የዓለም ዋንጫ ሰሞን ለእኛ ሰፈር ልጆች ደስ የሚል ረጅም ዓመት በዓል ነበር። ቴሌቪዢን ብርቅ በሆነበት፣ የጣሪያ ላይ አንቴና የሀብታም ቤት መለያ በሆነበት በዚያ ዘመን፤ የዓለም ዋንጫን ለማየት የማይጓጓ የለም። እንዲህ አይነት ቤቶችን ደጅ መጥናት ግድ ይለን ነበር። እንቡሹ ጓደኛችን ነው፤ ቤታቸው ከለር አልባ ትልቅ ቴሌቪዢን ነበረ። በእነሱ ቤት ማራዶናን፣ ዚኮን፣ ፕላቲኒን ወዘተ በቀጥታ ስርጭት አይተናል። የኳስ ጥበባቸውን ቀስመናል። የልጆች ክፍለ ጊዜን አይተናል። በአባባ ተስፋዬ ተረቶች ተደምመናል። በፈርዲናል ኩምክና ስቀናል፣ በእንግሊዝ ቢግሊግ ሶከር እግር ኳስ ተዝናንተናል። እምቡሹ (በኃይሉ ሶሎሞን) ዛሬ የት ትሆን? ባለህበት ሰላም ሁን።
ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖ የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እዚህ ቅርቤ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በሜክሲኮ፣ ካናዳና አሜሪካ አዘጋጅነት ከትላንት በስቲያ ተጀምሯል። እንደዚያ የልጅነት ዘመን ብርቅ ሆኖብኝ በመጓጓት የማየት ስሜት ባይኖረኝም፤ እንደ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ በቴሌቪዥን እመለከታለሁ። ከዚህ ይልቅ ግን ዛሬ ከኳስ ጋር በተያያዘ የነበረኝ የልጅነት ትውስታ ገኖ ይሰማኛል።
ልዩ የኳስ ፍቅር ያላቸው የኛ ሰፈር ልጆች የ“አባሲዮኒ” ሜዳ ተጎራባች መንደር ነዋሪ በመሆናቸው (በመሆናችን) ነው ከኳስ ጋር ቁርኝት የፈጠርነው። “አባሲዮኒ” የፖሊስ ስፖርት ክለብ እግር ኳስ መጋጠሚያ ሜዳ ነው። ከአዲስ አበባ ስታዲየም ቀጥሎ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚታው በዚህ ሜዳ ላይ ነበር። ያውም በነጻ!
ከ1970 ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80 ዎቹ አጋማሽ ቅዳሜና እሁድ በዚህ ሜዳ ይደረግ በነበረው ጨዋታ የተለያዩ ክለቦች በደጋፊዎቻቸው ታጅበው የኳስ ጥበባቸውን ሲያሳዩ ልዩ የደስታ ስሜትን ይፈጥሩ ነበር። በእነዚህ ቀናት ሰፈራችን በሕዝብ ይጨናነቃል። ከሜዳው ወደ ቤት፣ ከቤቱ ወደሜዳው የሚተመው ሁሉ፤ ስለ ኳሱ ብቻ እያውካካ በመሆኑ የድምጽ ብክለት ሳይሆን የሚሰማን ጥዑም ዝማሬ አይነት ነበር ። ከመሳለሚያ አማኑኤል፣ ከኮልፌ፣ ከአዲስ ከተማ፣ ከመርካቶ፣ ከተክለሐማኖት፣ከአብነት ከልደታ፣ ከሦስት ቁጥር ማዞሪያ፣ ከቀራኒዮ መድኀኒዓለም ወዘተ ወደ አባሲዮኒ የሚተመው ህዝብ ብዛት የሚገርም ነበር።
እኛ ታዳጊዮች እነዚህ ቀናትን እንደ ዓመት በዓላችን ነው የምንቆጥራቸው። ኦቾሎኒው፣ ሸንኮራወ፣ ማስቲካው፣ ባለ ክሬሙ በረዶው፣ ቆሎው . . . ወዘተ ሻጩ ሲተራመስ እኛንም የሚያውቀን፣ የሚገዛልን አናጣምና ውር ውር ማለታችን አይቀርም። በአንድ ቀን ሁለት ወይንም ሦስት ጨዋታዎችን በተከታታይ መመልከት የተለመደ ነበር። ስታዲየም ገንዘብ ከፍሎ በመግባት ማየት ያልተቻለውን ተደናቂ ተጨዋች በዚህ ሜዳ ማየት ይቻላል። የኳስ ጨዋታ ጥበባቸው ይማርካል። ዛሬ ተዘነጉኝ እንጂ ንጉሴ ገብር፣ ተስፋዬ ፈጠነ፣ ክብሮም፣ አባያ . . . ወዘተ የሚባሉ ተጨዋቾች ኳስን ሲያሽሞነሙኗት ለጉድ ነበር። ሲቪልና ወታደራዊ ክለቦች እንደ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ፣ መቻል፣ ፔፕሲ፣ መሐንዲስ፣ ማመላለሻ፣ መገናኛ . . . ወዘተ ክለቦች መደሰቻዎቻችን ነበሩ።
ሁሉም ክለቦች አቋማቸውን አጠናክረው ለግጥሚያ ሲሰለፉ በደጋፊዎቻቸው ማበረታቻ ዜማ ይታጀባሉ።
“ሲጊናል፣ ሲጊናል . . . ሳይዋጋ ድል አለው!” የሚለው ማንቂያና ማበረታቻ ዜማ የመገናኛ ክለብ ነበር። ከሰዉ ብዛት አንጻር ጠባብ የምትባለው አባሲዮን ሜዳ ትናፈቃለች። የእግር ኳሱን ሜዳ ዙሪያና ከውጪ የሽቦ አጥር ከቦ የሚታው ህዝብ ጎል ሲገባ ይጮሃል። ሆ. . . ሆ !!
እኛ ታዳጊዎች (ቀልጠፍ ያልን) በትላልቆች እግር ተሹሎክሉከን ከፊት ሆነን ጨዋታውን በግላጭ እንመለከታለን። የኳስ አጨዋወት ጥበብን እንቀስማለን። ያየነውን በሰፈራችን ሜዳ ላይ በምናደርገው ጨዋታ እንተገብረዋለን። በዚያን ዘመን ከትምህርት ቤት እንደተመለስን መክሰስ’ኳ የመብላት ትእግስት ሳይኖረን ኳሳችንን ይዘን ወደ ሰፈራችን ሜዳ መሮጥ ነው። የእኛ ሰፈር ልጆች ሁሉም ማለት ይቻላል ኳስን የመመልከት ፍቅርም ሆነ የመጫወት ጥበብን የተካኑ ናቸው። ኳስ ይችላሉ። አስገራሚው ነገር ግን ለማናችንም መክሊታችን እግር ኳስ አልሆነም። ሁላችንም በሌላ ሕይወት መስመር ነው የተጓዝነው። ይህ ይገርመኛል።
አዲስ አበባ ውስጥ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ጎን በሰሜን አቅጣጫ የሚገኘው ይህ መንደር ” የሰላም ሰፈር ” እና የአባሲዮኒ ሜዳ ዛሬ ላይ በጣም ጭር ብለው ይታያሉ ። እንዲያ አይነት ታሪካዊና አስደሳች ሁኔታን ያሳለፉ አይመስልም። ትዝታ ብቻ!። ከወላጆቻችን የሰማነውማ ቀደም ባለው ዘመን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ጃንሆይ) በተሰራላቸው ጎጆ ውስጥ በልዩ ክብር ሰገነታ ቸው ተቀምጠው ከሹማምንት ጋር ኳስና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትርኢቶችን ይመለከቱ ነበር ይባላል። አይ ጊዜ?!
እነሆ የዓለም ዋንጫ ከተጀመረ 100 ዓመት ሊሞላው ነው:: ይህ 23ኛው የዓለም ዋንጫን ማን ያነሳ ይሆን? ካናዳን’ኳ ተስፋ አላደርግም፤ ለሆኪ እንጂ ለእግር ኳስ አልተፈጠረችም። የሚገርመው ካናዳ በየመንደሩና ትምህርት ቤቱ የአዲስ አበባ ስታዲምን የሚልቁ፤ የቅርጫት፣ የሩጫና የእግር ኳስ መጫወጫን አጣምረው የያዙ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሜዳዎች አሏት። አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር (ያውም ተማሪዎች) ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም። ውበታቸውን እንደጠበቁ በእንክብካቤ ውስጥ ይታያሉ። አንዳንዴ ብቻዬንም ቢሆን ኳስ ይዤ አብዶ ስጠልዝ እገኛለሁ። ሰዉ ለኳስ ፍቅርም፣ ጊዜም የለውም።