸው ወይም ቱሪስቶች አሜሪካ የሚመጡት ለተወሰነ ጊዜ እና አላማ ነው። ቆይታቸው “የመኖሪያ ፈቃድ ፍለጋ የመጀመሪያ ደረጃ” ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል። አዲሱ ፖሊሲ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ነው ተብሏል።እንደ ሲቢኤስ ዜና ዘገባ ከሆነ በየአመቱ ወደ 600,000 የሚደርሱ ሰዎች እዚያው አሜሪካ ውስጥ ሆነው ግሪን ካርድ ይጠይቃሉ።ከእነዚህም ውስጥ ተማሪዎች፣ H-1B ቪዛ ያላቸው መሐንዲሶች፣ ተመራማሪዎች፣ የውጭ አገር ሰራተኞች (expatriates)፣ የአሜሪካ ዜግነት ካለው ሰው ጋር በትዳር የተቆራኙ ወይም ስደተኞች ይገኙበታል።

ይህ አዲስ የወጣው ፖሊሲ የስደተኞችን ጥያቄ የሚመለከቱ ባለሙያዎችን አስደንግጧል። ዘ ሲያትል ታይምስ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው አንድ ጠበቃ፣ በትራምፕ አስተዳደር በህጋዊ የኢሚግሬሽን ላይ ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል “ምናልባትም በጣም ትልቁ” እንደሆነ ይናገራሉ፣ ይህም “የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያመለከቱ ቤተሰቦችን የሚነጣጥል ነው” ብለዋል።

Share this post

Post Comment