በቅርቡ ወደ ኢትዮጲያ ለአጭር ጊዜ በሄድንበት ወቅት ሃረር እና ባቢሌንን የመጐብኘት እድል አግኝተን ነበር። በብዙ የአገሪቱ ቦታዎች ላይ የፀጥታ ችግር እንዳለ ብናውቅሞ፤ እዚያ አካባቢ ብዙም ስጋት እንደሌለ ወዳጆቻችን ነግረውን ስለነበር ነው ወደዚያ ያቀናንው።እንደተነገረንም የሐረር ጉብኝታችንን ያከናወንው ያለምንም ፀጥታ ችግር ነበር። ከሐረር ወደ ባቢሌ የሚወስደው መንገድ ላይ ያጋጠመን ሁኔታ ግን ስጋትን ፈጥሮብን ነበር። በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለው ርቀት 30 ኪሎሜትር ብቻ ነው። ከሃረር ወጥተን ትንሽ ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን ሶስት ዩኒፎርም የለበሱ፣ ሁለቱ ደግሞ ሲቪል ልብስ የለበሱ አምስት ታጣቂዎች ፤ ሚኒባሱን በኃይል በመደብደብ አስቆሙን። በመኪናው ውስጥ ሁለት ነጭ ሴቶችና ሶስት ክልስ ልጆች እንዳሉ ካዩ በኋላ ካስጐብኛችን ጋር ትንሽ ተነጋገረው እንድንሄድ ፈቀዱልን።አስጎብኚያችን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል መሆናቸውን ነገረን።ለኔ ግን ብዙም አልተዋጠልኝም። ምንም ሳያደርጉን በሰላም በማለፋችን ግን ተመስገን አልኩ። የግመል ገበያውን ማየቱ ሚስቴን እና ልጄን እንዲሁም አብረውን ያሉት ወዳጆቻችንን ያስደስታቸዋል ብየ ባስብም፤ እንዲህ አይነት ጣጣ ውስጥ መግባቱ ግን አስፈላጊ ነበር ወይ ብየ ማሰብ ጀመርኩ።
የግመል ገበያው ቀድሞ ከሚገኝበት ከባቢሌ ከተማ ስድስት ኪሎሜትር እንዲርቅ ተደርጓል። የተዘዋወረበት ምክንያት በኦሮሚያ እና በሶማሊያ ክልል መካከል በተፈጠረ ውጥረት መሆኑን ለመረዳት ቻልን፡፡ይህም ሶማሊያዎቹ የእኛ ገበያ ስለሆነ ወደ እኛ ክልል መካተት አለበት ብለው ስለወሰኑ ነበር።ከባቢሌ ወጣ እንዳልን፤ አንድ ፍተሻ ጣቢያ አጋጠመን።በአብዛኛው የሚቆጣጠሩት የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ስለሆነ መፈተሽ የለብንም በማለት አስጎብኚያችን ተሟገተ። ጠባቂው የሚያወራው በሶማልኛ ነበር።ከዚያ ሂዱ ይበለን አይበለን ግልፅ ሳይሆን፤ ሾፌሩ አስነስቶ መንዳት ጀመረ። በሁኔታው ብዙም ደስ ባይለኝም ምንም ማለት አልቻልኵም። አለፍ እንዳልን የያናቸው ወታደሮች የትጥቃቸው ብዛት ያስፈራል።
ባቢሌንን እንዳለፍን ትልቅ የተፈናቃዬች መጠለያ ጣቢያ አየን።ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በሸራ ተጠልለው ያሉ ሶማልያዎች ነበሩ።ቀጥሎ ገበያው ጋር ደርሰን መኪናችንን መንገድ ዳር አቁመን ወደ ቀኝ ታጥፈን ገባን። ገና ከጥዋቱ አራት ሰዐት ቢሆንም ፀሐይዋ ጠንከር ብላለች። ገበያውን በመዘዋወር መጎብኘት ጀመርን።

ነገር ግን ወዲያውኑ፥ ዩኒፎርም ሸሚዝ እና ሽርጥ የለበሰ ሰው የተቆለመመ ዱላ ይዞ ወደ እኛ መጣ። ወታደር እንደሆነ ተረዳሁ ፤ ፊቱ ላይ የተኳለው ኩል የማፊያ ገፅታ ሰጥቶታል። ህጋዊነታችንን ለማሣየት ወድያው ገበያውን ለመጎብኘት የከፈልንበትን ደረሰኝ አሳየሁት።ነገር ግን በተሰባበረ አማርኛ በፖሊስ ጣቢያ ማለፍ እንደነበረብን ነገረኝ። እንደዚህ አይነት ህግ መኖሩን አላውቅምና ከአስጐብኛችን ጋር አገናኘሁት።መጀመሪያ በእርጋታ፣ ከዚያም በኃይል ቃላት መለዋወጥ ጀመሩ። በኦሮምኛ ስለነበር የሚያወሩት፤ የሚባባሉትን መረዳት አልቻልኩም።ንግግራቸው ይበርዳል ብየ ተስፉ ባደርግም አተካራቸው ቀጠለ። ልጄ፣ ባለቤቴ እና ወዳጆቻችን አንዴ ገበያውን ያያሉ፤ አንዴ አስጕብኛችንን እና ወታደሩን ይመለከታሉ።መፍራታቸው ግልፅ ነው፤ ባለቤቴ ወታደሩ ገንዘብ ፈልጒ ከሆነ ለምን የተወሰነ ሰጥተን አንገላገለውም አለችኝ። እኔም የመጣልኝ ሀሳብ ነበር ግን ያንን ለማለት ክፍተት አላገኘሁም። ሰውየው ግን የሚላቀቀን አልሆነም። ብዙም ሳንቆይ አስጒብኝውን እየጓተተ ይዞት መሄድ ጀመረ። ከዚያም ሽጉጥ አወጣ። እኛ ከሓላ መከተል ጀመርን፤ አስጉብኛችን ተወኝ እያለ ቢማፀነውም ወታደሩ ግን ማንገላታቱን ቀጠለበት። በሁለት እጁ አንገቱን ቆለመመው። ከዚያ አስፋልቱ ጋር ደርሰን። አሁንም ይዞት መንገዱን ሲቀጥል ወዴት እንደሚወስደው ስላልገባኝ ባለቤቴን እና ጓደኛዋን እና መኪና ውስጥ እንዲገቡ ጠይቄአቸው እኔ እና የወዳጃችን ባለቤት ሁለቱን መከተል ጀመርን። መጠለያ ካምፕ ውስጥ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ነበር የወሰደው፤ እዚያ ሃላፊው የሚመስል ቦርጫም ሰውየ በትህትና አናገረን። ሌሎቹ እንግዶች የት ናቸው በማለት ጠየቀኝ። መኪና ውስጥ ናቸው ስለው ፤ ሁሉንም ይዛሃቸውና አለኝ። ወዲያው ይዤያቸው መጣሁ።ሁሉም ከመጡ በሗላ የእያንዳንዳችንን ፓስፖርት ተመለከተ። ይዞን ከመጣው ሰውየ አንፃር አለቅየው የተረጋጋ ሰው ነበር። ሊያረጋጋን ሞከረ፤ እናንተ ምንም ያደረጋችሁት ነገር የለም። ችግሩ ከአስጐብኛችሁ ነው፤ ካርድ፣ ባጅ እና ጃኬት ስላላደረገ እንደሆነ ገለፀ። ከዚያ አሰናብቶን በእፎይታ ወደ መኪናችን ተመለስን። ቶሎ ለመለለስ በማሰብ መኪና ውስጥ መሣፋር ጀመርን። በዚህ ጊዜ የመጀርያው ወታደር በባጃጅ እየከነፈ መጥቶ እኔን ነጥሎ ጠርቶ በግልፅ ገንዘብ ጠየቀኝ።ሳላቅማማ ሃያ ዪሮ ሰጠሁት። ከዚያ እያበረረን ምንም ሳንቆም ሐረር ገባን።የእኛ ዋና ስጋት የፀጥታ ችግር ነበር። በዚህ ብር መገላገልም አንድ ነገር ነው።
