በግብፃውያን ዘንድ ያለው የማንነት ክርክር

በግብፃውያን ዘንድ ያለው የማንነት ክርክር

አህመድ ኤል ፊሻዊ የተባለ ግብፃዊ የፊልም ተዋናይ፥ ማንነቱ አፍሪካዊ እንጂ አረብ እንዳልሆነ በመናገሩ፥ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ሠፊ መነጋገርያ ሆኗል። ግብፅ ውስጥ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት ተዋንያን መካከል አንዱ የሆነው፥ ኤል ፊሻዊ፥ ከአንዲት ጋዜጠኛ ጋር፥ ስለ ህይወቱ እና ሥራው በሚያወራበት ወቅት፥ ማንነቱን በተመለከተ ጥያቄ ሲቀርብለት፥ “እኛ የምንገኘው በአረብ ክልል አይደለም፤ አፍሪካ ውስጥ ነን።”በማለቱ፥ ጋዜጠኛዋ አታካራ ገጠመችው።አንዱ ጥያቄዋ፥”እና አረብ መሆንክን እየካድ ነው?” የሚል ነበር። እርሱ ግን፥ “በጭራሽ እየካድኩ አይደለም፤ ቋንቋየ አረብኛ ነው። የማወራው አረብኛ ግን በቀበሌኛ ዘየ ነው።” በማለት መለሠ።ጋዜጠኛዋ ግን አሁንም በድጋሚ “ግን አረብ አይደለህም?” ትለዋለች። “እኔ አፍሪካዊ ነኝ፥ ፈርኦናዊ”። ወዲያውኑ፥ ንግግሩ፥ በማህበራዊ ሚዲያ መዘዋወር ጀመረ። የተወሰኑ አስተያየት ሰጪዎች የአረብ ማንነቱን ክዷል በማለት የሰላ ትችት ሰነዘሩበት። ሌሎች በተቃራኒው፥ አፍሪካዊነቱ ላይ በማተኮሩ ምስጋናቸውን አቀረቡለት።

ይህ ንትርክ በቅርብ የጀመረ አይደለም። ከረጅም ዘመናት ጀምሮ፥ ግብጾች ማንነታቸው ምን እንደሆነ እና የት እንደሚመደቡ ፥ሲወያዩበት እና ሲከራከሩበት የነበረ ጉዳይ ነው። አረቦች ነን፣ ወይስ አፍሪካውያን ወይስ ደግሞ ፈርኦናዊያን? በሚል። እነዚህ ተጣምረው የሚኖሩ፥ ሦስት ማንነቶች ዘርፈ ብዙ የሀሪቱን ታሪክ የሚያሱ ቢሆንም የትኛው ያመዝናል የሚለው ግን ሁሉንም አያስማማም። በ1950ዎቹ ጋማል አብዱልናስር፥ አገራቸው የአረብ ብሔርተኝነት አንድነትና ዋነኛ አንቀሳቃሽ በማድረግ አፍሪካዊ መሠረቷንም በማጉላት ይናገሩ ነበር።ከእርሳቸው ቀጥለው ወደ ሥልጣን የመጡት አንዋር አልሳዳት፥ ግብፃውያን አረብ እንደሆኑ ማስረዳት”ምንም ክርክር የማያሻው ጉዳይ ነው ይሉ ነበር።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፥ የጥንት ፈርዖናዊ ሥልጣኔ ነው መድረኩን የተቆጣጠረው። የንጉሣዊ ሙሚዎች ሰልፍ፣አዳዲስ ሙዚየሞች፣ ትላልቅ የአርኪኦሎጂ ስራዎች የአገሪቱን ጥንታዊ ታሪክና ማንነት የሚያጐሉ ናቸው። ነገር ግን ለብዙ ግብጻውያን፣ እነዚህ ማንነቶች እርስ በርሳቸው አይጋጩም፤ ይልቁንም በሰላም አብረው ይኖራሉ።አፍሪካዊም፣ፈርኦናዊም፣ አረብም  በአንዴ መሆን እንችላለን በሚል።

Share this post

Post Comment