“የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በሚል ርዕስ በአምባሳደር ዘውዴ ረታ ከተፃፈው መጽሃፍ ላይ የተወሰደ
በፋሽስት የተወረረችውን ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ለሚደረገው ጦርነት በካርቱም ስብሰባ ላይ በተወሰነው መሠረት፤ ሜጀር ኦርድ ሻርል ዊንጌት (Orde Charles Wingate) የተባለው እንግሊዛዊው የጦር መኰንን፤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለሚመሩት ዘመቻ አዘጋጅና አማካሪያቸው እንዲሆን የታላቋ ብሪታንያ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦር ዋና አዛዥ ዤኔራል ኧርል¸ዌቨል መርጦ አቀረበው፡፡ የጦር ሚኒስትሩ አንቶኒ ኤደን ለዚህ ኃላፊነት የተመረጠውን መኰንን ሹመት ከማጽደቁ በፊት፣ ስለሰውየው ታሪክና ችሎታ እንዲሁም ስለጠባዩና ስለ አቋሙ በዝርዝር ማወቅ አስፈልጐት ነበር፡፡
እ.ኤ.አ የካቲት 26 ቀን 1903 ዓ.ም የተወለደው ኦርድ ዊንጌት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከፈጸመ በኋላ፤ በእንግሊዝ አገር በታወቀው በወልዊች (Woolwich) በሚገኘው ሮያል ሚሊታሪ አካዳሚ የመድፈኛ መኰንን ሆኖ ተመረቀ፡፡ የዊንጌት ቤተሰቦች በአባቱም ሆነ በእናቱ በኩል ያሉት የውትድርና ሞያ የተማሩና ያገለገሉ ናቸው፡፡ለምሳሌም ያህል፤ አባቱ ሻርል ዊንጌት በውትድርና ሞያው የአገልግሎት ዘመኑን ያሳለፈው በሕንድ በተቋቋመው የታላቋ ብሪታንያ ጦር ሠራዊት ውስጥ ሲሆን፤ የአባቱ አጐት ሰር ሪጂናልድ ዊንጌት ደግሞ፤ (Sir Reginald Wingate) ከ1899 እስከ 1916 ዓ.ም ድረስ የሱዳን አገረ ገዥ ሆኖ ከሠራ በኋላ፤ ከዚያ ቀጥሎ ለሁለት ዓመታት በግብፅ የታላቋ ብሪታንያ ኮሚሽነር የነበረ ነው፡፡ኦርድ ዊንጌትም በበኩሉ፤ በሚሊታሪ ሞያ ለመቀጠል የተቆረጠ ውሳኔ ያደረገው፤ ይህንን የቤተሰቡን ታሪክና ፈለግ በመከተል ነው እየተባለ ይነገርለታል፡፡
እ.ኤ.አ በ1928 ዓ.ም ኦርድ ዊንጌት የሐያ አምስት ዓመት ወጣት መኰንን በነበረበት ጊዜ፤ በአባቱ አጐት በሰር ሪጂናልድ ዊንጌት ምክርና እርዳታ፤ ሱዳን ላይ በሚገኘው በእንግሊዝ የጦር ድርጅት ተዛውሮ፣ ሮዛይር እና ጋላባት በተባሉት ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያዋስነት ግዛቶች የፀጥታ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ፡፡ በእነዚሁ ሁለቱን አገሮች፤ ሱዳንና ኢትዮጵያን በሚያካልሉት ጠረፎች ላይ፣ የሰውን ልጅ “ባሪያ” እያሉ በገንዘብ የሚሸጡትን ጨካኞችና እንዲሁም ዝሆኖችን እየጨፈጨፉ “የአሰናባሪ” ንግድ የሚያካሂዱትን ሕገወጦች፤ መቶ አለቃ ዊንጌት እያደነ ለመያዝ በወሰደው የጠነከረ እርምጃ፤ እጅግ የሚያስደንቅ ውጤት ለማስገኘት ቻለ፡፡በዚህ በኢትዮጵያና በሱዳን ወሰን ላይ ሲካሄድ የቆየውን ሕገወጥ የንግድ ሥራ አድፍጦ በማጥመድ ዊንጌት የተጠቀመበትን ዘዴ፤ እሱም ወደ ሌላ ቦታ ከተዛወረ በኋላ ባለሥልጣኖቹ እንዲቀጥል በማድረጋቸው፤ የወጣቱ መኰንን ስምና መልካም ዝና ለብዙ ጊዜ ሲደነቅ የኖረ ሆኗል፡፡
እ.ኤ.አ በ1936 ኦርድ ዊንጌት ዓ.ም በታላቋ ብሪታንያ ምግዚትነት በሚተዳደረው በፓሌስቲን ተዛውሮ፣ በዚያ ላለው የጦር ሠራዊት የመረጃ መኰንን ሆነ፡፡ወጣቱ የጦር መኰንን ፓሌስቲን ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ፣ አይሁዳውያኖች ነፃነታቸውን ለማወጅና የእሥራኤልን መንግሥት ለማቋቋም የሚያደርጉትን ጥረት ከልዑ የሚደግፍና የሚያምንበት በመሆኑ፤ የዕብራይስጥን ቋንቋ ሌት ተቀን አጥንቶ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ ቋንቋውንና ሥነ፡ ጽሑፉን ለማወቅ ቻለ፡፡ ዊንጌት፤ ምንም እንኳ የይሁዳ ዘር እንደሌለበት የታወቀ ቢሆንም፤ ለእነሱ ያለው ስሜትና ድጋፍ ከሚገባ በላይ ግልጽ ሆኖ በመታየቱ፤ በአለቆቹ ዘንድ የተወደደ አልነበረም፡፡ወጣቱ መኰንን በሞያው ደፋርና መንፈሰ ጠንካራ፣ ብልህና አስተዋይ ከመሆኑም በላይ፤ በሚያምንበት ፀንቶ መገኘቱ መልካም ዝና ቢያተርፍለትም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለበላዮቹም ሆነ ለበታቾቹ፤ ተግባቢ ወይም ምቹ የሆነ ጠባይ ስለሌለው፤ አስቸጋሪና እምቢተኛ ነው የሚል አስተያየት ተወስዶበታል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1936 እስከ 1939 ዓ.ም ድረስ በፓለስቲን በኖረበት ዘመን፤ ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ከይሁዲዎቹ ጋር የሚያደርገው መቀራረብና ወዳጀነት፤ ከዚህም አልፎ በሚችለው ሁሉ የአገሩ ነዋሪ ከሆኑት ዓረቦች ጋር ልዩነት እየፈጠረ፤ ለይሁዲዎቹ ፊት ለፊት የሚያደርገው አድልዎ የበላይ አለቆቹን እጅግ አድርጐ የሚያሳስባቸው ሆነ፡፡ ብዙ ምክርና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም፣ ኦርድ ዊንጌት ከዕምነቴ አልዛነፍም አለ፡፡እንዲያውም፤ ከቀን ወደ ቀን ለይሁዲዎቹ ያለው ጽኑ ድጋፍ እየጨመረ፤ ወጣቶቹን በሥውር የደፈጣ ውጊያ በማስተማር ለነፃነታቸው ለሚያደርጉት ጥረት ዋና ረዳታቸውና ፕላን ቀያሻቸው ሆነ፡፡
እንግዲህ! ሜጀር ኦርድ ዊንጌት የተሰጠውን ሚሲዮንእየጣሰ፤ የፖለቲካውን ጉዳይ በመከታተል ይሁዲዎቹን ለመርዳት የሚሠራው ሁሉ አደገኛሆኖ ስለተገመተ፤ በግንቦት 1939 ዓ.ም በፓለስቲን የታላቋ ብሪታንያ ጦር አዛዥ የሆነው ዤኔራል ዌቨል፤ ከነበረበት ሥራ ላይ አስነሥቶ ወደ እንግሊዝ አገር እንዲመለስ አደረገው፡፡ በዚያን ጊዜ በፓሌስቲን የነበሩት የዊንጌት አለቆችም ስለመኰንኑ የገለጹት አስተያየት “ኦርድ ዊንጌት በሞያው የሚከበር ጀግና ወታደር ቢሆንም፤ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት እየወጣ የሚያደርገው የፖለቲካ ንቅናቄ አደገኛነቱ በግልጽ ስለሚታይ፤ከፓሌስቲን መዛወሩ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የፓሌስቲንን ጉዳይ በሚመለከት ሥራ መመደብ የለበትም…” የሚል ስለሆነ፤ የፓሌስቲን የጦር አዛዥ ይህንኑ ሐሳብ ተቀብሎ ከመፈጸም በስተቀር ሌላ መንገድ አልነበረውም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ዤኔራል ኧርል ዌቨል፣ ሜጀር ዊንጌት ከተሰጠው ኃላፊነት እየወጣ፤ ለይሁዲዎቹ ድጋፍ ሰጭ ሆኖ መገኘቱ የተገባ አለመሆኑን ደህና አድርጐ ቢያውቅም፤ ስለ መኰንኑ የውትድርና ሞያ ያለውን አድናቆት አልቀነሰም ነበር።ስለዚህም፣ “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” ለተባለው ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዘውድ፤ ኦርድ ዊንጌት መልካም አስተያየት እንደሚኖረው ስለሚያምን፤ በካርቱም ስብሰባ በተወሰነው መሠረት፤ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመቻ ዝግጅትና ኃላፊነት ከእሱ የተሻለ ሌላ የጦር መኰንን አይታየኝም ብሎ አቀረበው፡፡
የጦር ሚኒስትሩ አንቶኒ ኤደንም፤ ስለ ዊንጌት የቀረበለትን የመረጃ ሪፖርት በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ፤ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦር አዛዥ ዤኔራል ዌቨል በሰጠው ሐሳብ ተስማምቶ፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በፋሽስት ላይ ለሚያደርጉት ዘመቻ አዘጋጅና የኦፕሬሽኑ መሪ እንዲሆን፤ በሌተና ኮሎኔልነት ማዕረግ ሹመቱን አጸደቀለት፡፡ዊንጌት፤ ከፓሌስቲን ወደ እንግሊዝ አገር ከተዛወረበት አንድ ዓመት ተኩል ከሚሆን ጊዜ ጀምሮ፤ የበላይ አለቆቹ በእሱ ላይ መልካም አስተያየት እንደሌላቸውና ለወደፊቱም የተሻለ ዕድል እንደማይሰጡት ተሰምቶት ሞራሉ ተዳክሞ ነበር፡፡ በኅዳር ወር 1940 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ ከፋሽስት ጋር ለሚደረገው ጦርነት፤ በሌተና ኮሎኔልነት ማዕረግ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የዘመቻ ጦር አዘጋጅና መሪ እንድትሆን ተመርጠሃል የሚለው ቴሌግራም ሲደርሰው ያልጠበቀውና ያላሰበው በመሆኑ፤ ለጊዜው ማመን አቅቶት ነበር፡፡ ዤኔራል ዌቨል እንደገመተው፤ የኢትዮጵያ ነገሥታት ከይሁዳ የዘር ሐረግ አላቸው እየተባለ የሚነገረውን ታሪክ ዊንጌት በመልካም አስተያየት ስለሚመለከተው፤ ይህን የተሰጠውን ኃላፊነት የተቀበለው እጅግ በጋለ መንፈስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት፤ የዚህን የዘውድ ታሪክና የኢትዮጵያን ሕዝብ ነፃነት
ለማስመለስ፤ በቆራጥነትና በጀግንነት ተዋግቶ ጠላትን ድል እንደሚያደርግ ታጥቆ መነሣቱን ለዤኔራል ዌቨል ካስታወቀ በኋላ፤ ኦርድ ዊንጌት ጊዜ ሳይፈጅ ገሥግሶ ወደ ሱዳን መጣ፡፡
ዊንጌት ካርቱም እንደደረሰ፤ ከሁሉ አስቀድሞ በሰፊው የተነጋገረው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የፖለቲካ ኦፊሰር ሆኖ ከተመደበው ከቻፕማን አንድርውስ ጋር ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከሎንዶን ተነስተው ካርቱም ከደረሱበት ካለፉት አምስት ወራት ጀምሮ የሱዳን አገረ ገዢ ሰር ስቲዋርት ሳይምስና፣ የጦሩ አዛዥ ዤኔራል ዊሊያም ፕላት፣ የጃንሆይን መምጣት ባለመቀበል የፈጸሙባቸውን በደል
ዘርዝሮ ስለአስረዳው፤ ዊንጌት እጅግ አድርጐ አዘነ፡፡

ቻፕማን ለዊንጌት በሰፊው እንዳስረዳው፣ በሱዳን ያሉት ባለሥልጣኖች አገረገዥው ስቲዋርት ሳይምስና የጦር አዛዡ ዊሊያም ፕላት፣ ሙሶሊኒ ከሂትለር ጋር መሰለፉን ከማወጁ በፊት፣ ለፋሽስቱ መንግሥት አድናቂዎችና በተለይም የኢትዮጵያ ምክትል ንጉሥ (Vice Roy) ከሆነው ከዱካ-ዳ-ኦስታ ጋር ከፍ ያለ የወዳጅነት ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ይህ ወዳጅነት የተመሰረተው፣ በሱዳንና
በኢትዮጵያ ወሰን ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሽፍቶችና ሕገ ወጥ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ተባብረው ለማጥፋት የወሰዱትን እርምጃ ምክንያት በማድረግ ነው::ለዚህም፤ የኢትዮጵያ ም/ንጉሥ የተባለው ካርቱም መጥቶ ጉብኝት ሲያደርግ፣ ከፍ ያለ አቀባበልና መስተንግዶ ተደርጐለታል፡፡ በተጨማሪም የፋሽስቱን መንግሥት እነፕላት የሚፈሩት፣ በምሥራቅ አፍሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ፣ በሰሜን፣ በሊቢያ ያሠፈረው የምድር ጦር ኃይል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሲሆን፤ ያሉትም የአየር ኃይል ተዋጊ አይሮፕላኖች ቁጥራቸው ከአምስት መቶ በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ በዚህ አንፃር፤ ታላቋ ብሪታኒያ ግን፤ በግብፅና በሱዳን፣ በፓሌስቲንና በኤደን፣ እንዲሁም በኬንያና በዑጋንዳ ያላት የጦር ኃይል ከመቶ ሺህ አይበልጥም፡፡ስለዚህ፤ በካርቱም ያሉት ባለሥልጣኖቻችን ለፋሽስት መንግሥት ካላቸው መልካም የሆነ የግል ስሜት በላይ፣ የሙሶሊኒ የጦር ኃይል እጅግ አድርጐ የሚያሠጋቸው ስለሆነ፣ ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚያስቡ ወይም የሚጨነቁ አይደሉም፤ ሲል ቻፕማን አንድርውስ፤ ትክክለኛውን ሁኔታ ደህና አድርጐ አብራርቶለታል፡፡ኦርድ ዊንጌት፤ ቻፕማን የገለጸለትን ጠቅላላ ሁኔታ ካዳመጠ በኋላ፤ በወጉ መሠረት ወደ ዤኔራል ፕላት ቢሮ ሄዶ ቪዚት አደረገ፡፡ ከዚያም በቀጥታ ከካርቱም ሠላሳ ማይልስ ርቆ ወደሚገኘው ወደ ጀበል አውልያ በአውቶሞቢል ተጉዞ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር ተገናኝቶ ተዋወቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ የተቀበሉት በሞቀ መንፈስ ሲሆን፤ እሱም በደስታ መንፈስ የሚከተለውን ንግግር አደረገላቸው፡፡
ጃንሆይ! እኔ ወደ እርስዎ የመጣሁት ትልቅ ኃላፊነት ተቀብዬ ነው፡፡ ከባድ ነው ብዬ የምጠራው ኃላፊነት፣ በፋሽስት መንግሥት በግፍ የተቀማውን የአገርዎን ነፃነት ለማስለቀቅና የግርማዊነትዎ የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ በመንበርዎ ላይ እንዲመለስ ለማድረግ ስለሆነ ነው፡፡ ይህም ሐሳብ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምናልባትም ቢበዛ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ እንዲፈጸም የሚያስፈልግ ነው፡፡ የግርማዊነትዎ ዘመቻ የሚያመራው፤ ከሱዳን በቀጥታ እስከ መናገሻ ከተማዎ እስከ አዲስ አበባ ስለሆነ፣ የመጀመሪያው ግዳጃችን የጐጃም ግዛትዎን ነፃ ማድረግ ነው፡፡ ሌሎቹን የምንሠራቸውን ሁሉ በፕላን እየቀየስን በየመልካቸው እርምጃ እንወስድባቸዋለን፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ ግርማዊነትዎ የደረሰብዎትን መከራና ፈተና፣ በሰፊው ትዕግሥትዎና በማይበገረው ጥንካሬዎ እንደተቋቋሙት ሁሉ አሁንም ከፊታችን የተደቀነውን ከባድና አስቸጋሪ የሆነውንም የነፃነት ትግል አሸንፈው፣ ለድሉ ደስታ እንደሚበቁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለዚህም ግብ፣ የጦሩን ፕላን እንዳዘጋጅና የግርማዊነትዎን ዘመቻ እንድመራ፤ ከአገሬ ከታላቋ ብሪታኒያ መንግሥት ኃላፊነቱን እንድቀበል በመመረጤ የተሰማኝን ጥልቅ የሆነ ክብርና ደስታ ሳልገልጽልዎ ማለፍ አልፈልግም፡፡
ጃንሆይ! እንግዲህ እስከዛሬ ሲያደርጉት እንደቆዩት ሁሉ፤ እምነትዎን እንዲያጸኑ ተስፋዎን እንዲያጠነክሩ እያሳሰብኩ፤ በመጨረሻም ድሉ የእርስዎ መሆኑን እንዲያውቁት ከልብ የመነጨ መልካም ሐሳቤንና መልካም ምኞቴን አቀርብልዎታለሁ፡፡
ከዊንጌት ንግግር በኋላ፤ ጃንሆይም ወዲያውኑ አከታትለው አጠገባቸው በነበሩት በአርበኛው በአቶ መኰንን ደስታ አስተርጓሚነት የሚከተለውን መልስ ሰጡ፡፡
“የታላቋ ብሪታንያ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ዤኔራል ዌቨል የእርስዎን መሾም ሲገልጹልኝ፤ አያይዘው የላኩልኝን የሕይወት ታሪክዎን አንብቤ እጅግ ደስ ብሎኛል፡፡ የጠለቀ ከፍተኛ ትምህርት የፈጸሙና በውትድርና ሞያዎም፤ እስከዛሬ ያከናወኑት ሁሉ የተወደደና የተደነቀ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነቴ ሹመትዎን የተቀበልኩት፤ ከታላቅ ደስታና ከሙሉ
ዕምነት ጋር ነው፡፡ የተሰጠዎትን ከፍተኛ ኃላፊነት ከግቡ ለማድረስ በሚያደርጉት ጥረት፤ ፈጣሪያችን እንዲረዳዎ ጸሎታችንና መልካም ምኞታችን አይለይዎትም፡፡ አሁን ስለ እኔ ሲናገሩ፤ “እስከአሁን የደረሰብዎትን መከራና ፈተና በትዕግሥት ለመቋቋም ያሳዩት ጥንካሬ የሚደነቅ ነው ብለውኛል…፡፡ ስለዚሁ መልካም አስተያየትዎ ከልቤ የሚሰማኝንና የማምንበትን እውነቱን ልገልጥልዎ እወዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንድመራ ከባዱን ኃላፊነት የተቀበልኩት በእግዚአብሔር ፈቃድና በሕዝቤ ፍላጐት ስለሆነ፤ ያለብኝን ግዳጅ ለመፈጸም ማናቸውም መከራና ፈተና ሊገታኝ አይገባም፡፡ በሕይወት አለሁ ድረስ፤ በአገሬ ጉዳይ ማናቸውንም ችግር መቀበልና መቋቋም አለብኝ፡፡ስለዚህም፤ እስከ ዛሬ የደረሰብኝን ሁሉ ከምንም አልቆጥረውም፡፡ ዋናው ዓላማዬ፤ የአገሬ ነፃነት ከባዕድ ቀንበር እስኪላቀቅ ድረስ፤ ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ በተቻለኝ አሟልቶ መፈጸም ስለሆነ፤ ወደፊትም በማደርገው ጥረት ብዙ ፈተና እንደሚገጥመኝ ደህና አድርጌ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም፤ የወደፊቱን ሕይወቴን ተዝናንቼ አልመለከተውም፡፡ ለክፉውም ሆነ ለደጉ ተዘጋጅቼ መገኘት አለብኝ፡፡ በዚህም መሠረት እርስዎ በተሰጠዎ ኃላፊነት በሚያደርጉት የዘመቻ ዝግጅት፤ በሚፈልጉበት ቦታና በሚያስፈልግዎ ዓይነት፤ ያለ አንዳች መታከት አብሬዎ እንደምቆም አረጋግጥልዎታለሁ፡፡ እንደሚያውቁት ግፈኛው የፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ክሰብዓዊ መንፈስ ውጭ የሚያደርሰው ሥቃይና መከራ፣ ወሰንና ወደር የሌለው መሆኑ በዓለም ታሪክ ላይ ተመስክሮበታል፡፡ ይህ ሕዝብ፣ የእኔን የንጉሠ ነገሥቱን ሱዳን መድረስና በታላቋ ብሪታንያ እርዳታ በጠላታችን ላይ ለመዝመት ዝግጅት ላይ መሆናችንን ሰምቶ፣ ለነፃነቱ መሥዋዕትነትን ለመቀበል ቆርጦ ይጠብቀናል፡፡ ስለዚህ፤ ይህ የቆረጠ ዕምነትና ይህ የነቃ መንፈስ በጊዜ ብዛት ተሰላችቶ እንዳይወድቅብን፤ ሥራችንን ማፍጠን ያለብን መሆኑን ላሳስብዎ እወዳለሁ፡፡ ” ካሉ በኋላ፤ ጃንሆይ በንግግራቸው መጨረሻ ላይ እግዚአብሔር ሥራዎንና ድካምዎን ይባርክልዎ የሚለውን ምርቃት ሰጥተዋል፡፡ እንግዲህ! ከዚህ በላይ እንደታየው፤ ዊንጌት ያደረገው የመተዋወቂያ ንግግር ንጉሠ ነገሥቱን ምን ያህል እንዳስደሰታቸውና፤ ጃንሆይም የሰጡት መልስ ዊንጌትን የቱን ያህል ስሜቱን እንደነካው
ካሉ በኋላ፤ ጃንሆይ በንግግራቸው መጨረሻ ላይ እግዚአብሔር መገንዘብ ይቻላል፡፡ መቸም መልካም በሆነ የመግባባት መንፈስ
የሚጀመር ሥራ ውጤቱ እንደሚያምር አያጠራጥርም፡፡
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሱዳን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ፣ በቁጥር 101 የተመደበው የኮሎኔል ሳንድፎርድ፣ የአዛዥ ከበደ እና የጌታሁን ተሰማ ሚሲዮን፤ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ገብቶ ከሚያካሂደው መልካም ተግባር በስተቀር ሌላ የተሠራ አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመቻ ዝግጅቱ የሚጀመረው፤ ዊንጌት ከተሾመ በኋላ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እነ ዊሊያም ፕላት፤ ከፋሽስት ጋር ለሚደረገው ጦርነት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለአንዱ ግንባር እንኳ የዘመቻ መሪነት ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም በማለት፣ በሱዳን አካባቢ የሚገኙትን የኢትዮጵያን ተዋጊ አርበኞች አሰባስቦ
ሥልጠና ለመስጠትም ሆነ ለማዘጋጀት አሻፈረን ብለው የአምስት ወራት ጊዜ በከንቱ አቃጠሉ፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦር አዛዥ ዤኔራል ዌቨል እና የጦር ሚኒስትሩ አንቶኒ ኤደን የፕላትን የተቃውሞ አቋም ስለተረዱት፤ ኦርድ ዊንጌት ለሚያደርገው ዝግጅት እሱ ራሱ በቀጥታ የሚያዝበት አንድ ሚሊዮን ፓውንድ የሥራ ማስኬጃ በጀት መደቡለት፡፡ ለዊንጌት ይህ የተሰጠው በጀት ከጦር
መሣሪያዎች በስተቀር ተዋጊዎቹን ለማሠልጠኛና ለስንቅ ማደራጃ እንዲሁም ለትራንስፖርት የሚያስፈልጉትን ወጭዎች ሁሉ ስለሚሸፍንለት፤ ዊሊያም ፕላትን ከመለማመጥ አድኖታል፡፡
ዊንጌት ከተሾመ በኋላ፤ ዤኔራል ፕላት ተስፋ አድርጐ የተጠባበቀው፣ ሰውየው በጠባዩ አስቸጋሪነት የታወቀና እኔ ያልኩት ብቻ ካልተፈጸመ የሚል ስለሆነ፤ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር መጋጨቱ ስለማይቀር፤ በዊንጌት የሚተካውን መኰንን እኔ መርጨ የፈለግኩትን ማድረግ እችላለሁ ብሎ አልሞ ነበር፡፡ነገር ግን ይህ ምኞት ሊሳካለት አልቻለም፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው፤ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና ዊንጌት በጀበል አውልያ ተገናኝተው እንደተዋውቁ በመካከላቸው ከፍ ያለ የመግባባትና የመቀራረብ መንፈስ ስለተፈጠረ፤ የፕላት ምኞት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በዚህም አኳኋን፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመቻ የሚዘጋጀውና የሚራመደው በኦርድ ዊንጌት ፕላን እንጂ በዊሊያም ፕላት ጠማማ አስተሳሰብ ሊሆን አልቻለም፡፡
እንደ እንግሊዞች መሠሪ በምድር ላይ የለም። በአገራችን ላይ ከፋሺስት ኢጣልያ ያልተናነሰ፣ ትውልድ ሊረሳ የማይገባውን አረመኔአዊ በደል ፈጽመውብናል። በ2ኛው የዓለም ጦርነት እንግሊዝን የናዚ ጀርመን አካሄድ አስግቷት ነበር። ይልቊን ሂትለር ከጣልያኑ ሙሶሊኒ ጋር መቀራረባቸው። ስለዚህ የጣልያን አገራችንን መውረር ለእንግሊዝ የሂትለርን ኃይል ማዳከሚያ አንድ ስልት ነበር። አገራችን የሊግ ኦፍ ኔሽንስ መሥራች አባል እና ጥቃት ቢደርስባት ሌሎች ሊተባበሯት ግዴታ የገቡበት ማኅበር ነበር። እንግሊዝ ግን ጣልያን ከሃምሳ ዓመት በፊት በዐድዋ ድል የደረሰባትን ኃፍረት ሙሶሊኒ ሊበቀልላት መፈለጉን፣ ሚሊዮን ሥራ አጥ ጣልያኖችን አምጥቶ ለማስፈር እና ለእህል ጎተራነት ኢትዮጵያን መፈለጉን ታውቅ ነበርና ኢትዮጵያ ራሷን መከላከያ መሳሪያ እንዳታገኝ አግዳብን ነበር። ጣልያን ወረረችን። ኬንያ ሱዳን ሶማሌላንድ የእንግሊዝ ቅኝ ነበሩ። ጂቡቲ የፈረንሳይ። የጦር መሳሪያ በየትኛውም በኩል እንዳናስገባ ተስማምተው አገዱብን። ጣልያን ያለርኅራኄ በመርዝ ሳይቀር ጨፈጨፈችን። እንግሊዝ አፄ ኃይለሥላሴን እንደማይሆን አድርጋ አንገላትታ በስደት 5 ዓመት እንደ መያዣ ይዛቸው ቆየች። ጣልያን ጀርመን እና ጃፓን በጦርነቱ ሲሸነፉ፣ ያን ጊዜ ኃይለሥላሴን አጅባ፣ አርበኞቻችን አምስት ዓመት በዱር በገደሉ የተጋደሉበትን ድል፣ አገራችንን ነፃ ለማውጣት በሚል በሱዳን አድርጋ በጎጃም መጣች። ከጃንሆይ ጋር ኦርድ ዊንጌት የሚሉት ሰላይ የእንግሊዝ ኮሎኔል ነበር። ዓላማው በጣልያን ፈንታ እንግሊዝ አገራችንን ልታቀና የታሰበ ነው። ጃንሆይ ይህን ያውቁ ነበር። ነገር ግን አማራጭ አልነበራቸውም፤ አማራጭ እስኪያገኙ ቀን ይጠብቁ ነበር። ዛሬ ከኤርትራ ጋር ያለን ሰላም አይሉት ጦርነት ምንጩ የኢሳይያስ አፈወርቂ ዕውር መሪነት ብቻ ሳይሆን እንግሊዞች ቀብረው የሄዱት ፈንጂ ነው። ለማንኛውም፣ የባህር በር የማጣታችን መንስዔው ጣልያን ከተባረረ በኋላ እና ሎንዶን ላይ እነ መለስ ዜናዊ እና ኢሳይያስ በእንግሊዞች አሻጥር ኢትዮጵያን ሳያካትት በ1983 ዓም የተደረሰው ውል ውጤት ነው። እንግሊዞች የመሠሪ መሠሪ ናቸው፤ ዛሬ ድረስ አልተኙልንም። እርግጥ ነው፤ ከጃንሆይ በኋላ የመጡት መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊ፣ አሁን ደግሞ ዐቢይ ሁላቸውም የየራሳቸው ሥልጣን ላይ የመቆያ አካሄድ ነበራቸው። መንግሥቱ ልዩነቶችን በጦር ኃይል እንጂ በድርድር አልፈታም ማለታቸው። የኢሳይያስ ሎሌ መለስ ዜናዊ የባህር በር አያስፈልገንም ማለታቸው። ዐቢይ እንደ ቀዳዳ ስልቻ በየመንገዱ ዳር ያልተገባ ቃል መዝራታቸው የዲፕሎማሲን ስልት ማራከሳቸው።። በሌላ አነጋገር፣ ሊያጠቁን የሚሹ ያጠቁን መሪዎቻችን ከንቱ ስለ ሆኑ፣ ሥልጣናቸው ከአገራችን ደኅንነት ስለ በለጠባቸው ነው። እንግሊዞች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን ግፍ ትውልድ አይርሳ!
_________________________________________
“የመሪነት አበሳ” በሚለው ጽሑፍ ውስጥ (December 10, 2020፤ አንቀጽ 8)፦ “የዐቢይ መንግሥት “ህግ የማስከበር ዘመቻ”፦ የሰላምን መንገድ ሞክረናል፤ ውርድ ከራሴ ብሏል። “ሠላሳ፣ አርባ” የህወሓት መሪዎችን ወደ ፍርድ ለማቅረብ የተገባው ቃል እንደተባለው አይጠናቀቅ ይሆን?” የሚለው ዐረፍተ ነገር ጸሐፊው እንደፈራው ዕውን ሆኗል። በዚህም የዐቢይን አመራር ወላዋይነት ቊልጭ አድርጎ አሳይቷል።
“የመሪነት አበሳ” (Ethiopia Observer)