የአሜሪካ በቀጥታ ጦርነቱ ላይ መሳተፋ ያለው አንደምታ

የአሜሪካ በቀጥታ ጦርነቱ ላይ መሳተፋ ያለው አንደምታ

አሜሪካ እስራኤልን በመደገፍ በቀጥታ ወደ ጦርነቱ ውስጥ ትገባለች ወይስ አትገባም የሚለው ጥያቄ አሁን መልስ አግኝቷል።ዶናልድ ትራምፕ ብለውት የነበረውን ሁለት ሳምንት እንኳ መጠበቅ አልቻሉም።የአሜሪካ መከላከያ ኃይል በኢራን ሦስት የኒውክሌር ተቋማት ላይ የቦምብ ድብደባ ፈፅሟል።በተራራዎች መካከል የተደበቀውንና የእስራኤል መከላከያ ኃይል የአየር ጥቃት ሊያወድመው ያልቻለውን ፎርዶን ጨምሮ።ይህ ከባድ መዘዝ ያለው ውሳኔ ነው ይላሉ ታዛቢዎች።ክልሉን ወደ አደገኛ አረንቋ የሚያስገባ። የፕሬዘዳንቱን የአገዛዝ ዘመን ታሪክም በበጐም ሆነ በክፉ ሊቀርፅ የሚችል።

ትራምፕ፥ ጦርነቱ ላይ በቀጥታ ከመሳተፋቸው በፊት፥ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የእስራኤል የአየር ጥቃት፥ የኢራንን የኒውክለር ማበልፀጊያ ጣቢያዎችንና ወታደራዊ መዋቅሮች በማወዳደም ላይ ናቸው፤ በርካታ ወታደራዊ ጄኔራሎችን ገድለዋል።

ያለ ፖለቲካዊ ማዕቀፍና ምንም አይነት ትንኮሳ በሌለበት አሜሪካ ጉልበትና ሃይል ለመጠቀም መወሰኗ፤ ሕዝቡ የመጀመርያ ሠለባ የሚሆንበት አረንቋ ውስጥ ነው የሚያስገባው ፤ የማይጠገን ስብራትንም ያስከትላል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች። እልህን፣ ቁጭትን እና የበቀል ጥማትን ያገነግናል። ኢራቅን፣ አፍጋኒስታንን፣ ሊቢያን ማስታወስ ይበቃል። አሜሪካ እጇን የነከረችበት ግጭትና ቀውስ ውጤቱ በተደጋጋሚ ታይቷል። ሀገራት ፈራርሰዋል፤ የበርካታ ሕይወት ተቀጥፏል።ብዙ ሃብት ንብረት ወድሟል። የአንድ ሀገር ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲጨራረሱ ተደርጏል፤ ደመኛ ሆነዋል። ብዙዎች አሜሪካንን ጠል ሆነዋል፤ ጽንፈኝነት ጨምሯል።ሳዳም ሁሴን ከተወገደ በኋላ ኢራቅ የጽንፈኛ ግለሰቦችና ቡድኖች መፈልፈያ ሆናለች፡፡ ራሱን እስላማዊ መንግሥት በማለት የሚጠራው ቡድን፤ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ (አይሲስ) በኢራቅ ተስፋፍቶና ተጠናክሮ ለቀጠናው ስጋት ሆኗል።አፍጋኒስታን በታሊባን ቁጥጥር ስር በድጋሚ መውደቋ ፣ ሊቢያ ለረዥም ዓመታት የመሯት ሞአማር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የምትገኝበት ቀውስ፣ በአፍሪካ የሳህል አካባቢ ታጣቂ ጂሃዲስት ቡድኖች በፍጥነት እየተስፋፉ መምጣት የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ያስከተለው ቀጥተኛ ሆነ ተዘዋዋሪ ጉዳት collateral damage ብዙ መሆኑን ያሳያል። ወደ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት፣ የበርካታ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖርያ፣ በስፋት ከፈረንሣይ አንጻር ሶስት እጥፍ የምትበልጠው ኢራን ተመሳሳይ ነገር ያጋጥማት ይሆን? የአሜሪካ ጥቃት ከመሰነዘሩ አንድ ቀን በፊት፣ ፎርየን አፌርስ በተባለው መጽሔት ላይ ኃሳባቸውን ያሰፈሩት፣ በእስራኤል የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዳን ኩርትዘር፣ “ኢራን አሜሪካ ለምትፈፅመው ጥቃት በአሜሪካ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች ብለዋል።ይህ ደግሞ አሜሪካ ተጨማሪ ጥቃቶች እንድታደርግ ያስገድዳታል። ከዚያ በመቀጠል አሜሪካ የሚቀራት የመጨረሻ ግብ የስርዓት ለውጥ ብቻ ይሆናል። ያም ዩናይትድ ስቴትስ እንደገና የስርዓት ለውጥ የማምጣት እንቅስቃሴ ውስጥ ልትሳተፋ ነው ማለት ነው” ብለዋል። “Iran would almost certainly retaliate by killing American civilians. That, in turn, would compel the United States to reciprocate in an iterative process. Soon enough, the only targets left for Washington to would be the Iranian regime’s leaders, and the United States would again go into the regime-change business.” ይህ ሁኔታ በ 2003 እ.አ አሜሪካና ብሪታኒያ በኢራቅ ላይ የፈፀሙትን ወረራ ይመስላል።ለወረራው ምክንያት የነበረው በኢራቅ አለ የተባለው የጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ባይገኝም የኢራቅ ነዋሪዎችን እና የአሜሪካ ወታድሮችን ግን ዋጋ አስከፍሏል።ኢራቅን ኃይለኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ከትቷት ያንን በመከተል እስላማዊ መንግስት ሊነሳ ችሏል። በመጋቢት ወር የአሜሪካ ብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ቱልሲ ጋባርድ ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን ወደ ማይታወቅ ደረጃ ብታሳድግም “የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እየገነባች አይደለም” ብለው ነበር። ይህንን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ “የተሳሳተ መረጃ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ፤ የራሳቸውን የስለላ ተቋም የሥራ ውጤት በመቃረን።

ኢራን የኒውክሌር ማበልጸጊያ ፕሮግራሟ ለሰላማዊ አገልግሎት ነው ብትልም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ከብዙ ዓመታት ጀምረው በድብቅ የጦር መሳሪያ እያመረተች ነው በማለት ይወቅሷታል።እውነታውንና የባለሙያዎችን አስተያየት ችላ ማለት የትራምፕ የተለመደ ፀባያቸው ቢሆንም ይህ ክስተት የሚያሳየው ሌላ ነገር ኔታንያሁ በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ የሚያሳድሩትን ታላቅ ተፅእኖ ነው።የእስራኤል የረጅም ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር በፖለቲካ ሕይወታቸው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በዓለም ላይ የደቀነውን አደጋ ማስጠንቀቅ የግላቸው ተልዕኮ በማድረግ ይታወቃሉ።እ.አ.አ በ2023 ጥቅምት ወር ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፤ እስራኤል የሚሰነዘሩባትን ስጋቶች በሙሉ ለማስወገድ ወሰነች። እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በአየር እና በምድር ጥቃት ስታደርስ ቆይታለች። እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሰላማውያን ዜጎች መቋጫ በሌለው የሞት ዑደት ውስጥ ናቸው። እንዲሁም በሊባኖስ በሚገኙ የሂዝቦላ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ አካሄዳ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ገድላለች። እንደ እስራኤል እይታ አደጋ ለመፍጠር የቀረችው አገር ኢራን ብቻ ነች። አጋሮቿ ተዳክመዋል፤ በሶርያ የባሺር አል-አሳድ አገዛዝ አክትሟል። ኢራን በኑክሌር መሣሪያዋ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ በምትደራደርበት ወቅት ፤ኔታንያሁ በኢራን ላይ የፈጸሙት ጥቃት የወዳጃቸውን ትራምፕን እጅ ጠምዝዞ ጦርነት ውስጥ ማስገባት ይመስላል።ምክንያቱም እሳቸው ብቻ ናቸው የፎርዶ የኒውክሌር ጣቢያን ለመምታት የሚችል፤ 13 ቶን የሚመዝነው እና እጅግ ከባድ እና ኃይለኛ “Massive Ordnance Penetrator” የተባለ ቦምብ ያላቸው። በ2013 ፔንታጎን ማሻሻያዎችን በማድረግ ይህ ቦምብ ፎርዶን እና ሌሎች የኒውክሌር ተቋማትን እንዲያጠቃ በማለም ሠርቶታል። ዓላማው ዩናይትድ ስቴትስ ጥቃት የመሰንዘር ወታደራዊ ችሎታ እንዳዳበረች እስራኤልን ማሳመን ነበር ። እስከዚያው ድረስ፥ ከኢራን ጋር የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን እንድትገድብ የሚያደርግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ ገብተው የኒውክሌር ማብላያዎቹ ከሲቪል ዓላማ ውጪ ለጦር መሳሪያ ማምረቻ አለመዋላቸውን አንዲከታተሉ ስምምነት ለመፈራረም። በምላሹም ኢራን ኢኮኖሚዋን ካሽመደመደው ማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ተስማምተው ነበር። እ.አ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን ሀገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል የኢራን የኑክሌር ስምምነት በቪየና ተፈረመ። ሆኖም እአአ በ2016 ትራምፕ አገራቸው ከስምምነቱ መውጣቷን አሳውቀዋል። ዶናልድ ትራምፕና ኔታንያሁ ስምምነቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሲተቹት ነበር።

እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት የሕልውናዋ ዋና አደጋ አድርጋ ትቆጥረዋለች። የእስራኤል ባለሥልጣናትም በቀጣናው እስራኤልን የሚወጉ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች ብለው የሚከሷትን ኢራንን እንደዋና አደጋ ይመለከቷታል።

 “ከእሥራኤል አኳያ ስናየው፣ የእስራኤል እርምጃ ስትራቴጂያዊ ግልፅነት አለው ይላሉ ሬይድ ስሚዝ Stand Together የተባለ “ቲንክ-ታንክ” (የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል) ተንታኝ። “አሜሪካ ግን በቅርብ ዓመታት ባካሄደችዉ ዉጊያ ከዚህ አንፃር የከሸፈ ነበር። በሌሎች አገሮች የሚካሄዱ ጦርነቶች የዩናይትድ ስቴትስ ጦርነቶች መሆን የለባቸውም። ” በማለት ይጨምራሉ። ሃዋርድ ፍሬንች የተባለ ተንታኝም ፎርየን አፌርስ በተባለው መጽሔት ላይ “ዩናይትድ ስቴትስ መሆን እንዳለበት እስራኤልን ለመከላከል ቁርጠኛ አቋም የወሰደች አገር ነች፤ ይሁን እንጂ ብሔራዊ ጥቅሟን ከመካከለኛው ምሥራቅ ቀንደኛ አጋሯ ለመለየት ያላት አቅም ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል።” ብለው ፅፈዋል። (The United States is rightly committed to the defense of Israel, but it has suffered a progressive decline in its ability to distinguish its national interests from those of its most important traditional Middle Eastern ally.) የአሜሪካ ሁለቱ አስተዳደሮች እስራኤል በጋዛ ውስጥ በተከታታይ የምትፈፅመውን ጥቃትና በዌስት ባንክ ፍልስጤምን የማጥፋት እና ህዝቦቿን የማፈናቀል ፖሊሲ እንድታቆም በቂ ጫና ሲያሳድሩ አልነበረም።ከዚያም አልፎ፥ የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው አንዱ ለሌላኛው እውቅና በመስጠት የሁለት መንግስታት መፍትሔ እንዲተገበር ዋሽንግተን ምንም አይነት ጫና ስታደርግ አልነበረም።

Share this post