እንደምን ከርማችኋል የመልዕክተ ቅዳሜ ታዳሚዎች፡፡ ዛሬ ሁለት ብርቱ ጉዳዮች ስለተገጣጠሙብኝ ሁለቱንም በአንድ ርዕስ ስር ለመዳሰስ ወሰንኩ፡፡ የመጀመሪያው በይስሙላ ምርጫ ወይም sham election ስም እንዴት እንዴት ዲሞክራሲን አርቆ መቅበር እንደሚቻል እና ይህ አይነቱን አይን ያወጣ አንባገነናዊነት ትክክለኛው የእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አስመስሎ ለማለፍ ወይም በሕዝቡ ዘንድ illusion of normality ለመፍጠር የተደረገውን እርብርብ በመጠኑ መዳሰስ ነው፡፡ ሁለተኛው ትኩረቴ ደግሞ ከምርጫ የፖለቲካ ውጥረት ለመውጣት ሲባል የአገዛዝ ሥርአቱ እጅግ አስደንጋጭና አሰቃቂ የጭፍጨፋ ተግባርን እንደ ትኩረት አቅጣጫ ማስቀየሪያ መጠቀም ላይ በማተኮር በአሪሲ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ የተፈጸመውን ማንነት ተኮር ጥቃት መዳሰስ ይሆናል፡፡
1ኛ/ የይምሰል ምርጫ መዘዝ፡
አብይ አህመድ ያካሄደውን የይምሰል ምርጫ በተመለከተ ከአምስት ወር በፊት ይመስለኛ “የግፍ አገዛዝን በምርጫ ካርድ ማጽናት ያብቃ” በሚል 29 ገጽ የቅድመ ዳሰሳ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ በዛ ጽሑፈ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጥኩት ይህ ንርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ የግፍና የጭካኔ አገዛዝን በላዩ ላይ የሚያነግስበት፣ የአፈናውን ሸምቀቆ በራሱ ፈቃድ አንገቱ ላይ የሚያጠብቅበት እና አብይ አህመድ አገሪቱን ወደ ከፋ እልቂትና አዳዲስ ጦርነቶች እንዲከታት በምርጫ ካርድ መፍቀድ ነው፡፡ በመሆኑም ሕዝቡም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫውን በጥንቃቄ በማየት ከቻሉም ከተሳትፎ ራሳቸውን እንዲያገሉ ጥሪ የሚያቀርብ ነበር፡፡ ያ አልሆነም፡፡ ነገር ግን የአብይን ፍጹም ኢ ዴሞክራሲያዊ የሆነ፣ አሳታፊነት የሌለው፣ ፍትሃዊና ነጻ ያልሆነ ምርጫ ለማድመቅ የተሰለፉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የአፍሪካ ሕብረትና የኢጋድ አይነት ታዛቢዎች፣ በሲቪክ ማህበራት ስም የተሰባሰቡ አገር በቀል ድርጅቶች፣ በዋነኝነት ደግሞ በፓሪስ ፕሪንስፕልስ ይመራል ተብሎ የሚገመተው በመንግስት በጀት የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይህን የማጭበርበርና በአፈና እና ግጭቶች ውስጥ የተጠናቀቀን ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ ነበር በማለት የአገዛዝ ሥርአቱን ውንብድና ለመሸፈን የሰጡት ምስክርነት ዲሞክራሲን አርቆ ለመቅበር የተደረገ እርብርብ አድርጌ ቆጥሬዋለሁ፡፡
በውሸት እና የአፈና ምርጫ የዲሞክራሲ ባህሎችን ቀብሮና አፈር አልብሶ ለአፋኝና ጨካኝ የአገዛዝ ሥርአት landslide victory አጎናጽፎ በምርጫ ስም የሚደረግ አፈና በቅርቡም በMyanmar (Burma) እና በታንዛኒያ ሲካሄድ አይተናል፡፡ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ የሕዝቡን ቁጣ ተከትሎ የተካሄዱትን ምርጫዎች ሲያወግዝ አይተናል፡፡ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰራበትን ፕሮፓጋንዳ ችላ ብሎ በመተው ወይም ኢትዮጵያ ትመርጣለች/መረጠች በሚል የተሰራበትን ድግምት የመሰለ የፕሮፓጋንዳ illusion of normality በመቀበል ይመስላል በምርጫው ሂደትም ላይ ሆነ በተፈጸመበት ሸፍጥ ላይ ምንም ድምጹን ባለማሰማት አለም አቀፍ ተቋማትም የምርጫውን ሂደት በመቀበል ለቀጣዩ የግዞትና አፈና ምዕራፍ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል፡፡
እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ የአገሩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በዚህን ያህል ደረጃ በምርጫው ላይ ምንም አይነት ተነሳሽነት ካጣ፣ አፈናውንም በጸጋ ወይም በፍርሃት ከተቀበለ፣ ለቀጣዩም አፈና እና ጭካኔ የተሞላው የግፍ አገዛዝን ለመሸከም ትከሻውን ካደላደለ “ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ ማንም አይቀበለውም” እንደሚባለው የአለም አቀፉም ማህበረሰብ በምርጫው ዙርያ የተፈጸመ ከፍተኛ ጥፋቶችን እና ወንጀሎች ላይ የሚያተኩርበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ የሕዝቡ ዝምታ እስከመቼ ይዘልቃል የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ለጊዜው ዝምታው ክፍን እንደመቀበል፣ ራስን ከግፈኞች ጋር አስማምቶ ለመኖር መፍቀድን፣ ጥልቅ ፍርሃትን፣ ተስፋ መቁረጥን እና ግፍን መለማመድ ያሳያል፡፡
2ኛ/ የአሪሲው ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ
በኦሮሚያ ክልል የሚፈጸሙ ማንነት ተኮር ጭፍጨፋዎች፣ አውቶቢስ ሙሉ ሰዎችን አፍኖ በመሰወር ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅና የተጠየቁትን ገንዘብ ማምጣት ያልቻሉ ሰዎችን መግደል፣ መንገዶችን ዘግቶ የዜጎችን እንቅስቃሴ መገደብ፣ ሺዎችን ማፈናቀልና ማዋከብ የተለመዱ ክስተቶች ሆነዋም፡፡ በተለይም በክልሉ ውስጥ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ አነጣትረው የሚፈጸሙት ግድያዎችና ማሳደዶች በአገዛዝ ሥርአቱ የሥልጣን እድሜል ልክ ቢሆንም ድርጊቶቹ ሲባባሱ እንጂ ሲቆሙ አይስተዋልም፡፡ ትልቁ ጥያቄ ይህ ለምን ሆነ የሚለው ነው፡፡ እነዚህን ድርጊቶች በአካባቢው ላይ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወይም ራሱ መንግስት ያደራጃቸው ሚሊሺያዎችና ሌሎች ታጣቂዎች እንደሚፈጽሟቸው በርካታ ማስረጃዎችና ሪፖርቶችም ወጥተዋል፡፡ አብዛኛዎቹን ጥቃቶች በክልሉ የሚንቀሳቀሱና መንግስት ሽኔ የሚላቸው ታጣቂዎች የፈጽሟቸው ለመሆኑ በቪዲዮና በምስል የተደገፉ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ራሱ መንግስት ያሰማራቸው ታጣቂዎች በጥፋቱ ላይ ተሰማርተውና የወንጀሎቹ ተካፋይ ሆነው ታይተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በእንዲህ ያሉ ወንጀሎች ላይና ማንነት ተኮር ጭፍጨፋዎች ላይ መሳተፉን፣ የአቶ ቤቴን የጭካኔ ግድያና 15 የሚሆኑ የከረዩ አባገዳዎችን ግድያ ራሱ መንግስት የፈጸመው መሆኑን የመንግስቱ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አረጋግጧል፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት በተከታታይ በአሪሲ ውስጥ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና በአካባቢው በሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ባለው ጭፍጨፋና ግድያ የክልሉና የአካባቢው የመንግስት ታጣቂዎች ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ለሰብአዊ መብት መርማሪ ተቋማትም ደርሷል፡፡ አሁንም የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በምርጫው ዋዜማ በምስራቅ አርሲ ሦስት ወረዳዎች የተፈጸመው ጥቃትና ግድያ የአገዛዝ ሥርአቱ የሕዝቡን አትኩሮት ከተጭበረበረው ምርጫ ላይ ወደ አሰቃቂ ወደሆነው እልቂት እንዲያተኩር ሆን ብሎ አካባቢው ላይ ባሉ ታጣቂዎች እንዲፈጸም ያመቻቸው መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህ የብልጽግና መገለጫና የተለመደ ስልት ተደርጎ የተወሰደው አንድን የፖለቲካ ስብራትና ኪሳራ በሌላ አቅጣጫና ትኩረት ማስቀየሪያ አሰቃቂ ተግባር የመፈጸም ተደጋጋሚ አድራጎት የአዘዛዝ ሥርአቱ ምን ያህል ለሰው ልጅ ነፍስ የማይራራ፣ ለዜጎች ሕይወት የማይጨነቅ፣ ጨካኝና አደገኛ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡
ብልጽግና ፓርቲ እስካለ ድረስ ግፉም፣ ጭፍጨፋውም፣ ጦርነቱም፣ ሰቆቃውም፣ የኑሮ ውድነቱም፣ መከራውም ይቀጥላል የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ግፉ እንዲነጥፍና በማንነት ላይ ያነጣጠሩትም ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች እንዲያበቁ የአገዛዝ ሥርአቱን መታገል የግድ ይላል፡፡
መልካም ሰንበት!
የፎቶ ምንጭ፦ MARCO SIMONCELLI / AFP በ2026 ዓ.ም. ግንቦት 27 ጅማ ከተማ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የሚያሳይ የምረጡኝ ቅስቀሳ ፖስተር።